April 21, 2014
ፓትሪያርኩ ኢትዮጵያውያን ግብረ ሰዶማዊነትን እንዲዋጉ ጥሪ አቀረቡ
ሁለት መቶ ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ይሳተፉበታል የተባለውና ሚያዝያ 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰላማዊ ሠልፍ እንዲቀር የተደረገው፣
ከቤተ ክህነት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በቀረበ ቅሬታ መሠረት መሆኑ ተገለጸ፡፡ ቅሬታው ከሰላማዊ ሠልፉ አዘጋጆች አንዱ የነበረው ማኅበረ ወይንዬ ተክለሃይማኖት ሕጋዊ አይደለም የሚል መሆኑን የማኅበሩ ሊቀመንበር መምህር ደረጀ ነጋሽ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሰላማዊ ሠልፉ መከልከሉን የሚገልጸውን ደብዳቤ የተረከበው ከማኅበረ ወይንዬ ጋር በመሆን ለከንቲባው ጽሕፈት ቤት ሰላማዊ ሠልፍ ለማካሄድ ጥያቄ አቅርቦ የነበረው የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም መሆኑን የሚናገሩት መምህር ደረጀ፣ የፎረሙ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ፀጋዬ ገብረ ፃድቅ የሰላማዊ ሠልፉንም ሆነ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ውይይት መሰረዙን በቃል ቢያሳውቋቸውም፣ እስካሁን ድረስ የደብዳቤውን ኮፒ ማግኘት አለመቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡
ማኅበሩን በአሁኑ ወቅት ሕጋዊ አይደለም የሚለው ጉዳይ መሠረት ያለው ተጨባጭ ነገር ሳይሆን፣ ማኅበሩና ፎረሙ ይዘው የተነሱትን አቋም መቃወምን ዒላማ ያደረገ መሆኑን
መምህር ደረጀ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለከንቲባው ጽሕፈት ቤት ቅሬታ ያቀረቡት በቤተ ክህነት ያሉ የተወሰኑ ሰዎች ናቸው ወይስ ቤተ ክህነት በግልጽ የላከቻቸው ተወካዮች የሚለውን
ለመረዳት ጥረት እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡
አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የቤተ ክህነት ሠራተኛ የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰላማዊ ሠልፉ የታገደው በቤተ ክህነት ጥያቄ መሆኑን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ በቤተ ክህነት ጥያቄው የቀረበው ባለፈው ሳምንት ሲሆን በሸዋ ሀገረ ስብከት ዕውቅና ተሰጥቶት የነበረው ማኅበረ ወይንዬ ተክለ ሃይማኖት ሕጋዊ አይደለም መባሉ ለሰላማዊ ሠልፉ መታገድ ዋና ምክንያት ሆኖ መቅረቡን ያስረዳሉ፡፡
ጉዳዩን በሚመለከት ማኅበረ ወይንዬ ለሲኖዶስ ጥያቄውን እንደሚያቀርብ የጠቆሙት መምህር ደረጀ፣ ማኅበራቸው በቀጣይ ከፀረ ግብረ ሰዶማዊነት እንቅስቃሴ ውጪ ቢደረግ እንኳን እንቅስቃሴውን ሌሎች ኢትዮጵያውያን እንደሚቀጥሉበትና እስከ ክስም ሊሄድ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሳቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የይቅርታ ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ በቅርቡ ለፓርላማ ቀርቦ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ላይ ግብረ ሰዶም ይቅርታ የማያሰጥ ተደርጐ ከሌሎች ወንጀሎች ጋር ተዘርዝሮ ተቀምጦ ነበር፡፡ የይቅርታ ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጁ በአሁኑ ወቅት በሕግና ፍትሕ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ እጅ የሚገኝ ሲሆን፣ የግብረ ሰዶም ወንጀል ይቅርታ የማያሰጥ ተደርጐ የተጠቀሰበት አንቀጽ መሰረዙን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን ለአሶሼትድ ፕሬስ ፀረ ግብረ ሰዶማዊነት የመንግሥት ሳይሆን የተወሰኑ ቡድኖች አጀንዳ መሆኑን፤ ስለዚህም በሕግ የተቀመጠው ቅጣት በቂ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ለአሶሼትድ ፕሬስ ገልጸው ነበር፡፡
ግብረ ሰዶማዊነት በኢትዮጵያ በሕግ የተከለከለ ሲሆን እስከ 15 ዓመት በእስር ያስቀጣል፡፡ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት አንድን ግለሰብ ለኤችአይቪ ቫይረስ ማጋለጥ ደግሞ በ25 ዓመት እስራት ያስቀጣል፡፡
በሌላ በኩል ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ሃይማኖታዊ ቡራኬ የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ኢትዮጵያውያን ግብረ ሰዶማዊነትን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ግብረ ሰዶማዊነትን እንደምትዋጋ አስታውቀዋል፡፡
Source: Ethiopian Reporter
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen