April 29/2014
ሚያዚያ ፳፩ (ሃያአንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዓለማቀፉ የጋሴጠኞች ተንከባካቢ ድርጅት(ሲፒጄ) ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን በ9 ጸሀፍያን ላይ የወሰደው የእስር እርምጃ፤ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ከተቃጡ የከፉ እርምጃዎች አንዱ ነው ብሏል።
“የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሰላማዊ መንገድ ሀሳብን መግለጽን እንደወንጀል እየቆጠሩት ነው” በማለት ነው -የሲፒጄ የምስራቅ አፍሪቃ ወኪል-ቶም ሩድስ-እርምጃውን የኮነኑት።
እሁድ ዕለት የመንግስት አቃቤ ህግ በ አዲስ ጉዳይ ዋና አዘጋጅ በ አስማማው ሀይለጊዮርጊስ፣ በፍሪላንስ ጋዜጠኞቹ በተስፋለም ወልደየስ እና በ ኤዶም ካሣዬ፣ እንዲሁም በጦማርያኑ በ አቤል ዋቤላ፣በ አጥናፍ ብርሀኔ፣በማህሌት ፋንታሁን፣ በዘላለም ክብረት እና በበፈቃዱ ሀይሉ ላይ ከውጪ ድርጅቶች ጋር ይሠራሉ፣ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀምም በሀገሪቱ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ይንቀሳቀሳሉ.. የሚል ክስ እንደመሰረተባቸው ሲፒጄ አውስቷል።
ተስፋለም፣አስማማውና ዘላለም ለፊታችን ሚያዚያ 28 ቀሪዎቹ ደግሞ ለሚያዚያ 29 እንደተቀጠሩ ከሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች የደረሰውን መረጃ ዋቢ አድርጎ የጠቀሰው ሲፒጄ፤ በታሳሪዎቹ ላይ እስካሁን መደበኛ ክስ እንዳልተመሰረተ ጠቁሟል።
ሲፒጄ በመግለጫው-ፀሀፊዎቹ ዞን ዘጠኝ ተብሎ የሚጠራ የገለልተኛ አክቲቪስቶች ስብስብ አባል ሆነው የተለያዩ ዜናዎችንና ጽሑፎችን ይጽፉ እንደነበር አመልክቷል።
“ዞን ሰጠኝ የተሰኘው ስያሜ ከቃሊቲ የተገኘ መሆኑና የጸሐፊዎቹ መሪ ቃል፦”ስለሚያገባን እንጦምራለን” የሚል መሆኑ በሲፒጄ መግለጫ ተመልክቷል።
ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ከደህንነቶች በሚደርስባቸው ወከባ ምክንያት ላለፉት ሰባት ወራት ዘግተውት የቆዩትን የፌስቡክ ገፃቸውን ዳግም በከፈቱ ማግስት መሆኑን እንደተረዳም የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ተቋሙ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ አማካሪ የሆኑት ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ፦”የታሰሩት ጋዜጠኞች አይደሉም፤ እስሩ ከጋዜጠኝነት ሥራቸው ጋር የተገናኘ አይደለም። ከከባድ ወንጀል ጋር የተገናኘ ነው” ማለታቸውን ሲ.ፒ.ጄ ጠቁሟል።
“በጋዜጠኝነት ወይም ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ላይ የቃጣነው በትር የለም። ሆኖም ማንም ቢሆን ሙያውን ሽፋን በማድረግ ወንጀል ለመፈፀም ሲሞክር በህግ ይጠየቃል” ሲሉም አክለዋል-አቶ ጌታቸው ረዳ።
“የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ወደለየለት ፈላጪ ቆራጭ አገዛዝ ማዘንበላቸውን እንዲገቱና በሀገሪቱ ነፃ ሀሳቦች ይንሸራሸሩ ዘንድ እንዲፈቅዱ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል-ሚስተር ቶም ሩድስ።
የታሰሩት 9ኙም ጸሀፊዎች በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል። ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎችና ሌሎች ድርጅቶችም የ ኢትዮጵያ ባለስልጣናት በጦማርያኑ እና በጋዜጠኞቹ ላይ የወሰዱትን እርምጃ በማውገዝ ፤ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ዛሬ አዲስ አበባ የሚገቡት የ አሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ እስረኞቹን እንዲፈታ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የተለያዩ ዓለማቀፍ የሚዲያ ተቋማትም ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንግስት በ9ኝ ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ላይ የወሰደውን የማሰር እርምጃ ሽፋን ሰጥተውታል።
ከሚዲያ ተቋማቱ መካከል ኤ.ቢ.ሲ ኒውስ፣ ሲ ኤን.ኤን፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ሬውተርስ፣ እና አልጀዚራ ይገኙበታል።
እንዲሁም የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በጉብኝታቸው ስለታሰሩት ጦማርያን እና ጋዜጠኞች አጠንክረው እንደተናገሩ የኒውዮርክ ታይምሱ ታዋቂ አምደኛ ኒኮላስ ክሪስቶች ለሰጣቸው አስተያዬት፤ “ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው። ዩናይትድስቴትስ በመላው ዓለም ላይ የፕሬስ ነፃነትን በመደገፍና ከጥቃት በመከላከል ባላት ጠንካራ አቋም ትቆያለች” በማለት ምላሽ ሰጥተውታል።
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen