Netsanet: የኢቲቪ “የቀለም አብዮት” ስጋት!

Montag, 14. April 2014

የኢቲቪ “የቀለም አብዮት” ስጋት!

April 13/2014
ኢቲቪ “የቀለም አብዮት” ዝግጅት (ስጋት) አቀረበልን። ግን የኢህአዴጉ ኢቲቪ ለምን የቀለም አብዮት ጉዳይ አጀንዳ አደረገው? የቀለም አብዮት ጉዳይ ለምን ዝግጅት አስፈለገው? አዎ! “የቀለም አብዮት” ጉዳይ አጀንዳ የሆነው የቀለም አብዮት (በትክክለኛው አጠራሩ ህዝባዊ ዓመፅ) ስጋት ስላለ ነው። የህዝብ ዓመፅ (የቀለም አብዮት) ለምን ስጋት ሆነ? ኢህአዴግ ለምን ህዝባዊ ዓመፅን ሰጋ? ተግባሩ ስለሚያውቅ ነው።

የኢህአዴግ መንግስት ዓፋኝ መሆኑ አውቀዋል፣ ተገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ዓፈና እንደማያስፈልገው መገንዘቡም የኢህአዴግ መንግስት የተገነዘበ ይመስለኛል። ህዝብ ስለ ዓፈና ግንዛቤ ካለው ነፃነት መፈለጉ አይቀርም። ነፃነት የፈለገ ህዝብ በማፈን መግዛት እንደማይቻል ኢህአዴጎችም የተገነዘቡት ይመስላል።

አሁን ኢህአዴግ የህዝብ ድጋፍ እንደሌለው እየተረዳ ነው። የኢህአዴግ ዓላማ ስልጣን እስከሆነ ድረስ በህዝብ ባይመረጥም የህዝብን ድምፅ አጭበርብሮ የተመረጠ አስመስሎ በስልጣን ለመቆየት ጥረት ማድረጉ አይቀርም። ነፃነት የፈለገ ጭቁን ህዝብ ድምፁን ለማስከበር ጥረት ሲያደርግ የህዝብ የነፃነት ትግል ከኢህአዴግ የስልጣን ፍላጎት ጋር ይጋጫል። ግጭቱ ህዝባዊ ዓመፅ ሊወልድ ይችላል የሚል ስጋት አድሮበታል። ለዚህም ነው የቀለም አብዮት (ህዝባዊ ዓምፅን) አጀንዳ አድርጎ ዝግጅቱ (ይቅርታ ስጋቱ) ያቀረበልን።

በኢቲቪ ከቀረበልን ዝግጅት በመነሳት ኢትዮጵያ የቀለም አብዮት (ህዝባዊ ዓመፅ) ያሰጋታል። ምክንያቱም የኢህአዴግ መንግስት ህዝባዊ ዓምፅን ባያሰጋው (ባይፈራ) ኑሮ በምስራቅ አውሮፓና ላቲን አሜሪካ ስለተከናወኑ የቀለም አብዮቶች ባላሳሰበው ነበር። ኢቲቪዎች “ምዕራባውያን የራሳቸው ጥቅም ለማሳካት ሲሉ በሌሎች ሀገሮች ህዝባዊ ዓመፅ እንዲቀሰቀስ ያደርጋሉ” አሉን። በዓለም አቀፍ ግኑኝነት ማንኛውም ሀገር የራሱ ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ይሰራል። ምዕራባውያን ይሁኑ ምስራቃውያን የየራሳቸው ጥቅም ለማስከበር ነው የሚሰሩት። ይህ ግልፅ ነው።

ዓቅም ያላቸው ሐያላን ሀገራት በአንድ ሀገር የመንግስት ግልበጣ ሊያካሂዱ ይችላሉ (በገንዘብና በወታደራዊ ሃይል በመታገዝ)። የዉጭ ሃይል መፈንቅለ መንግስት ሊያካሂድ ይችላል። ህዝባዊ ዓመፅ የመቀስቀስ ዕድሉ ግን አነስተኛ ነው። ምክንያቱም ህዝባዊ ዓመፅ የሚካሄደው በሀገርኛ ህዝብ ነው። የዉጭ ሀገር መንግስት ብጥብጥ ወይ ዓመፅ ሊቀሰቅስ ይችላል። ዓመፁ የሚካሄደው ግን በህዝብ ነው። ስለዚህ የህዝባዊ ዓመፅ ዋነኛ ተዋናይ ህዝብ እስከሆነ ድረስ የዉጭ ሃይል ዓመፅ የመቀስቀስ እንጂ ዓመፅ የማካሄድ ዕድል የለውም። ምክንያቱም የዉጭ ሃይል ፍላጎቱ ለማሳካት ዓመፅ ቢቀሰቅስ እንኳ ህዝቡ ቅሬታ ከሌለው፣ ነፃነቱ ከተጠበቀ፣ ካልታፈነ ለዓመፅ አይዘጋጅም። ህዝብ ለዓመፅ ካልተዘጋጀ የዉጭው ሃይል የፈለገ ጥረት ቢያደርግ አይሳካለትም።

በአንድ ሀገር ህዝባዊ ዓመፅ ሊቀሰቀስ የሚችለው በዉጭ ሃይል ፍላጎት ሳይሆን በጭቆና ነው። ህዝብ ሲጨቆን ነፃነት ይፈልጋል። ነፃነት ሲፈልግ ከስልጣን ጥማተኛ አምባገነኖች ጋር ይጋጫል። አምባገነኖች የህዝብን የነፃነት ጥያቄ በሃይል ለመጨፍለቅ ይሞክራሉ። ህዝብ ያምፃል። ህዝባዊ ዓመፅ ይቀሰቀሳል። ስለዚህ የህዝባዊ ዓመፅ መንስኤ ጭቆና ነው። ህዝብ የስልጣን ባለቤት ከሆነ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቱ ከተጠበቀለት፣ በእኩል ዓይን ከታየ፣ ፍትሕ ከሰፈነ ወደ ዓመፅ የሚሄድበት ምክንያት አይኖርም።

ኢህአዴጎች “የቀለም አብዮት” ከምዕራባውያን ብሄራዊ ጥቅም ጋር ያገናኙበት ምክንያት ምናልባት ኢትዮጵያ ዉስጥ ህዝባዊ ዓመፅ ቢቀሰቀስ ‘የኢትዮጵያውያን ቅሬታ የቀሰቀሰው ሳይሆን የምዕራባውያን ሴራ ነው’ በማለት ዓመፁ በሃይል ለመጨፍለቅ እንዲችሉ ሐሳባዊ ቅድመ ዝግጅት ለማስቀመጥ ነው። ግን እስካሁን የተደረጉ ዓመፆች ይሁኑ ጦርነቶች አንድ አምባገነን ስርዓት በሌላ አምባገነን ስርዓት እንዲተካ ምክንያት ሆኑ እንጂ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲገነቡ አላየንም። የዴሞክራሲ መንገድ በቃ ዴሞክራሲ ራሱ ነው።

ኢህአዴጎች ራሳቸው በዓመፅ (በጦርነት) ስልጣን ይዘው ሲያበቁ ስለ ዓመፅ መጥፎነት ይነግሩናል። ዓመፅ መጥፎ መሆኑ ቢያውቁ ለምን በደርግ ግዜ ዓመፅ ቀስቀስው ደርግን በሃይል አባረው ስልጣን ያዙ? ለምንስ አሁን በዓመፅ ስልጣን መያዝ መጥፎ ነው ይሉናል?

አዎ! ‘ደርግ ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር ስላልፈቀደ ነው፣ ጨቋኝ ስለነበረ ነው፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስላለነበረ አማራጭ አጥተን ጫካ ገብተን ከስልጣን አባረነዋል’ ይሉን ይሆናል። ልክ ነው ዓመፅ የሚነሳው በዓመፀኛ ስርዓት ነው። ስርዓት ጨቋኝ ሲሆን በህዝብ ላይ የሚፈፅመውን ግፍ ዓመፅ ይወልዳል። ስለዚህ የዓመፅን መንስኤ ህዝብ ወይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይሆኑ ጨቋኝ ስርዓት ነው።

አሁን ዓመፅን እየቀሰቀሰ ያለው ማነው? ህዝብ? ተቃዋሚዎች ወይስ ገዥው ፓርቲ? ህፃናት እያደራጀ፣ ሰለማዊ ህዝብን እንዲበጠብጡ ከፍሎ እየላከ ያለው ማነው? የህዝቦችን የመሰብሰብ መብት እየነፈገ ያለው ማነው? ሰለማዊ ተቃዋሚዎችን በድንጋይ እየወገረ በሰለማዊ ትግል ተስፋ ቆርጠው የዓመፅ መንገድ እንዲከተሉ እያስገደደ ያለው ማነው? ዓመፅን የሚፈጥረው ገዥው መደብ ነው።

በኢትዮጵያ ህዝባዊ ዓመፅ ከተነሳ መንስኤው የኢህአዴግ ጭቆና ነው። በኢትዮጵያ ህዝባዊ ዓመፅ እንዳይኖር ለማድረግ ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር በማድረግ ጭቆናን እናስወግዳለን። ከጎጂነቱ አንፃር ህዝባዊ ዓመፅን መከላከል የምንችለው ስለ ህዝባዊ ዓመፅ መጥፎነት በቲቪ በማቅረብ ሳይሆን ስልጣን የህዝብ በማድረግ ነው። ህዝብ የሚያምፀው የህዝብን ልአላዊነት ለማስከበር ነው። የህዝብን የበላይነት ለማረጋገጥ ነው። ስለዚህ ህዝባዊ ዓመፅን የምናስቀረው ስልጣን የህዝብ በማድረግ እንጂ ህዝቦችን በመጨቆን አይደለም። የህዝብን ነፃነት በማፈን ህዝባዊ ዓመፅን መከላከል አይቻልም።
አዎ! ዓላማችን ህዝባዊ ዓመፅን ማስቀረት ነው፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገንባት።

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/29087

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen