Netsanet: በማንነት ጥያቄ የተወጠረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሽናል እግር ኳሰኛ ቤተሰቦቹን ማግኘት ይሻል

Freitag, 25. April 2014

በማንነት ጥያቄ የተወጠረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሽናል እግር ኳሰኛ ቤተሰቦቹን ማግኘት ይሻል

April 24/2014
ምንጭ  Ethiotube.net 
ይሁን በሕፃናት ማሳደጊያ በነበረበት ወቅት

በሙሉ ስሙ ሲሞን ይሁን ስቶለን ማርኬንግ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በኖርዌይ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ትራኤፍ ለሚባል ክለብ በአጥቂነት በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ በ2009 በወጣት ቡድን ደረጃ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ሕይወትን አሀዱ ብሎ ወደጀመረበት ትራኤፍ ክለብ ተመልሶ በመጫወት ላይ የሚገኘው ይሁን በኖርዌይ ፕሪምየር ሊግ (ቲፐሊጋ) ላይ በሚወዳደረው ሞልደ ክለብ ውስጥም ለአስር ወር የቆየበትን ዕድል አግኝቶ ነበር፡፡ ሞልደ በቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ድንቅ አጥቂ እና በአሁኑ የካርዲፍ ሲቲ አሰልጣኝ ኦሌጉናር ሶልሻየር እየተመራ የቲፐሊጋው ሻምፒዮን መሆን የቻለ ትልቅ ክለብ ነው፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ወጣት በ2010 በሞልደ እያለ ለኖርዌይ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ከጀርመን ጋር በተደረገ አንድ ጨዋታ ላይ መሰለፍ ችሏል፡፡ ሶልሻየር ክለቡን ከያዘ ከጥቂት ግዜ በኋላ በውሰት በወቅቱ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ይወዳደር ለነበረው (በዓመቱ መጨረሻ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን አድጓል) ክርስቲያንሱንድ ክለብ በውሰት የተሰጠ ሲሆን ክለቡ ወደአንደኛ ዲቪዚዮን ካደገ በኋላም በቋሚነት አስፈርሞታል፡፡
በ2013 የውድድር ዓመት በክርስቲያንሱንድ ክለብ ውስጥ በአብዛኛው ተጠባባቂ ሆኖ መጀመሩ ያላስደሰተው ይሁን ዘንድሮ በብዙ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ ዕድል ለማግኘት ሲል በሁለተኛ ዲቪዚዮን ወደሚወዳደረው የመጀመሪያ ክለቡ ትራኤፍ ተመልሷል፡፡ ይሁን የሚጫወትበት የኖርዌይ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የ2014 የውድድር ዓመት ባለፈው ሰኞ የተጀመረ ሲሆን ክለቡ ትራኤፍ ከሜዳው ውጭ ከሮዘንበርግ 2 ጋር ባደረገው ጨዋታም 1-1 በመለያየት ዓመቱን ጀምሯል፡፡ በሞልደ እያለ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ሲሳተፍ ለነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጫወት ፍላጎቱን በወኪሉ በኩል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቅርቦ እንደነበረ የጠቀሰው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ተጫዋች ከፌዴሬሽኑ ጋር የነበረው ግንኙነት በመሀል በመቋረጡ ፍላጎቱን እውን ማድረግ አለመቻሉንም አሳውቋል፡፡ ‹‹ወደኖርዌይ ያቀናሁት እ.አ.አ በ1995 (ከዛሬ 19 ዓመት በፊት) ገና የሁለት ዓመት ልጅ እያለሁ አምባ ከሚባል ሕፃናት ማሳደጊያ በጉዲፈቻ ተሰጥቼ ነበር›› የሚለው ይሁን በአሁኑ ሰዓት በአዕምሮው ውስጥ ለሚመላለሰው የማንነት ጥያቄ ምላሽ የማግኘት ፍላጎቱ ከፍተኛ እንደሆነ እና የዘንድሮው የውድድር ዓመት ሲጠናቀቅም ለዚሁ ጉዳይ ወደኢትዮጵያ የመምጣት ዕቅድ እንዳለው ለEthiotube.net በሰጠው አስተያየት ገልጿል፡፡
‹‹በ1995 ዓ.ም (በኢትዮጵያ 1987) ወደኖርዌይ ከመጣሁ ወዲህ ወደኢትዮጵያ ተመልሼ አላውቅም፡፡ ያን ግዜ ገና የሁለት ዓመት ልጅ ስለነበርኩም ምንም አይነት መረጃ አልነበረኝም፡፡ ትክክለኛ መረጃ ወይም ሰዎች ዝም ብለው የፃፉት መሆኑን ባለውቅም የልደት ሰርተፊኬቴ ላይ የትውልድ ከተማ ጅማ ይላል፡፡ ሰዎች ተመልክተውት እንዲያስታውሱኝ ቢረዳኝ ብዬ በሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ሳለሁ የተነሳኋቸውን ፎቶዎች ይዣለሁ፡፡ ቤተሰቦቼን ፈልጌ ለማግኘት ያለኝ ተስፋ ዝቅተኛ ቢሆንም ፍለጋውን አድርጌ ቁርጤን እስካላወቅኩ ድረስ አዕምሮዬ እረፍት አያገኝም፡፡ ፎቶዬን ተመልክቶ የሚያስታውሰኝ ሰው ቢገኝ ጥሩ እገዛን ያደርግልኛል›› ያለው ይሁን በጉዲፈቻ ስለተሰጠበት ሁኔታ ሲገልፅም ‹‹ለኖርዌያውያኑ አሳዳጊዎቼ ልሰጥ ስል ሜይ 25/1995 (ግንቦት 17/1987 ዓ.ም) በፎርም ቁጥር 75 አዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ተቃዋሚ ካለ የሚል ማስታወቂያ ወጥቶ የነበረ ቢሆንም ተቃዋሚ ሆኖ የቀረበ ሰው አልነበረም፡፡ የዛን ግዜ ይጠሩኝ ነበረው ይሁን ብለው ነው፡፡ ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ የቆየሁት ለስድስት ወር ብቻ የነበረ መሆኑ ከዛ በፊት ቤተሰብ እንደነበረኝ የሚጠቁም ነው፡፡ ስያሜው እስካሁን ድረስ ተመሳሳይ ስለመሆኑ እርግጠኛ ባልሆንም የነበርኩበት ማሳደጊያ ካልተሳሳትኩ ‹አምባ› የሚባል እና በፎቶው ላይ አቅፋኝ የምትታየው አሰፋሽ የምትባል ሰው የምታስተዳድረው ነበር›› ብሏል፡፡ ይሁን ስለኋላ ታሪኩ የሚያውቀው ካደገ በኋላ ጠይቆ የተረዳቸውን ጥቂት ነገሮች ብቻ መሆኑ ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቹን የማግኘት ዕድሉን የጠበበ እንደሚያደርግበት ቢያስብም ‹‹እግዚአብሔር ከፈቀደ የማይሆን ነገር የለም›› ብሎም ያምናል፡፡ ዘንድሮ በዝቅተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ ቢጫወትም በብዙ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ ዕድልን በማግኘት ብዙ ጎሎችን ማስቆጠርን እና ወደተሻለ የብቃት ደረጃ መሸጋገርን የሚያልም ሲሆን በዓመቱ መጨረሻም ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቹን የማግኘት ፍላጎቱ እንዲሳካለት በትንሹ ተስፋ ያደርጋል፡፡

* ከዚህ ዜና ጋር የተያያዙትን የልጅነት ፎቶዎቹን ተመልክታችሁ የምታስታውሱትና መረጃ ልትሰጡት የምትፈልጉ ካላችሁ በሞባይል ቁጥር 0920550862 ደውላችሁ ልትተባበሩት ትችላላችሁ፡፡

ይሁን በሕፃናት ማሳደጊያ በነበረበት ወቅት
ይሁን በሕፃናት ማሳደጊያ በነበረበት ወቅት
የሲሞን ይሁን ማርኬንግ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ፎቶዎች
የሲሞን ይሁን ማርኬንግ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ፎቶዎች
ተጫዋቹ ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በፊት ሐምሌ 15/2004 ለወጣው የኢንተር ስፖርት ጋዜጣ የሰጠው ቃለ ምልልስ
* ከዚህ ዜና ጋር የተያያዙትን የልጅነት ፎቶዎቹን ተመልክታችሁ የምታስታውሱትና መረጃ ልትሰጡት የምትፈልጉ ካላችሁ በሞባይል ቁጥር 0920550862 ደውላችሁ ልትተባበሩት ትችላላችሁ፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen