APRIL 20, 2014
‹‹የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ ለደላላ አበል መከፈል የለበትም›› ወ/ሮ መና ግርማ፣ የቀድሞው የፕሬዚዳንት ልጅ
ከመኖሪያ ቤት ኪራይ ጋር በተገናኘ የ360 ሺሕ ብር የኮሚሽን ክፍያ ክስ የተመሠረተባቸው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ክስ ክርክር ሊደረግ ነው፡፡
ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. የሚደረገው የፍትሐ ብሔር ክርክር ከሳሽ ከሆኑት የኮሚሽን ሠራተኛው አቶ አንተነህ አሰፋ ጋር ሲሆን፣ ምክንያቱም ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ቤት ከነሙሉ ዕቃው ደልለው በማከራየታቸው ነው፡፡
የኮሚሽን ሠራተኛው አቶ አንተነህ ለፕሬዚዳንቱ ቤት እንዲያፈላልጉና ለቤቱ ኪራይ ከሚከፈለው የገንዘብ መጠን ላይ አሥር በመቶ እንደሚከፈላቸው ውል የተፈራረሙት፣ ከአቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ልጅ ወ/ሮ መና ግርማ ጋር በመሆኑ ነው፡፡ አቶ አንተነህ ለመሠረቱት የፍትሐ ብሔር ክስ ወ/ሮ መና በጠበቃቸው በአቶ አዳሙ ሽፈራው በኩል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጠበቃው አቶ አዳሙ ወ/ሮ መናን በመወከል ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ፣ ‹‹የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ ለደላላ አበል መከፈል የለበትም፣ የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ የግለሰብ ማበልፀጊያ እንዲሆን ግማሽ ሰዓት ላልፈጀ ሥራ ሊከፈል አይገባም፤›› በማለት ክሱን ተቃውመዋል፡፡
ከሳሽ አቶ አንተነህም በጠበቃቸው አቶ ወርቅዬ ዓባይነህ አማካይነት ባቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ፣ ክስ የመሠረቱት በፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ላይ፣ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ በወ/ሮ አማረች በካሎ (የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ)፣ በወ/ሮ አምሳለ ፋንታሁንና በልጃቸው በወ/ሮ መና ግርማ ላይ መሆኑን ክሳቸው ያሳያል፡፡ በመሆኑም ከሳሽ ከወ/ሮ መና ጋር ጳጉሜን 3 ቀን 2005 ዓ.ም. በተጻፈ የኮሚሽን ውል መሠረት፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 16 የቤት ቁጥር 658 ባለሁት ፎቅ ቤት ከነሙሉ ዕቃው ጋር በ400 ሺሕ ብር እንዲከራዩ በመስማማታቸው፣ የዘጠኝ ወራት የቤት ኪራይ 3.6 ሚሊዮን ብር ከአከራዩ አቶ ሰለሞን ግርማ ገብሩ ጋር በማፈራረም እንዲከፈላቸው ማድረጋቸውን በክሳቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ አንተነህ በውላቸው መሠረት የኮሚሽን አበል 360 ሺሕ ብር ሲጠይቁ ሊከፈላቸው ባለመቻሉና ማንን እንደሚጠይቁ ግራ መጋባታቸውን ገልጸው፣ ከፋዩ ተለይቶ እንዲወሰንላቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 36/5/ መሠረት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ተከሳሽም ከመስከረም 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከሚታሰብ ዘጠኝ በመቶ ወለድ ጋር እንዲከፈላቸው እንዲወሰንላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. የቃል ክርክር ከማድረጋቸው በፊት ወ/ሮ መና ባቀረቡት መቃወሚያ፣ ውሉ ፀንቶ ከሚቆይበት ጊዜ አንስቶ አምስት የሥራ ቀናት ብቻ በመሆኑና የተፈረመው ውል ጳጉሜን 3 ቀን 2005 ዓ.ም. በመሆኑ እሳቸውን እንደማይመለከታቸው ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ መና ውሉን የፈጸሙት የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ባዘዛቸው መሠረት መሆኑን ጠቁመው፣ ውሉ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2189 መሠረት ግዴታ እንደማይሸከሙ አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው የፕሬዚዳንቱን ጽሕፈት ቤት በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 244 (2) (መ) መሠረት እንደማያገባቸው አስረድተው፣ በማያገባቸው ክስ ተካፋይ መሆን ስለሌለባቸው ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል፡፡
የወ/ሮ መና ጠበቃ አቶ አዳሙ ሽፈራው ዝርዝር መከራከሪያ የሕግ አንቀጾችን በመጥቀስ ለፍርድ ቤቱ መቃወሚያቸውን አቅርበው፣ ፍርድ ቤቱ ክርክራቸውን የሚያልፈው ከሆነ ከሳሽ የሙያ ኮሚሽን ሊከፍላቸው የሚገባው ከቤቱ ኪራይ ላይ እንጂ ከዕቃው አለመሆኑን፣ የቤቱን ኪራይ ያጋነነው የቤቱ ዕቃ ተደምሮ በመሆኑ የቤቱ ወርኃዊ ክፍያ በገለልተኛ ወገን መገመት እንዳለበት ተከራክረዋል፡፡ ውል ሲፈራረሙ የቤቱ ኪራይ ዋጋ መጠን ባለመገለጹ ከምን ያህል ወራት ላይ ኮሚሽን እንደሚከፈል አልተጠቀሰም፡፡ የ360 ሺሕ ብር ክፍያ እንዲከፈላቸው መነሻ የሚሆን ድንጋጌ በውሉ ስለሌለ ሊከፍሉ እንደማይችሉ በመቃወሚያቸው አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የመንግሥት አካል የሆነውን የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት የተጋነነውን የደላላ አበል ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ ለማንኛውም ሰው ትምህርት በሚሰጥ ሁኔታ የተከሳሽ ወጪና ኪሳራ መብት እንዲወሰን ጠበቃ አዳሙ ወ/ሮ መናን ወክለው መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡
Source: Ethiopian Reporter
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen