Netsanet: ድምፃዊ ጐሳዬ ተስፋዬ መገናኛ ብዙሃንን እከሳለሁ አለ “ሃይማኖቴን አልቀየርኩም” ብሏል

Montag, 21. April 2014

ድምፃዊ ጐሳዬ ተስፋዬ መገናኛ ብዙሃንን እከሳለሁ አለ “ሃይማኖቴን አልቀየርኩም” ብሏል

April 20/2014
ድምፃዊ ጎሳዬ “ሃይማኖቱን ቀየረ” በሚል በመገናኛ ብዙሃንና በድረ-ገፆች የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑን ገልፆ መገናኛ ብዙሃኑ ስህተታቸውን ካላስተባበሉ ክስ እንደሚመሰርት በጠበቃው በኩል ለአዲስ አድማስ ገለፀ፡፡

ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ “ሃይማኖቱን ቀይሮ ሙዚቃ በቃኝ በማለት መዝሙር ሊያወጣ ነው” በሚል በዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮና በ “ቃልኪዳን” መጽሔት የተሰራጨው ሃሰተኛ ዘገባ  የድምፃዊውን ስምና ዝና የሚያጠፋ ነው ያሉት ጠበቃው አቶ ጳውሎስ ተሰማ፤ የሚዲያ ተቋማቱ በአስቸኳይ ማስተባበያ እንዲያወጡ ጠይቀው፤ ይህ ካልሆነ ግን ክስ እንደሚመሰረትባቸው አሳስበዋል፡፡

ድምፃዊው ሃይማኖቱን በተመለከተ ለማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን የሰጠው አስተያየትም ሆነ ቃለ ምልልስ የለም ያሉት የአርቲስት ጐሳዬ ጠበቃ፤ የቀረበው ዘገባ የድምፃዊውን አድናቂዎችና የሙዚቃ አፍቃሪዎቹን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳሳነና ያስደነገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡



በዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ “በዳጊ ምልከታ” በተሰኘ ፕሮግራም፤ ድምፃዊው “ሃይማኖቱን ቀይሮ የመዝሙር ነጠላ ዜማ ሊለቅ ነው፤ ከአርቲስት መሐሙድ አህመድ ጋር በለቀቁት ነጠላ ዜማ የገባውን ቃል አልጠበቀም” የሚል የተሳሳተ ዘገባ መሠራጨቱን ጠበቃው ገልፀዋል፡፡

በሚያዚያ 4/2006 ለንባብ በበቃው “ቃልኪዳን” መጽሔት ላይም “ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ ዘፈን አቁሞ ዘማሪ ሆነ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ “አሁን ዳግመኛ ተወልጃለሁ፤ ጌታ ለዚች ቀን ስለመረጠኝ ክብርና ምስጋና ለናዝሬቱ ኢየሱስ ይገባዋል፤” ብሎ መናገሩንና ሙዚቃ በቃኝ ብሎ ማቆሙን ከፎቶግራፉ ጋር መውጣቱን ጠበቃው ተናግረዋል፡፡

የቀረቡት ዘገባዎች ሃሰተኛ ስለሆኑ መጽሄቱም ሆነ ዛሚ ኤፍ ኤም ሬድዮ ድምፃዊውን እንዲሁም አንባቢና አድማጩን ይቅርታ በመጠየቅ እንዲያስተባብሉ አሳስበዋል፡፡ መገናኛ ብዙሃኑ ይህን የማያደርጉ ከሆነ ግን ክስ በመመስረት የጉዳት ካሳ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡

“ሃይማኖቱን ቀየረ” የሚለው ወሬ በፈረንጆች ኤፕሪል መጀመሪያ ላይ በፌስ ቡክ እንደተሰራጨ የገለፀው ድምፃዊ ጎሳዬ፤ ትንሽ ቆይቶ እዚያው ፌስ ቡክ ላይ “ኤፕሪል ዘ ፉል ነው” የሚል ነገር እንደወጣ ይናገራል፡፡ ሃሰተኛ የፈጠራ ወሬ መሰራጨቱ ለጊዜው እንዳናደደው የገለፀው ጎሳዬ፤ ወዲያው ግን ለወሬ ጊዜና ቦታ አልሰጥም ብሎ ስራው ላይ ማተኮሩን ተናግሯል፡፡


ከአንጋፋው ድምፃዊ መሃሙድ አህመድ ጋር ባወጡት ነጠላ አልበም የገባውን ቃል አልጠበቀም በሚል የተሰራጨው ወሬ የተሳሳተ ነው ያለው ጎሳዬ፤ አዲስ አልበም ለማውጣት ቀን ከሌት እየሰራ መሆኑንና ቃሉን እንዳላጠፈ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ በቅርቡም ከአዲሱ አልበም ነጠላ ዜማ እንደሚለቅ ጠቁሞ፣ ለክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ መልካም የትንሳኤ በዓል ተመኝቷል- ድምፃዊው፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen