April 20, 2014
ዳዊት ዳባ
በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ተቃውሞ ለማድረግ ሲያስቡ ህጉ ማሳወቅ ቢልም አሳውቀናል ብቻ ብለው ለመቀጠል ያለው ተጽኖ ቀላል አይደለም። ሆን ብሎ ወደ ግጭት [confrontation] የሚገፋቸውን አገዛዝ መብለጥ አለባቸው። ስለዚህም ለማስፈቀድ የሚያልፉበት ውጣ ውረድና ዝቅ ማለት ይኖራል። ባሰቡት ቦታና ጊዜ ተቃውሟቸውን ማሰማቱ ደግሞ ሌላ ሆን ብሎ ባገዛዙ የሚቀናበር ጋሬጣ ማለፍን ይሻል።ስለተቃውሞው ህዝብን ማሳወቁም እንዲሁ።
በዚህ አፈና ውስጥ ሲንቀሳቀሱ አንዳንዴ በውሳኔ አለመፅናት፤ መላዘብ፤ አልፎ አልፎም ተሸንፎ ለጊዜውም ቢሆን መተው፤ ለህግ መከበር ደንታ የሌለው ስረአት መሆኑ ግልጽ ሆኖ እያለ ጥንቃቄ በበዛበትና በህግ አግባብ ለመንቀሳቀስ መሞከራቸውና በሌሎችም የዚህ አይነት እውነቶች ላይ ተነተርሶ በተወሰኑ ዜጎችና ድርጅቶች ዘንድ ጥረታቸው ጥያቄ የሚያስነሳባቸውና የሚያስወቅሳቸው ሆኗል።
አስፈቅዶ በሚደረግ ተቃውሞ ነጻነት አይመጣም ከሚል ጀምሮ ተቃወማችሁ ከዛስ?። እሱ በፈቀደው ቦታና ጊዜ የሚደረግ ተቃውሞ ምን የሚሉት ተቃውሞ ነው። የናንተን የመጀመርያ እቅድና ምርጫ ባስለወጣችሁ ቁጥር ይህ ሁኔታ የህዝብን አመኔታና የመታገል መንፈስ አይሸረሽረ ነው። የሚመስሉሉ ጥያቄዎች እና ወቀሳዎች እንዲነሱ አድርጓል።
ጭራቅ የሆነ ጭካኔ ካለው ባላንጣ ጋር አስፈሪና አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚያደርጉት የትኛውም አይነት ትግልና ጥረታቸው ቀላል በማይባል ዜጎች እና የነሱ አይነት ሌሎች ድርጅቶችን አላረካም። ሊመልሱት የሚከብድ ጥያቄ ሲያስነሳባቸው ብዙ ጊዜ ይደመጣል። ማሸማቀቅና መንጓጠጥም አለ። ወቀሳው ጭራሽ ማስተዋል በጎደለው ሁኔታ ይቀርባል። ግጭት ያለበትን ሌላኛውን አማራጭ ሳያዩትና የሚገኘውን የመጨረሻ ውጤት ሳያሰሉት ተደርጎ ተወስዷል። ከእውቀት ማነስ ያለዚያም ቅጥ ከሌለው ፍራቻ {ለዛውም ለነሱ ብቻ በሆነ} ምክንያት አድርጎ ማቅረብም ይታያል። ተወስዷልም። በእርግጥ በዚህ ፅሁፍ ወደዚህ ጉዳይ ውስጥ መስመጥ አልፈልግም። ያም ሆኖ ይህ ሁኔታ ለዜጎችም ቢሆን አንዱ እጅግ የበዛ መሰዋትነት እየከፈለ ሲታገል ሌሎቻችን ጠያቂና ወቃሽ ለመሆን የሚያስችለን የትኛው ምክንያት ይሆን?። ሞራላዊስ ነው ወይ?። በድርጅቶች ሲሆን ደግሞ በተጨማሪ የናንተ ድርጅት የኪነት ነው?። ወይስ ታክስ ልትሰሩ ነው የተደራጃችሁት የሚል ጥያቄ ባንጻራዊ ማስነሳቱ አልቀረም።
ታዲያ ምን ይሻላል?።
በኛ አገር ሰላማዊና በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችም ቢሆን የሚደርጓቸው የትኞቹም እንቅስቃሴዎች መሰዋትነትና ስጋት በሌለበት የሚያካሂዷቸው አይደሉም። የበዛ መሰዋትነት የሚያስከፍል ጥርት ያለ ጥቁር ትግል ነው እየተካሄደ ያለው። መሞት፤ መታሰር፤ ስራን ማጣት፤ኪስን ማራቆት ይባስ ብሎም ከራስ አልፎ ቤተሰብንና የሚቀርቧቸውን በሙሉ የከፋ መስዋትነት እየከፈሉበት ነው። ሲጀመር ፈቅደው ከዛም በላይ ተደስተው የሚያካሂዱት ነው። በርምጃቸው፤ በውስኔያቸውና ከሚያደርጉት የበዛ ጥንቃቄ ግን ከራስ በላይ ለሌሎች መጨነቃቸውን ነው ከፍት ልብ ላለው የሚታየው።
በኛ ጊዜና የቦታ ምርጫ የመረጥነውን ሰላማዊ የትግል አይነት ማድረጉ ለማሸነፍ የግድ ልናደርገው የሚገባ ነው። ጥሪ የሚያደርገውም ሆነ የሚመራው ግን ውጪ ባሉ ድርጅቶች ወይ አመራሩ የትም ይኑር የማይታወቅና ሊያዝ የማይችል ቢሆን አይሻልም ወይ?። አገር ውስጥ ያሉት ሊጠሩት ይችላሉ። እንደምናውቀው በግላጭ ያሉ የሚታወቁ ናቸው።ይህን ሲያደርጉ ይመቻቹለትና በሚቀጥለው ቀን ሰብስቦ ያጉራቸዋል። ይህ ሲሆን ችግርም አሳዛኝም የሚሆነው የነዚህ ዜጎች መሰዋት መሆን ብቻ ግን አይደለም። መሪ ሰለማይኖር ትግሉ አይቀጥልም። የዚህ አይነቱ ሀሳቡ መነሻ መሰረት ”መሰዋት የሚሆን መሪ ያስፈልገናል” ከሚለው ነው። ይህን አባባል በጣም ብዙ ጊዜ፤ ከብዙ ቦታ፤ ከብዙ አዋቂዎች ሰምተንዋላ። ከመደጋገሙ ብዛት መሪ የሚያስፈልገን እንዲመራን ሳይሆን መሰዋት ልናደረገው እስኪመስል። ወይ ትግሉን በማስቀጠልና ደም መመለሱም ላይ ሆነ ማስፈታቱ ላይ ደግሞ የተጨበጨበልን አይደለንም። ካዘሬ አስር አመት በፊት ጊዜው ደግሞ እንዴት ይሄዳል እባካችሁ!። ያንን አይነት የህዝብ ለለውጥ ቆርጦ መነሳትና መሰዋትነቱ ለመክሸፉ አሁን ላይ በተገኘው አጋጣሚ ሀላፊነቱን ሁሉ የምንለድፍባቸው መሪዎች ተሰብስበው ሲታሰሩ የበሰለ ትግል ተቀብሎ ወደድል የሚመራን አልነበረም። ከአስር አመት በሗላስ ዛሬስ?።
ይህን ትግል አሸናፊ ለማድረግ እሰከድል አስተውሎትና ጥንቃቄ ባለበት የሚመራን መሪና መሪዎቹ ላይ አመኔታ አድርገው ለመመራት የፈቀዱ ብዙ ዜጎችን ይፈልጋል። የአረቡ አቢዬት ከሰላማዊና ከሀይሉ አማራጭ ውጪ ሶስተኛ አማራጭ እንዳለ ያሳየን ነበር። ባለው ነባራዊ የአገራችን እውነታ ህዝባዊ እንቢተኛነት በኛም አገር እንደሚሰራ ደግሞ ከሙስሊም ወገኖቻችን ትግል ታላቅ ተሞክሮ እየወሰድንበት ነው።
የስልምና እምነት ተከታይ ወገኖቻችን መንግስት አድርጉም ሆነ አታድርጉ ለሚለው ደንታ መስጠቱን አቁመዋል። በሌላ በኩል ግን መሪዎቻቸው አድርጉ ያሏቸውን ያደርጋሉ። አታድርጉ ያሏቸውን ደግሞ አያደርጉም። ወናው ጉዳይ who is in control now or in charge now? የሚለው ነው:: እውነታው ላገዛዙ ቤተመንግስቱን ትተውለት አመራሩን በከፊል ተረክበውታል።
አሁን መሪዎቻቸው እንዳይያዙ ሆነው ስላለ ወያኔ ህዝብን በገፍ ሲገድል ሆነ ሲያስር ቢከርም ከዚህ በሗላ ትግሉ የበለጠ ጉለበት እያገኘ እየረቀቀ ይቀጥላል እንጂ ወይ ፍንክች። ቱ ብሎ ምሎ መናገር ይቻላል። ቆያይቶ ጥያቄዎቻችሁን ልመልስ ብሎ ይለምናል። መሪዎቻቸውንም ፈትቶ ሊደራደር ይሞክራል። ማወቅ ያለብን ካገዛዙ የተቀበሉት አመራሩን ብቻ አይደለም። የተሻለ ላገርና ለህዝብ ደህንነት አሳቢም ሆነው ነው የወጡት። ሊያጫርስ ሲያስብ አስማሚ ሆነዋል። ሽብርተኛ ናቸው ሲል ፍጽም ሰላማዊ መሆናቸው ማሳየት ላይ መቼ ተገትተው። አሸባሪነቱ የሱና የባህሪው መሆኑን አጋልጠውበታል። የሚታገሉት ጥያቄዎቻቸውን ለማስመለስ እንጂ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ተከታዬቻቸውን ለመክተት ስላልሆን አገዛዙ ሲበሳጭ፤ ደሙ ሲንተከተክና ለመግደል ሲያቆበቅብ ትግሉን ያስቆሙና አልመች ይሉታል። ጊዜ ወስደው በነሱ የጊዜ ቀመርና ምርጫ ደግሞ አደባባዩን ፍጽም ሰላማዊ በሆነ ተቃውሞ ይሞሉታል። አድሏዊ በሆነ ዘረኛ አንባገነን ተቀጥቅጦ እንደሚኖር ህዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከምእራብ ዜጎች በሙሉ ይህን አይነቱን ጫወታ መጫወት የቻልን ጊዜ ያኔ ነጻነታችን እውን ሆነ ማለት ነው። እኛ ባንድ ሆነን ያደረግነው ጊዜ ሲገቡ እንደነበረው ቤተ መንግስት ውስጥ ጋቢ ለብሰው ኩርምት ብለው ቁጭ ብለው መረጃ እያነደዱ ሲሞቁ ሳሏቸው።
መሪ አስከድል መምራት እንጂ መሰዋት መሆን የሌለበት ትግሉን ለማስቀጠልና አሸናፊ ለመሆን ሲባል ብቻ ነው። ስለመሰዋትነቱ ከሆነ እንኳን በስልጣናቸው ተመጥቶ ሰዎቻችን መግደልና ማንገላታቱ እንደው ላመላቸው ነው። ተመልከቷቸው። ሰሞኑን ደግሞ አዙራቸዋል። በአሉ ነው መሰል። ዶሮ ወይ በሬ አይደለም እኮ የሚታያቸው። ሰበብ ሲያጡ ሆን ብለው የወገኖቻችንን ቤት አፈርሰው እና አቃጥለው ሲያጉረመርም ሸክ ነው። የዚህ አይነቱ ሁኔታ መግደልና ማሰቃየት እንዳይችሉ እስክናደርጋቸው አይቆሙም። ትግሉ የሚጠይቀውን የትኛውንም አይነት መሰዋትነት ከፍሎ ነጻነትን የመቀዳጀት አስፈላጊነት ላይ ብዥታ በጭራሽ የለም ለማለት ነው።
አገር ውስጥ ያሉ ሰላማዊ ታጋዬች እንደመጥምቁ ዮህንስ ፍትህ እኩልነትና የነጻነት ዘመን መቅረቡንና እንደሚገባን የማብሰሩን ስራ ላይ እንደጀመሩ ይቀጥሉ። ጥሩም ይዘዋል። ህዝባዊ እንቢታውን የመምራቱን ስራ በስተማማኝ ደህንነት ላይ ያሉ ይውሰዱ። ይህን ያደርጉ ዘንድ ህብረቱን ማስተዋሉን ብለሀቱንና እውቀቱን ይስጥልን።
Saturday, April 19, 2014
dawitdaba@yahoo.com
dawitdaba@yahoo.com
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen