Netsanet: ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ "የኢህአዴግ ደጋፊም አባልም መሆን የምቸገረው ኢህአዴግ የሚያራምደው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለግለሰብ ነፃነት የሚሰጠው ቦታ ስለሌለ ወይም የይስሙላ ስለሆነ ነው፡፡ አሁንም አቋማችን መሆን ያለበት የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ የዜጎችን ነፃነት ቀምቶ የሚመጣ ከሆነ ባአፍንጫችን ይውጣ የሚል መሆን አለበት፡፡" ይሉናል።

Dienstag, 22. April 2014

ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ "የኢህአዴግ ደጋፊም አባልም መሆን የምቸገረው ኢህአዴግ የሚያራምደው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለግለሰብ ነፃነት የሚሰጠው ቦታ ስለሌለ ወይም የይስሙላ ስለሆነ ነው፡፡ አሁንም አቋማችን መሆን ያለበት የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ የዜጎችን ነፃነት ቀምቶ የሚመጣ ከሆነ ባአፍንጫችን ይውጣ የሚል መሆን አለበት፡፡" ይሉናል።

April 22/2014
ነፃነት የጎደለው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 
ግርማ ሠይፉ ማሩ 
girmaseifu32@yahoo.com 
 
የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን በዝርዝር ተመልክቶ የገመገመ ተቃዋሚ ፓርቲ ከአንድነት በስተቀር ያለ 
አይመስለኝም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የዕቅዱን ግምገማ ውጤት ለህዝብ ለማድረስ ባለመቻሉ ግን ይህ የሚታወቅ 
ነገር አይደለም፡፡ ግምገማው የተከናወነው የተለያዩ ዘርፎችን ለሙያው ቅርበት ባላቸው ሰዎች በሚመሩት ሁኔታ 
ነው የተገመገመው፡፡ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን አንድ ክፍል ለመገምገም ሃላፊነት ከወሰዱት ሰዎች 
ውስጥ/አሁን ስም መጥቀስ አያስፈልግም/ ኢህአዴግ ይህን ዕቅድ ካሳካ ኢህአዴግ እሆናለሁ ማለታቸውን 
አሰታውሳለሁ፡፡ እኔ በግሌ ዕቅዱን እንደማያሳካ ሰጋቴን ባስቀምጥም እቅዱን ቢያሳኩትም ኢህአዴግ እንደማልሆን 
አውቃለሁ፡፡ እነዚህ ቁሳዊ ነገሮች የበዙበት ዕቅድ ነፃነቴን ለመውሰድ የተዘጋጀ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ የኢህአዴግ 
ደጋፊም አባልም መሆን የምቸገረው ኢህአዴግ የሚያራምደው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለግለሰብ ነፃነት የሚሰጠው ቦታ ስለሌለ ወይም የይስሙላ ስለሆነ ነው፡፡ አሁንም አቋማችን መሆን ያለበት የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ የዜጎችን ነፃነት ቀምቶ የሚመጣ ከሆነ ባአፍንጫችን ይውጣ የሚል መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በተቃራኒው የሚቆም መብቱ ነው፡፡ በህዳሴው ግድብ ከሚገኝ መብራት ኢትቪን እየተመለከተ ነፃነቱን በእልሙ ማየት ይችላል፡፡ ወይም በህዳሴው ግድብ መነሻ በሚፈጠር ማነኛም የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆኖ ነፃነት ድሮ ቀረ ብሎ የሌሎች ሀገር ዲሞክራሲን ማወደስ ሲሻው መሳደብ መብቱ ነው፡፡ ነፃነት በነፃ አይገኝም ብቻ ሳይሆን ነፃነትን ለፈለጉት ቁሳዊ ጥቅም አሳልፎ መሸጥ የግለሰቦች ምርጫ ነው፡፡ ነፃነት የሚገኘው በ “ምርጫ” ነው፡፡ ነፃ ለመሆን በመፈለግና ለዚህ ፍላጎት የሚከፈለውን ዋጋ በመክፈል የሚገኝ ነው፡፡ 
 
እኛና ኢህአዴጎች የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅዱን በዕቅዱ ዘመን መጨረሻ ሰንገመግም እንዲሁም አቋም ስንይዝ በብርጭቆ ውስጥ እንደሚገኝ ውሃ “ግምሻ ሙሉ እና ግማሽ ጎዶሎ” በሚል ፍልስፍና መነፅር ኢህዴጎች ግማሽ ሙሉ እኛ ግማሽ ጎዶሎ እንደመረጥን ተደርጎ ቢወሰድ ልክም ተገቢም አይደለም፡፡ ኢህዴጎች ከአሁኑ እንደማይሆንላቸው ስላወቁ በዕቅድ ዘመኑ ከተቀመጡት “ወሳኝ ቁሳዊ ግቦች” ቢሆን ፈቀቅ ብለው፤ አሁን የደረሱበትን እና ወደፊት ያለውን “ተስፋ” በመመገብ ለቀጣይ ምርጫ እንደ ዋናኛ የምርጫ ግብዓት እየተዘጋጁ ነው፡፡ በቀጣይ ዓመት በዕቅድ የተቀመጡትን ግቦች ከማሳካት ይልቅ በዋነኝነት በፕሮፓጋንዳው ስለሚጠመዱ አሁን ከደረሱበት ብዙ ፈቀቅ እንደማይሉ ለመገመት አያስቸግርም፡፡ 
 
የኢህአዴግ ሰዎች በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በእያንዳንዱ ዘርፍ የተጣለው ግብ በዋና ዋናዎቹ ግማሽ ለመደረስ እንደማይቻል አመላካች ነገሮች እንዳሉ ይረዳሉ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን አጠቃላይ ግቡ ሊሳካ ይቻላል ብለው ማመን መርጠዋል፡፡ ግማሽ ሙሉ ፍልስፍናን እንደመስፈርት እንደንጠቀም የሚገፉንም ለዚህ ነው፡፡ ለዚህም መከራከሪያ ብለው ያስቀመጡት በመሰረታዊ ዕድገት አማራጭ ከአስራ አንድ በመቶ በላይ እናድጋለን ብለን ነበር አሰር በመቶ ከዚያም ትንሽ ዝቅ ያለ ቢሆንም ዋናው ዕቅዱ የተለጠጠ ስለነበር ጥሩ ነበር ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል እንደሆነ ተደርጎ ስለሚነገረን መዘጋጀት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለምን? ቢባል መልሱ ባለ ብዙ ዘርፍ ነው፡፡ አንዱ በምክር ቤት ደረጃ ባሉ የኢህአዴግ አባላት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አልተሳካም ተብሎ በሚመጣ ጣጣ ከሞቀ /አንፃራዊ ነው/ ወይም ከአዲስ አበባ ኑሮ ወደ ወረዳ መውረድ ሊያስከትል ይቻላል፡፡ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም እንዳሉት ወረዳ ወርዶ መስራት ቀላል አይደለም፡፡ ሌላው ደግሞ ይህ የተጠቀሰው ስጋት የብዙዎቹ ካድሬዎች ሊሆን ቢችልም ይህ ሰጋት የሌላቸው ጎምቶዎቹ ኢህዴጎች ግን የተንደላቀቀ የገዢነት ቦታ ላለማጣት የእድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ በአብዛኛው ተሳክቶዋል በሚለው የመንግሰት ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ እኛንም እራሳቸውንም ለማሳመን መጣራቸው የማይቀር ነው፡፡ በኢህዴግ የሚዲያ አጠቃቀም ስትራቴጂ 
የተወሰኑ ሰዎች ሰለጉዳዩ የፈለገ ጥልቅ እውቀት ቢኖራቸው አጠቃላይ ህዝቡን በተለይም ለስልጣኝ መሰረቴ ነው የሚለው ድሃውን 
እስካታለለ ድረስ ስለ መረጃ ትክክለኝነት አይጨነቅም እና ለዚህ በሚደረግ ሽርጉድ እኛንም እውነት እስኪመስለን ድረስ ይህን እውሸት ልንሰማው መቻላችን በቅርብ ርቀት ያለ ሀቅ ነው፡፡ 
 
የዚህ ፅሁፍ መነሻ በቅርቡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሶስተኛ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ አሰመልክቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ቀርቦ ነበር፡፡ ሪፖርቱን ተከትሎ የኢህአዴግ አባላት የሚሰጡት አስተያየት ሪፖርቱን ያነበቡት አይመስሉም፡፡ ከሪፖርቱ ይዘት ይልቅ ቀልባቸውን የሳበው የኢቲቪ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ሪፖርቱ በግልፅ ዋና ዋና የተባሉትና ዕቅዱ በቀረበበት ወቅት እነዚህ ዕቅዶች አሁን ባለ የፋይናንስ እና የመፈፀም አቅም የሚታሰቡ አይደሉም በሚል ትችት ሲቀርብባቸው የነበሩትን በሙሉ ለማሳካት የማይቻሉ እንደሆኑ አሳይቶዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሲቀርብ የነበረው ትችት ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የቀረበው ሪፖርት “በአጠቃላይ በመሰረተ ልማት ፕሮግራሞች አፈፃፀም ዙሪያ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሁለንተናዊ አቅም ማነስ፤ የመሰረተ-ልማት ግንባታና ማማከር አግልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም ማነስ እና የፋይናንስ እጥረት ቁልፍ ማነቆዎች ሆነው ታይተዋል” ይላል፡፡ ሲጀመር እኛም ያልነው ኢህአዴግ በሚመራት ሀገረ ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሱት ዋና ግብዓቶች ማነቆ ስለሆኑ እንደዚህ ያለ የተለጠጠ ዕቅድ መሳካቱ ያጠራጥራል ነው እንጂ በዓለም ላይ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የሰፈሩት ፕሮጀክቶ አይተገበሩም መተግበር የማይችሉ አስማት ናቸው አላልንም፡፡ አንባቢ ልብ እንዲልልኝ የምፈልገው በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ የሀገራችን እድገት 11.2 በመቶ አማካይ ይሆናል 
የተባልነው፤ የኢንዱስትሪ/ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከ20 በመቶ በላይ፤ የአስፋልት መንገድ ሳይጨምር የገጠር ቀበሌዎችን ከዋና መንገድ ጋር የሚያገናኙ ከ71 ሺ ኪሎ ሜትር ክረምት ከበጋ የሚያገለግሉ መንገዶች ግንባታ፤ የአዲስ አበባን ቀላል ባቡር ግንባታን ሳይጨምር 2395 ግርማ ሠይፉ ማሩ ኪሌ ሜትር የባቡር መስመር ግንባት፤157 ሺ ቤቶችን መገንባት፤ 10 ሺ ሜጋ ዋት የሚደርስ የኢነርጂ ልማት፤ በስኳር ልማት የሀገር ውስጥፍጆታን ሸፍኖ ከስድሰት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማሰገባት፤ በማዳበሪያ ምርት ከፊል የሀገር ውስጥ ፍጆታን መሸፈን፤ወዘተ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አሰማተኛውን የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ድርጅት የተሰጠውን ተግባር የተቀመጠለትን ግብ ትተን ማለት ነው፡፡ በግብርና ዘርፍ በሰፋፊ እርሻ የታቀዱትን ዝርዝር ግቦችንም ሳንረሳ ማለት ነው፡፡ 
 
እነዚህ ሁሉ በማነኛውም መመዘኛ በዕቅዱ ዓመት ማጠናቀቂያ የዕቅዱን ግማሻ ሊያሳኩ እንደማይችሉ ለመገመት ነብይ መሆን 
አይጠይቅም፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት ዋና ዋና በተለይም ኢቲቪ ለፕሮፓጋንዳ የሚጠቀምባቸውን እንደማሳያ ወስደን እንመልከት፡፡ የባቡር መስመር ዝርጋት ከተጣለለት ግብ 2395 ኪሎ ሜትር በዕቅድ ዘመን 239 ኪሎ ሜትር ወይም 10 ከመቶ ማሳካት አይቻልም፡፡ በኢነርጂ ዘርፍ የህዳሴው ግድብ ያማነጫል ተብሎ የሚጠበቀውን 750 ሜጋ ዋት እና ግልገል ጊቤ 3ን ጨምሮ አጠቃላይ የሀይል አቅርቦት የእቅዱን ግማሽ ማድረሽ ከባድ ነው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩ የተጣለወን ሃያ በመቶ እድገት ለማሳካት የሚያስችል የግል ሴክተር ተነሳሽነት አይታይም፤ ቢመጣም ማነቆ ብዙ ነው፡፡ የማዳበሪያ ፋብሪካ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ኮንትራቱን ለወዳጅ ዘመዶቹ ቆርሶ በመስጠት /sub-contracting ለሙስና የተጋለጠ አሰራር አለ እየተባለ አሜት ውስጥ ነው፡፡ በዚህ መስመር ምንም የሚታይ እንደሌለ ልማታዊው ኢቲቪ ምስክር ነው፡፡ በቤቶች ግንባታ በአዲስ አበባ ከ850 ሺ በላይ ቤት ፈላጊዎች ቢመዘገቡም በዕቅድ የያዙትን ያህል መስራት ሳይሆን ከተማውን ማፍረስ ነው የተያያዙት፡፡ እነዚህን ሁሉ ደምረን ስናያቸው የ11.2 በመቶ እድገት እንደማይመጣ እነርሱም እኛም ብናውቅ የፖለቲካ ቁጥር ሁለት አሃዝ እድገት ከ 10 በመቶ በላይ እድገት አሰመዝገበናል ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ይበልጣል እንባላለን፡፡ እንዴት ነው ጎበዝ ይህ ነገር ልክ አይደለም ስንል ፀረ ልማት የሚል ቅፅል የያዘ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ይከፈታል፡፡ እንግዲህ ሁሉም ከዚህ አንፃር መዘጋጀት ያለበት ይመስለኛል፡፡ 
 
የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሲጠናቀቅ ኢህአዴግ ቀጣይ የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ እንደሚያቀርብ ፍንጭ የሚሰጡ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡ አዲስ የተቋቋመው በአቶ መኮንን ማንያዘዋል ኮሚሽነርነት የሚመራው የዕቅድ ኮሚሽን ይህን ሃላፊነት ወስዶ እየሰራ ነው፡፡ ቀጣዩ እቅድ የአምስትም ይሁን የአስር አንድ ሀገር ከዚያም ያለፈ መሪ እቅድ እንዲኖራት ማድረግ ራዕይ ካለው መሪና ፓርቲ ይጠበቃል፡፡ በቀጣይ አስር ዓመትም ያለነፃነት ቁሳዊ ግቦችን አስቀምጦ ለመመራት ፍላጎት ያለውን ማነኛውንም ቡድን ግን እያንዳንዱ ዜጋ እንቢ ማለት ያለበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ጊዜው አሁን የሚሆንበት ገፊ ምክንያትም ኢህአዴግ አሳካለው ብሎ ያቀደውን ቁሳዊ እቅድ እንኳን ለማሳከት አቅም እንደሌለው አስመስክሮዋል፡፡ ቀጣዩን ዘመን ከቁሳዊ ግቦች በተጨማሪ ነፃነታችንን የማይገዳደር ዲሞክራሲያዊ ሰርዓት ለሚገነባ ቡድን እድል ለመስጠት መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ኢህአዴግም ድርቅናውን ትቶ በቁሳዊ ዕቅድ ግማሽ ያደረሰውን ብርጭቆ ሳይሰብር ሌሎች የድርሻቸውን መወጣት የሚችሉበት እድል መኖሩን መቀበል ይኖርበታል፡፡ ነፃነት የራቀው የቁሳዊ እቅድ ጋጋታ መቀበል ያለመቀበል የነፃ ዜጎች ምርጫ እንጂ ፀረ ልማት መሆን ወይም የሀገር ልማት መጥላት አይደለም፡፡ 
 
ቸር ይግጠመን 

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen