Netsanet: መንግሥት የሕዝቡን ጩኸት መስማት ግድ ይለዋ

Mittwoch, 16. April 2014

መንግሥት የሕዝቡን ጩኸት መስማት ግድ ይለዋ

April 16/2014


የአክሲዮን ማኅበራትን በማደራጀት ሰበብ የተሰበሰበውን የሕዝብ ሀብት አስመልክቶ ለበርካታ ጊዜያት ለንባብ በቅተው የነበሩት የሕዝብ አቤቱታዎች ዛሬም ምላሽ ሲያገኙ አይታዩም፡፡

ለእነዚያ ብሶቶችና አቤቱታዎች የመንግሥት ምላሽ የዘገየ መሆን ሕዝቡ የሕግ ጥበቃና ከለላ ማግኘት አልቻልኩም በሚል ቅሬታ እንዳያድርበት መንግሥትን ሊያሳስበው ይገባል፡፡

በዚህ አኳኋን ስለተፈጸሙ ድርጊቶች ከኢኮኖሚያዊ አሉታዎችና ተፅዕኖዎች ባሻገር በባህላዊና ቁሳዊ ማንነት ላይ ስለጣሉት ጠባሳ መገምገም ተገቢ ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ችግሮቹን ለመፍታት አለመቻል አንዱ ችግር ሲሆን፣ በሌላ በኩል ግን በሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ እየተመላለሰ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር ድርጊቱ ለአገራዊ ልማታዊ አስተሳሰብ ነቀርሳ መሆኑ ታውቆ አግባብ የሕግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አያጠያይቅም፡፡

የአክሲዮን ማኅበራትን በማደራጀት ስም የተሰበሰበው በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት ጥቂት ጮሌዎች በአቋራጭ ብልፅግና ላልተገባ ጥምቅ እያዋሉት ስለመገኘታቸው ሲታሰብና ዝርፊያውም መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር ላይ የተፈጸመ መሆኑ ሲታወስ፣ የተጎጂዎች ቁጣ በዘራፊዎች ላይ ከመሆን ባለፈ በመንግሥት ላይ ኩርፊያ ሊያስከትል እንደሚችል ነባራዊ እውነታዎቹ እያሳዩን ነው፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው ደግሞ የሕዝብን ቅሬታ የሚሰማ አካል የመታጣቱ ጉዳይ ነው፡፡ በዘረፋው ሒደት ውስጥ የነበሩ እውነታዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ፡፡ በልማታዊ አስተሳሰብ ስም የተፈጸሙ የኪራይ ሰብሳቢዎች የአቋራጭ ብልፅግና ንድፎች እንደነበሩ ለማሳየት ጥናታዊ ጽሑፎችን ማጣቀስ ግድ አይልም፡፡

በአገራችን የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት የፈጠረውና ሕዝቡ በኢኮኖሚው ላይ የተቀዳጀውን የሞራልና የመንፈስ ድል በመጥለፍ ለግል ርካሽ ተልዕኮ የማዋል እኩይ ተግባር እየተስፋፋ ነው፡፡ አገራችን በፈጠነ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ መገኘትዋንና ይህንን የኢኮኖሚ ዕድገት ለሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ መነሳሳት ምክንያት መሆኑን የተረዱ የአቋራጭ ብዕግፅና ጥቅመኞች፣ የተነሳሳውን የሕዝቡን መንፈስ ምናባዊ  የፕሮጀክት ሐሳቦችን እያሳዩ የሕዝብ ሀብት መንጠቃቸው ሲታሰብ፣ ድርጊቱ በግለሰቦች አማካይነት ንዋይ ለመዝረፍ የተወጠነ ስትራቴጂ ከመሆን ባለፈ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ላይ የተፈጠረ ደባ እንደሆነ ለማወቅ አስረጂ አያስፈልገውም፡፡

አደራጆች በአክሲዮን ሽያጭ ወቅት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ጠንካራና ዓማላይ ቃላቶች ፋይዳቸው አክሲዮኖችን በመሸጥ ጠቀም ያለ ገንዘብ ከማግኘት ያለፈ እንዳልነበር በቆይታችን የታዘብነውና ያየነው ነገር ምስክር ነው፡፡

ለሕዝቡ ጩኸት ሕጋዊ ዋስትና ሊያሰጥ የሚችል አካል ብቅ አለማለቱ ለዘራፊዎች ትዕቢት ጥንካሬ ከመሆን ባለፈ የአክሲዮን አደራጆች ላይ ተስፋ መቁረጥን አስከትሏል፡፡

•ባልተገባ የአበልና የደመወዝ ክፍያዎች ዘረፋ፣

•በሽያጭ ስም ለሚወሰዱ እጅግ የተጋነኑ ኮሚሽኖች፣

•በግዥ ስም ለሚወሰዱ የኮሚሽን ዘረፋዎች፣

•የተሰበሰበውን ገንዘብ ለሌላ የግል ጥቅም የማዋል ሕገወጥ ተግባራት፣

•ለዘመድ አዝማድ ያልተገባ የሥራ ዕድል ባልተገባ ክፍያ ማመቻቸት፣

•የንግድ ልውውጡን ግላዊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባላቸው ፋይዳ ብቻ እንዲታዩ በማድረግ  ሕገወጥ ተጠቃሚነትን መከተል፣

•የድርጅቱን ስምና ዝና ለግል መጠቀሚያ ማድረግ ከሚታዩ ሕገወጥ ተግባራት በምሳሌነት የሚጠቀሱና ሕዝቡ የተቸገረባቸው ድርጊቶች ናቸው፡፡

ወላጆች ለልጆቻቸው ሕክምና ዋስትናና ለሌላ መጠባበቂያ የደበቁትን ሀብት፣ የሰሙትን በማመንና ተስፋ በማድረግ አክሲዮን ቢገዙም ማለቂያ በሌላቸው ምክንያቶች ገንዘቡ እየተበላ ትርፉ ቀርቶ ያዋጡትን ገንዘብ ዋናውን ማግኘት የሚችሉበትን ጊዜ ይናፍቃሉ፡፡

ውንብድናውን የሚያካሒዱት የሕዝብ ሚዲያ በመንተራስ፣ የሕጋዊነት ሽፋን ተላብሰው የታዋቂ ሰዎችን ስምና ምሥል በመጠቀም ስለሆነ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት አባብሰውታል፡፡ የመንግሥት መጠቃሚያ በሆኑ ሚዲያዎች ሕዝቡ ውሸት ይስተናገዳል ብሎ ስለማያስብ በቀላሉ ለመታለል ተመቻችቷል፡፡ ሚዲያውን፣ የታዋቂ ሰዎችንና የአገር ሽማግሌዎችን ስም ለግል እኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያነት ያውላሉ ብሎ የሚገምት ባለመኖሩ ችግሩ ተባብሷል፡፡

ሆኖም እነዚህ የመልካም ተግባር ማስፈጸሚያ የሆኑ ተቋማትን ተጠቅመው ጮሌዎች ሕዝቡን አሳሳቱ ከተባለ፣ ተቋማቱስ ተጠያቂ መሆን አይገባቸውም? እነዚህ ተቋማት ለእኩይ ነገር መጠቀሚያ እንዳይውሉ ሊጠብቃቸው የሚገባ አካልስ መኖር አልነበረበትም? ሕዝቡ የተሳሳተው እኮ በአሳሳቹ ብቻ ሳይሆን የመረጃ ማስተላለፊያ በሆኑ ተቋማት ጭምር ነው፡፡

ስለዚህ ጉዳይ ሳስብ አንድ የገጠመኝን ነገር እንደሚከተለው ላስነብባችሁ ወደድኩ፡፡ በአንድ አክሲዮን ማኅበር ውስጥ አንድ የታወቁ ጡረተኛ የአገር ሽማግሌ ከዋና አደራጅነት እስከ ቦርድ አመራርነት ይሳተፋሉ፡፡ በኩባንያው የምሥረታ ራዕይ ውስጥ ያላቸውን ሚና እንዲያስረዱኝ ስጠይቃቸው፣ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለና ለስብሰባ ሲጠሯዋቸው ከመምጣታቸው ውጭ ስለ ራዕዩና ሥራው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ስሰማ በጣም አዘንኩ፡፡ ይህንን አለማወቃቸው ከተጠያቂነት እንደማያድናቸው ቢታወቅም፣ በስማቸው ስንት ወንጀል እየተሠራበት ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ ባይዘገዩ ይበጃቸዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥታችን ከላይ በተጠቀሱት ተቋማት አማካይነት ስለተላለፉ መረጃዎች ትክክለኛነት ሊጠይቅና ሊከታተል አለመቻሉ ሕዝቡን ግራ አጋብቶታልና አሁንም ተጎጂው አቤት እያለ ነው፡፡

ዘረፋው ‹‹በመተማመን›› በሚለው የኢትዮጵያውያን ባህላዊ እሴት ካባ ሥር የተፈጸመ ደባ በመሆኑ የሕግ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ባህልና ወጋችን በሆነው መተማመን  እሴታችን ላይ በመመርኰዝ የተፈጸመ ዘረፋ ስለሆነ ባህላችንን ያቆሸሸና የበከለ ሥራ ተደርጎ  ሊፈረጅ ይገባዋል፡፡

ምሑሮች  ነን፣ መልካም የንግድ ሐሳብ አለን፣ በአጭር ጊዜ ኑሮን የሚለውጥ ትርፍ እናስገኝሎታለን፣ ለራዕያችን እውን መሆን አንዳች እንቅፋት የለብንም፣ በሚሉና በመሳሰሉት የውሸት ስብከቶቻቸው አማካይነት በሰበሰቡት ገንዘብ የገቡትን ቃል  ላለመፈጸማቸው ተጠያቂ ሊያረጋቸው የሚችል የሕግ አካል ማጣት፣ ለመተማመን ባህላችን ዋጋ ካለመስጠት ባለፈ ወንበዴን እንደማበረታታት ይቆጠራል፡፡

ከሕዝቡ በዘረፈው ገንዘብ ከመሬት ተነስቶ የብዙ ሚሊዮኖች ባለቤት ከመሆን አልፎ  የውጭ አገር ንግድ የጀመሩ አክሲዮን አደራጅ ጥቂት አይደሉም፡፡ ያደራጇቸው አክሲዮኖች ግን ገንዘባቸውን ላወጡ ሰዎች አንዳችም ፋይዳ ሳያመጡ እስከ ሰባት ዓመት ማስቆጠራቸው ሲታይ የማይገርመው ያለ አይመስለኝም፡፡

በምሥረታ ወቅት የንግድ ዓላማቸውን ጉዞ የሚያደናቅፍና የሚያዘገይ አንዳች ነገር እንደሌለ እንዳልሰበኩን ቆይተው ሲመጡ የመንግሥት ድጋፍ ሥልጣን ነው፤ የገንዘብ አቅርቦት በመንግሥት አመራር ሥር በመሆኑ ነው፣ መሬት በመንግሥት መያዙ ችግር ሆኖብን ነው፣ በማለት ልማታዊ አስተሳሰባቸው በልማታዊ መንግሥት እንደተደናቀፈባቸው በማውራት ሕዝቡን ከመንግሥት ጋር ሆድና ጀርባ እያረጉት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች አክሲዮን በሚሸጡበት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች እንዳሉ አንድም ወቅት እንዳላነሱ በማስታወስ ዛሬ ለምን ይህ ምክንያት እንዲያወቁ እንደተፈቀደላቸው ግራ ያጋባል፡፡ ፈረንጆቹ ‹‹Blame Game›› ወይም የማሳበብ ጨዋታ እንደሚሉት እየተጫወቱ የእነሱ ልማታዊ ራዕይ ልማታዊ ባልሆነ መንግሥታዊ ፖሊሲዎች እንደታገተባቸው የአዞ እንባቸውን የማንባት ሰበካ ጀምረዋል፡፡

በአጠቃላይ ሕዝቡ የደረሰበትንና እየደረሰበት ያለውን በደል የሚሰማለት አካል አጥቷል፡፡ መንግሥት የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ አገራዊ፣ አካባቢያዊና ግለሰባዊ ጠቀሜታቸውን በአግባቡ ለማካሄድ የሚያስችል አቅም በፈጠረበት በዛሬ ወቅት፣ በቢሊዮን ብሮችና በብዙዎች መስተጋብር ስም እየተፈጸመ ያለውን ያልተገባ ጥቅም የማግበስበስ ጥረት  ሊያስቆመው ግድ ይለዋል፡፡ በአክሲዮን ሽያጭ መግለጫዎች ላይ ቃል የተገባባቸው ዕቅዶችን ካልተፈጸሙ ተጠያቂ የማስደረግ ግዴታቸው እውን መደረግ አለበት፡፡ በአክሲዮኖች ውስጥ በግለሰቦች ትዕዛዝ የሚፈጸሙ ወጪዎች፣ ግዥዎችና ክፍያዎች ለአቋራጭ ብልፅግና መሠረት ሆነዋልና የሚያስጠይቁ ይሁኑ፡፡

ተበዳዮች ጥቆማቸውንም ሆነ ብሶታቸውን ሊያሰሙበት የሚችሉበት ማዕከል መፈጠርም አለበት፡፡ የግለሰቦች ባልተገባ ጥቅም ውስጥ መናኘት የኪራይ ሰብሳቢነት ባህል አስተማሪ ስለሆነም ይህንን የሚያስቆም አካል አሁንኑ ሊፈጠር ይገባዋል፡፡

በግዥ ኮሚሽን ሰበብ በርካታ ሚሊዮኖችን ያለ አግባብ በማካበት ተጠቃሚ የሆኑና በሕዝብ ገንዘብ የተመሠረተውን ኩባንያ ጥቅም እያሳጡ ያሉ የቦርድ አመራሮችን ማስቆም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም እላለሁ፡፡ በሚቀጥለው እስከምንገናኝ ድረስ ቸር ይግጠመን፡፡

(ከታዛቢ፣ አዲስ አበባ)

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen