አቶ ስብሃት ነጋ
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሠላም ኢኒስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑትና የቀድሞ የሕወሓት ሊቀመንበር አቶ ስብሃት ነጋ (አቦይ ስብሃት) በአሁኑ ወቅት ኒዮሊብራሊዝም የሚባል ነገር የለም ሲሉ ተናገሩ።
አቦይ ስብሃት ይህንን የተናገሩት የሚመሩት ተቋም በትናንትናው ዕለት Autocratic Developmental State (አምባገነን ልማታዊ መንግስት) በሚል ርዕስ በሸራተን ሆቴል የተካሄደውን ውይይት መሠረት በማድረግ ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ ነው።
አቦይ ስብሃት በአሁኑ ወቅት “ኒዮሊብራሊዝም” አስተሳሰብ እያከተመ መምጣቱን የገለፁት እ.ኤ.አ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስን ተከትሎ በአሜሪካና በአውሮፓ እንዲሁም በቻይና በገበያ ውስጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እየበረታ መምጣቱን በመግለፅ ነው።
“ሁሉም ካፒታሊዝም ያደገው በልማታዊ መንግስት ወይም በአጭሩ በመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው” የሚሉት አቦይ ስብሃት በአሜሪካ፣ በቻይናም ሆነ በአውሮፓ የካፒታሊዝም እድገት ሞተሩ መንግስት ነው ብለዋል። ይህም ማለት አሜሪካ አውሮፓና ቻይና ልማታዊ መንግስታት ነበሩ ማለት ነው ብለዋል።
በዓለም ላይ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ልማታዊ የነበረ መንግስት በፍፁም አልነበረም ሲሉ የሚጠቅሱት አቦይ፤ በኢትዮጵያ አሁን ያለው ስርዓት ግን ዴሞክራሲያዊም ልማታዊ ስርዓት ነው ሲሉ አብራርተዋል። ከኢትዮጵያ ጋር ሊቀራረብ የሚችለው በከፊልም ቢሆን፤ ዴሞክራሲንና ልማትን በማጣጣም ማስኬድ የቻለው ሀገር ህንድ ብቻ ነው ብለዋል።
በሸራተን አዲስ ሆቴል በተጠራው ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ በሁለት አሜሪካውያን ምሁራን የቀረበው ፅሁፍ “አምባገነናዊ ስርዓትና ልማታዊ መንግስት” አንፃር በኢንዶኔዢያ፣ በማሌዢያና በሌሎች የሩቅ ምስራቅ አገሮች የነበረውን ተሞክሮ ለማከፋፈልና ለመወያየት እንደሆነም ከአቦይ ስብሃት ገለፃ መረዳት ይቻላል። የውይይቱ አስፈላጊነት ምንድን እንደሆነም የተጠየቁት አቦይ “እኛ ኢትዮጵያውያን የምናውቀው ነገር የለም። ባዶ ነን። ዴሞክራሲ ምን እንደሆነ አናውቅም፣ ልማት ምን እንደሆነ አናውቅም፣ መልካም አስተዳደርም ምን እንደሆነ አናውቅም፣ ስለ ምርታማነትና የዋጋ ግሽበት የጠለቀ እውቀት የለንም። ካለፉት ስርዓቶች እየወረስነው የመጣነው ነገር ስለሌለ፤ እነዚህን ንድፈ-ኀሳቦች የባዕድ እቃ አድርገን ስለምንቆጥር ማንኛውም የንድፈ-ኀሳብ ውይይት ያስፈልገናል” ሲሉ መልሰዋል። ውይይቱ ግን ከመንግስት ከፖሊሲ መሻሻል ጋር ግንኙነት እንደሌለውም በዚህ አጋጣሚ ጠቁመዋል። መስሪያ ቤታቸው በቀጣይ ግንቦት ወር ተመሳሳይ ዝግጅት እንደሚኖረውም ገልፀዋል።
“ኒዮሊብራሊዝም” የሚለው ርዕዮተ ዓለም በተመለከተም ይበልጥ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት አቦይ ስብሃት አሁን ኑዮሊብራሊዝም የሚባል ነገር የለም፣ ይህ አስተሳሰብ “የእናንተ መንግስት ወደ ገበያ አይግባ፣ ለእኛ ልቀቁልን” ከማለታቸውም ባለፈ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን በአሁኑ ወቅት ከእኛ በላይ እነሱን [አሜሪካና አውሮፓዊያንን ማለታቸው ነው] ተግባራዊ እያደረጉት ነው ብለዋል።
“አሁን ባለው ሁኔታ በመንግስት ጣልቃ ገብነት አሜሪካ አንደኛ፣ አውሮፓ ሁለተኛ ሦስተኛ ቻይና ናት” የሚሉት አቦይ ስብሃት በተለይም ከ2008 እ.ኤ.አ በኋላ እስካሁን የአሜሪካ መንግስት በገበያው ውስጥ እጁን ያስገባው በሚያስደነግጥ ደረጃ ነው ብለዋል። መገለጫውም ቤል አውት፣ ሲትሙለስ በማለት ደሃውን እየቀረጠ ሀብታሙን የሚያድን ተግባር ውስጥ ዝፍቅ ብሎ ገብቷል ሲሉ አስረድተዋል። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ኢኮኖሚ የመንግስት ኢኮኖሚ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
በአውሮፓም የተከሰተውን የኢኮኖሚ ቀውስን ገበያው ሊፈታው ባለመቻሉ ገበያው አንቅሮ የተፋውን ሠራተኛ እንደውሻ እየመገቡ የሚኖሩ የአውሮፓ መንግስታት ተፈጥረዋል ሲሉ አስረድተዋል።
ቀደም ሲል “ኒዮሊብራሊዝም” የሚለው አመለካከት ያላደጉ አገሮችን መንግስታት ፖሊስ በማድረግ የአደጉ አገሮች እንዝረፋችሁ የሚል አቅጣጫ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ግን እነሱም በገበያ ስርዓታቸው ውስጥ ገብተው ሕዝባቸውን እየደጎሙ መሆኑን አብራርተዋል።
ምንጭ፦ ሰንደቅ ጋዜጣ
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen