April 29, 2014
ከ97ቱ በእጅጉ የተቀዛቀዘው የ2002ቱ ምርጫ የቀናት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል፤ ከመቼውም በላይ የፖለቲካ ምህዳሩን ያጠበበው ገዢው ግንባር፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገውን የምረጡኝ ክርክር እንደ 97ቱ በቀጥታ ስርጭት እንዲተላለፍም ሆነ በአዳራሹ ታዳሚዎችና ታዛቢዎች እንዲገኙ አልፈቀደም፤ በዚህ ክርክር ላይ ኢህአዴግ እንደተለመደው ለመጀመሪያ ጊዜ ካቀረባቸው ጥቂት አፈ-ቀላጤዎቹ መካከል የተመልካችን ትኩረት በመሳብ ጎልማሳው የወራቤ ፍሬ ሬድዋን ሁሴንን የሚተካከል አልነበረም፡፡ ሬድዋን ዕድሉን ካገኘ እንደ ‹‹ጓድ›› መንግስቱ ኃ/ማሪያም ለሰዓታት ሳያቋርጥ ቃላቶችን እንደ መትረየስ አከታትሎ ማንጣጣት ጎልቶ የሚታወቅበት ባህሪው ነው፤ ‹ከሎጂክ› ይልቅ የተዋቡ አረፍተ ነገሮችን መደርደር ይቀናዋል፤ በየመሀሉም የመድረክ ተወካዮችን ‹‹ራዕይና የጠራ ፖሊሲ የሌላቸው››በማለት ይዘልፋል፤ መልሶ ደግሞ ‹ፀረ-ኢትዮጵያዊና ፀረ-ሰላም ናቸው›› ሲል ይኮንናል፡፡ በየሰከንዱ በአስደንጋጭ እና በአደገኛ(Inflammatory) የቃላት ሰይፍ ይመትራቸዋል፡፡ ይህ ‹‹ታጋይ››ነቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በጉምቱ የድርጅቱ ሰዎች ዘንድ ሞገስን አስገኝቶለታል፡፡ ይሁንና ከዕለታት በአንዱ ቀን በዛው አድናቆት በተቸረበት የክርክር መድረክ፣ እንደልማዱ ቃላት ስንጠቃው ላይ ተጠምዶ የነገር ጦሩን ሲያወናጭፍ ድንገት አዳልጦት ታላቅ ‹‹ስህተት›› ፈፀመ፡፡
የሬድዋን ‹‹ስህተት›› ድርጅቱ-ኢህአዴግ አፄ ምኒሊክን፣ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ የሚያብጠለጥልበትን የታሪክ ንባብ ገልብጦ መተንተኑ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ግንባሩ ንጉሡ ዐድዋ ላይ ጣሊያንን ድባቅ ከመቱት በኋላ እግር እግሩን ተከትለው እያሳደዱ መረብን በመሻገር፣ ከምድረ-ኤርትራም ጠራርገው ለማስወጣት አለመሞከራቸው፤ በአካባቢው ተወላጆች ዘንድ ለተፈጠረው የተገንጣይነት ስሜት ገፊ-ምክንያት አድርጎ መስበክ የጀመረው ከበረሃው ዘመን አንስቶ ነው፡፡ ይሁንና ከተማ ውስጥ በአቋራጭ የተቀላቀላቸው አዲሱ ‹‹ካህን›› ሬድዋን ሁሴን ፕሮፓጋንዳው እንደ በረኸኞቹ ‹‹ካህናት›› ከደም-አጥንቱ ጋር በደንብ አልተዋህደምና ምኒሊክ ከአድዋ ድል በኋላ ጦርነቱን እስከ መረብ-ምላሽ ድረስ ልግፋው ብለው ወደፊት ቢቀጥሉ ኖሮ ለአሰቃቂ ሽንፈት ከመዳረጋቸውም በላይ፣ በሺዎች መስዋዕትነት የተገኘውን ድልም አሳልፈው በመስጠት ትርጉም አልባ ያደርጉት እንደነበረ በመሞገት፣ ስለወቅቱ የንጉሡ ውሳኔ ትክክልነት ኢህአዴግን ወክሎ በተገኘበት መድረክ ላይ በይፋ መሰከረ፡፡ ይህ ከድርጅቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ‹ቅዱስ መጽሐፍ› የሚጣረስና አለቆቹንም ያስከፋ ‹‹ስህተት››፣ በቀሪዎቹ የክርክር መድረኮች ላይ እንዳይሳተፍ እግድ አስጣለበት፡፡
ዘፍጥረት
ገዥው-ፓርቲ፣ በድል አድራጊነት መንግስታዊ ሥልጣኑን ጠቅልሎ ከያዘ በኋላ፣ መናፍቃውያን መሪዎቹ ባዘጋጇቸው ‹‹የታሪክ ድርሳናት››፤ በውይይት መድረኮች እና በቁጥጥሩ ስር ባዋላቸው መገናኛ ብዙሀን አማካኝነት ኢትዮጵያ የምትባለዋ የ3 ሺህ ዓመታት ቀደምት ገናና ባለታሪክ ሀገር፣ በተሟላ ቅርፅ የተፈጠረችው በግንቦት ሃያው ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች›› ድል አድርጎ የሚያቀርበውን የፈጠራ ታሪኩን እንደ እውነት ለማስረፅ በርካታ ድንጋዮችን ፈነቃቅሏል፤ ተራሮችን ቧጥጧል፡፡ ለዚህ ስሁት ስብከቱም በደጋፊ ማስረጃነት የሚያቀርበው የማዕከላዊ መንግስቱን ምስረታ የዘመናት ሂደት ሲሆን፤ ሂደቱንም ‹‹ታገልኩለት›› ለሚለው ዘውግ ተኮር ፖለቲካ ቅቡልነት ሲል ለዘረፋ እና ለወረራ (ለቅኝ ግዛት) የተደረገ አስመስሎ እስከ ማቅረብ ያደረሰው ዘመንና ታሪክ ሽቀባ ውስጥ ገብቷል፡፡ እነሆ የዚህ ውጤትም ዛሬ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ላንዣበበው ጊዜ አመጣሽ የእርስ በእርስ ግጭት መነሾ ሆኗል፡፡
ምዕራፍ አንድ
ኢህአዴግ-መሩ መንግስት ከአንድነት ይልቅ፣ በተናጠል ማንነት ላይ በተመሰረተ አዲስ ታሪክ እንዲቆሙ ያስገደዳቸው ህዳጣን ጨምሮ፤ በሀገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዘውጎችንም በራሱ የታሪክ ብያኔ አፍርሶ እንደ አዲስ ለመስራት አሀዱ ያለው ገና የሥልጣን እርካቡን እንኳ አደላድሎ ባልረገጠበት ጊዜ እንደነበር የትላንት ትውስታችን ነው፡፡ በተለይም ሰፊው ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪን፣ ራሱን የባለፈው ዘመን ብቸኛ የጥቃት ሰለባ አድርጎ በመውሰድ እንዲብሰለሰል ሲገፋ፤ አማርኛ ተናጋሪውን ደግሞ በቀደሙት አባቶቹ ታሪክ የሚያፍርና የሚሸማቀቅ ሆኖ እንዲቀር ለሁለት አስርታት ያልከለሰው ድርሳን፤ ያልደመሰሰው መዛግብት አልነበረም፡፡
አብዮታዊ ግንባሩ በታገለለት የዘውግ ፖለቲካ የሚበየነው ስርዓት ህልውናን ለማስረገጥ፤ በደምና አጥንት የቆሙ የአንድነት አምዶችን አፈራርሷል፤ የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብርን ለዘመናት ያፀኑ ቅፅሮችን ለመንደር ፖለቲካው ትግበራ ሰውቷል፡፡ ለከፋፋይ አስተዳደሩም በሀገር አቅኚነት ራዕይ ስር የተፈፀሙ የማንነት ጭፍለቃዎች፣ የራስ ገዝ አስተዳደር መናድ፣ የጦር ሜዳ እልቂቶች፣ የንብረት ውድመቶችን…
አብዮታዊ ግንባሩ በታገለለት የዘውግ ፖለቲካ የሚበየነው ስርዓት ህልውናን ለማስረገጥ፤ በደምና አጥንት የቆሙ የአንድነት አምዶችን አፈራርሷል፤ የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብርን ለዘመናት ያፀኑ ቅፅሮችን ለመንደር ፖለቲካው ትግበራ ሰውቷል፡፡ ለከፋፋይ አስተዳደሩም በሀገር አቅኚነት ራዕይ ስር የተፈፀሙ የማንነት ጭፍለቃዎች፣ የራስ ገዝ አስተዳደር መናድ፣ የጦር ሜዳ እልቂቶች፣ የንብረት ውድመቶችን…
እያጎነ ትልቁን ምስል ለማደብዘዝ ያለመታከት ሰርቷል፡፡ ለዚህ አይነቱ አፍራሽ ዓላማም እንደማቀጣጠያ የተጠቀመው የ‹‹ታሪክ ተጎጂ›› ወይም ‹‹ሰለባ›› እንደሆኑ ቀን ከሌት የሚሰብካቸው ህዳጣን በጥቂት ልሂቃኖቻቸው ግፊት ያቀነቀኑትን የ‹‹ተረሳን›› አጀንዳ፤ እንዲሁም በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሐረር የተለያዩ
ከተሞች የአፄ ምኒልክ ሠራዊት ያደረጋቸውን የአንድነት ዘመቻዎች ማሳካትን ተከትሎ የተከሰቱ የእርስ በርስ ጭፍጨፋዎች እና የባሕል ተፅእኖዎችን ነው፡፡
ከተሞች የአፄ ምኒልክ ሠራዊት ያደረጋቸውን የአንድነት ዘመቻዎች ማሳካትን ተከትሎ የተከሰቱ የእርስ በርስ ጭፍጨፋዎች እና የባሕል ተፅእኖዎችን ነው፡፡
ከዚህም ሌላ ሥርዓቱ ለእንዲህ አይነቱ የኑፋቄ ትርክት ያመቸኛል ብሎ የመዘዘው የታሪክ ሰበዝ በጊዜው አማራጭ ያልነበረውን ጠንካራው፣ ደካማውን ጨፍልቆና አስገብሮ አሀዳዊ ሀገር የመገንባት ሂደትን በማንሸዋረርና ፈጠራ በመጨመር ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ‹‹የጊዜ እንጂ የሰው (የብሔር) ጀግና የለውም›› እንዲሉ፤ ኢህአዴግ ጨቋኞቹ-ተጨቋኝ፤ ተጨቋኞቹ ደግሞ ጨቋኝ የሚሆኑበት ጊዜ እንደነበር ትንሽ እንኳ ግንዛቤ ለመውሰድ ጥቂት የታሪክ መዛግብትን ብቻ ማገለባበጥ በቂ መሆኑን በሚገባ ቢያውቅም፤ ታሪካዊ ተጠያቂነቱን ሙሉ ለሙሉ ወደ አንድ ዘውግ እስከ መወርወር ደፍሯል፡፡ በግልባጩ በዚህ አይነቱ ታግሎ የመጣል ትንቅንቅ ከዛላንበሳ እስከ ቦረና፤ ከቋራ እስከ ኡጋዴን የሚመተረው የዛሬይቷ ኢትዮጵያ ወሰን መፈጠሩን ሲክድ ቅንጣት ታህል ሀፍረት አልተሰማውም፡፡ በነገራችን ላይ የዚህ ነውረኛ የፖለቲካ ጨዋታ አመንጪዎቹ አቶ መለስ ዜናዊ እና ጓዶቹ ማዕከላዊ መንግስትን ለመመስረት የሚደረጉ መተጋግሎች ከነፍጥና መስዋዕትነት በቀር የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው፣ በዓለም ታሪክም የእነምኒሊክ የመጀመሪያው አለመሆኑን፤ እንደ አሜሪካንና አውሮፓውያንም ያሉ ታላላቅ ሀገራት በዚህ መሰል የእርስ በእርስ ደም መፋሰስ ውስጥ አልፈው፣ ዛሬ እኛም ጭምር በምኞትና በስደት የምንቀላውጠውን ነፃነትና ብልፅግና የተትረፈረፈበት ሀገር መገንባት መቻላቸውን ጠንቅቀው የማወቃቸው ጉዳይ አከራካሪ አይደለም፡፡ እናም ሌላ ሌላውን ትተን ከእነአሰቃቂው ጭፍጨፋ ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ጅማሮ የተከፈለውን ውጣ-ውረድ ብናስተውል፣ ሙት ወቃሽ የሆንባቸው በተከታታይ የመጡ ነገሥታትን ውለታ እንዲህ በቀላሉ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም ብዬ አምናለሁ፡፡
ምዕራፍ ሁለት
ኢህአዴግ ያለፉትን ሁለት አስርታት ያለመንገራገጭ ማለፍ የቻለው በጠብ-መንጃ፣ እንደ አሸን በፈሉ ሰላዮቹ፤ እንዲሁም ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ከኃይማኖታዊ እስከ ዓለማዊ ማሕበራት ውስጥ በዘረጋው የካድሬ ጥርነፋ ብቻ ሳይሆን፤ ለርዕዮተ-ዓለሙ ሳጋና-ማገር ያደረገው የሀገሪቱን ታሪክ ከልሶ፣ ደልዞ እና ፈጠራ አክሎበት በመስበኩም ጭምር መሆኑ በግላጭ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ መቶ እና ሁለት መቶ ዓመት ወደኋላ ተጉዞ የትላንት ስህተቶችን የዛሬ አስመስሎ ከማቅረብም ተሻግሮ፣ በፖለቲካው ቦታ ታሪክን ተክቶ እየሄደበት ያለው ዕርቀት ሰሞኑን ግንባታው አልቆ እስከተመረቀው የአኖሌ መታሰቢያ ሐውልት ያደረሰው መሆኑን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል (ቁልቢ ገብሬኤል አካባቢ እየተሰራ ያለው የጨለንቆ ሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልትም በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል)፡፡ ግና፣ ይህ በሰይፍ በተቆረጠ የእንስት ጡት ምስል የተሰራው ሐውልት፣ እንዲነግረን የታሰበውን ያህል ነውረኛ ድርጊቱ ተፈፅሟል፣ አልተፈፀመም የሚለው መከራከሪያ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በዚህ ተጠየቅ የምንፈትሸው ከመቶ ሃያ አራት ዓመታት በኋላ፣ በቀልን የሚሰብክ ሐውልት መገንባቱ ማንን ለመጥቀም ተብሎ ነው? የሚለውን ነውና በዛው ላይ እናተኩራለን፡፡
የርካሹ የፖለቲካ ስልት ጅማሮ የበረሃው ዘመን ቢሆንም፤ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የታየው የዘውግ አጥር ያላገደው ትብብርና የአትንኩኝ ባይነት ንቅናቄ፣ አገዛዙ በተወሰነ መልኩም ቢሆን፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነት ላይ የሚያተኩሩ ጉዳዮችን ለማጉላት እንዲሞክር አስገድዶት እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ይሁንና በ1997 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ውጤት የፈጠረበት ድንጋጤ ግን ከቀድሞውም በከፋ ሁኔታ ከፋፋይ ፖለቲካውን ወደማጎኑ እንዲመለስ አድርጎታል፡፡ ያ እንደዋዛ የምናነሳው፣ አቶ በረከት ስምኦን ‹‹ናዳ›› ሲል የገለፀው ምርጫ ብዙሃኑን ሕዝብ የልዩነትን ደጃፍ አሻግሮ ከአም-ባገነኑ ሥርዓት በተቃራኒ በአንድነት እንዲቆም ማስቻሉ መንግስትን ከዘላለማዊነት ማማው አውርዶ፣ የሥልጣን ዕድሜውን በቀናት እንዲወሰን እየገፋው ስለመሆኑ በሴራ ከተካኑት የድርጅቱ መሪዎችም ቢሆን የተሰወረ አልነበረም፡፡ እናም ከ‹‹ናዳ›› ጋር ባነፃፀሩት የምርጫ ውጤት ልባቸው የከፋ ቂም በመቋጠሩ መደብዘዝ ጀምሮ የነበረው የ‹‹ከፋፍለህ ግዛ›› ስልታቸው ይበልጥ አቆጥቁጦ፣ የዘውግ ልዩነቱ ወደከፋ ጥላቻ እንዲቀየር ቀን-ተሌሊት እየሰሩ መሆኑን ለማስረገጥ ሰሞኑን መነጋገሪያ ከሆነው የአኖሌ ሐውልት ግንባታ በተጨማሪ ጥቂት ማሳያዎችን አቀርባለሁ፡፡
የመጀመሪያው በምርጫው ማግስት በየዓመቱ ህዳር 29 ‹‹የብሔር ብሔረሰብ ቀን›› ተብሎ በከፍተኛ ወጪ እንዲከበር አዋጅ እስከ ማውጣት መድረሱ ነው፡፡ ምናልባትም የኢህአዴግን አምታች ፕሮፓጋንዳ በፍፁም ልቦና በማመን ይህ ጉዳይ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጥበቅና የልምድ ልውውጥ ለማካበት ታስቦ የተዘጋጀ የሚመስላቸው የዋሃን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግና፣ ደጋግመን እንደተመለከትነው የበዓሉ ዋነኛ ማድመቂያ ከምዕተ-ዓመት በፊት ‹‹ተፈፀሙ›› የተባሉ አገዛዛዊ በደሎች፣ ዘውግ-ተኮር ጥቃት መስለው እንዲቀርቡ በማድረግ ላይ ያነጠጠረ መሆኑን ነው፡፡ ሁሌ በየክብረ-በዓሉ ሰሞን አንዳንድ ፀጉራቸው ላይ ላባ የሰኩና ቆዳ ያገለደሙ ሰዎች በቴሌዥቪን እየቀረቡ ያለፉት ሥርዓታት ምን ያህል በደል እንዳደረሱባቸው እንባ እየተናነቃቸው ከገለፁ በኋላ፣ ዛሬም ቢሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በብሔር ብሔረሰቦች ትግል ወደተሸነፈው አገዛዝ ለመመለስ የሚሰሩ መሆናቸውን አስታውሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ በንቃት እንዲከላከልና የተገኘውን ድልም ነቅቶ እንዲጠብቅ ሲመክሩ ማድመጣችን ከበዓሉ ጀርባ ያለውን ቴአትር ያጋልጣል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሁለተኛው ማሳያ ደግሞ በ2001 ዓ.ም. በደቡብ ክልል ለሚገኙ ዞኖች በደብዳቤ ከተላለፈ አንድ ትዕዛዝ ጋር ይያያዛል፡፡ የደብዳቤው ፍሬ ሀሳብ በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ብሔሮች የየራሳቸውን ታሪክ አጥንተው እንዲያቀርቡ የሚያዝ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ይሆን? ብለን ስናንሰላስል የምናገኘው ምላሽ፣ ከዚህ ቀደም በበቂ ደረጃም ባይሆን በተለያዩ የታሪክ ምሁራን የተዘጋጁ መዛግብትና የተጠኑ ሰነዶች ተደምስሰው፤ ፖለቲከኞቹ እንደ አዲስ የብሔራቸውን ታሪክ ቀምረው የአንድነቱን መስተጋብር ጨፍልቀው፣ በተናጠል ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ማንነት እንዲኖራቸው ማስቻል የሚል ይሆናል፡፡ ከዚህም አኳያ ይመስለኛል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው የሚገኙ አንዳንድ ዘውጎችን በተመለከተ የሚወጡ ‹‹ጥናቶች›› በፀረ-ነፍጠኛ የተጋድሎ ታሪኮች ዙሪያ ሲዳክሩ የምንታዘበው፡፡ ዳሩ! የሥርዓቱ ተጠቃሚ ፖለቲከኞች የራሳቸውን ታሪክ እንዲጽፉ ሲታዘዙ፣ ለእውነትና ለሕሊና መታመንን መጠበቅ ቂልነት ይመስለኛል (በነገራችን ላይ በደቡብ የሚገኙ ብሔሮችን በተመለከተ እየቀረበ ያለው የፈጠራ ታሪክ ‹‹ነፍጠኛ›› የሚሉትን ሥርዓት ብቻ የሚኮንን አይደለም፤ ይልቁንም ወላይታውን ከሲዳማ፤ ሀድያን ከአላባ፤ ጉራጌን ከስልጤ፤ ጉርጂን ከጉጂ… የሚያቃቅር እንደሆነ ፍንጮች እየታዩ ነው) በሶስተኛነት የምጠቅሰው በስውር ሴራ ከዝግመተኛ ሞቱ ጋር እንዲፋጠጥ የተደረገውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍልን ነው፡፡ በ1956 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲግሪ ደረጃ ሥልጠና መሰጠት የጀመረው ይህ ክፍል፣ ላለፉት አምስት አስርታት ከየትኛውም የምሁራን ጥናት በላይ፣ የሀገሪቱን ታሪክ ተሸክሞ ዛሬ ላይ ያደረሰ ታላቅ ባለውለታ መሆኑ አይዘነጋም፡፡
በአናቱም በርካታ አጨቃጫቂና የተደበቁ ታሪካዊ ጉዳዮችን በማጥናት በማስረጃ አስደግፈው ያቀረቡ እና በዚህ አበርክቶአቸው አለም ሳይቀር ያመሰገናቸው፡- ፕ/ር መርዕድ ወ/አረጋይ፣ ፕ/ር ታደሰ ታምራት፣ ፕ/ር ባሕሩ ዘውዴ፣ ፕ/ር መሀመድ ሀሰን፣ ፕ/ር ሽፈራው በቀለ፣ ፕ/ር ሁሴን አህመድ፣ ፕ/ር ሹመት ሲሳይ፣ ዶ/ር ጉልማ ገመዳ፣ ዶ/ር ዳንኤል አያና፣ ዶ/ር ህዝቅኤል ገቢሳ እና መሰል ጉምቱ ምሁራን ከዚሁ ክፍል የተገኙ እንጂ፤ የሥርዓቱ አገልጋይ እንደሆኑት ከላሽ ‹‹ምሁራን›› (የግንቦት ሃያ ፍሬዎች) አለመሆናቸው ማንም ይመሰክርላቸዋል፡፡ በርግጥ ይህ እውነታ የትምህርት ክፍሉን በአገዛዙ መዓት ዓይን እንዲታይ አድርጎ ለዚህ አብቅቶታል ወደሚል ጠርዝ ቢገፋንም፤ አንጋፋውን ተቋም ስልታዊ በሆነ ጥቃት ከአገልግሎት ውጪ ከመሆን ልንታደገው አለመቻላችን ግን ያስቆጫል፡፡ ከዚህ ድርጊት ጀርባ ግዙፉ መንግስታዊ እጅ መኖሩን የሚያሳየን፤ ትምህርት ክፍሉ የተዘጋበት ምክንያት ‹‹የታሪክ ተማሪዎች ስለሌሉ›› የሚል መሆኑ ነው፡፡
ኧረ ለመሆኑ! ከመቼ ጀምሮ ነው ተማሪ በራሱ ቀጥታ ምርጫ ወደሚፈልገው ‹ዲፓርትመንት› የሚገባው? ይህ ጉዳይ በትምህርት ሚኒስቴር ምደባ የሚተገበር መሆኑ ተዘንግቶ ነውን? አሊያም የታሪክ ትምህርት ክፍልን ከጥቂት ዓመታት በፊት የከፈተው መቀሌ ዩኒቨርስቲ ለ2006 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን 300 (ሶስት መቶ) የዘርፉ ተማሪዎች ሲመደቡለት፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው አንድም አለማግኘቱስ ምን ይሆን የሚነግረን? በጥቅሉ እነዚህ የአደባባይ እውነታዎች በብሔር-ብሔረሰቦች ስም ታሪክን ለመቀልበስ የሚደረጉትን በርካታ ማሳያዎች ሳናካትት ሀገሪቱን ታሪክ የሌላት ለማስመሰል የሚሸረበውን ሴራ በጨረፍታም ቢሆን ያመላክታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ታሪክ ያሌለው ሕዝብ ደግሞ ስለሀገር የማይጨነቅ ደንታቢስ መሆኑ አይቀርም፡፡ እናሳ! ከእንዲህ አይነቱ ትውልድ ማን የሚጠቀም ይመስላችኋል? ሀገር ወይስ ህወሓት…
ምዕራፍ ሶስት
‹‹የአባቶች ስንብት›› የሚለው የዚህ ጽሑፍ ርዕሰ-ሃሳብ የተመረጠው፣ ‹‹ሮም በአንድ ጀንበር አልተገነባችም›› እንዲሉ፤ ለዛሬዋ መልክአ-ኢትዮጵያ እልፍ አእላፍ የዘውግ አጥር ያላገዳቸው አባትና እናቶች ከመሪነት እስከ ተራ ወታደርነት በመሰለፍ የማገልገላቸውን ሀቅ ያሳያል በሚል ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በቀላል ምሳሌ ከሚያስረዱ ታሪካዊ ገድሎች መካከልም የዐድዋ ድል አንዱ ነውና እስቲ አሰላለፉን በጨረፍታ እንጥቀሰው፡፡ እንደሚታወቀው ዳግማዊ ምኒልክ ዛሬ የሚወቀሱባቸውን በርካታ አካባቢዎች ሀገር በማቅናት ዘመቻ ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር የቀላቀሉት ከዐድዋው ጦርነት በፊት ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የተቆረጠ ጡት ሐውልት ለመታሰቢያነት በቆመለት አኖሌ የተደረገው ውጊያ ከዐድዋው ድፍን አስር ዓመት የቀደመ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በአካባቢው የጎሳ መሪዎች ከነበሩት መካከል ሱፋ ኩሶ እና ዳሙ ኩሶ በሰላማዊ መንገድ የንጉሱን አስተዳደር ለመቀላቀል ሲወስኑ፤ የተቀሩት ደግሞ ሀሳቡን ውድቅ በማድረጋቸው ጦርነት መቀስቀሱን በርካታ የታሪክ ድርሳናት አትተዋል፡፡ እንዲሁም ወደ ሌቃ ነቀምት፣ ሌቃ ቀለም፣ ጅማ፣ ሀድያ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ወለጋ፣ ከፋ፣ ሐረር… የተደረጉት ዘመቻዎች በሙሉ ከዐድዋው በፊት ነው፡፡ እዚህ ጋ የሚነሳው ቁልፍ ጥያቄም፡- በዚህ መልኩ ከድሉ በፊት የማዕከላዊ መንግስት አካል የሆኑት የነዚህ አካባቢ ነዋሪዎች በዐድዋው ጦርነት ከምኒሊክ ጎን እንዲሰለፉ ያስቻላቸው ምስጢር ምንድር ነው? የሚለው ነው፡፡ …መቼም ለዚህ ጥያቄ የህወሓት የታሪክ ባለሙያዎች ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠየቁ ‹እንደ ደርግ ዘመኑ የብሔራዊ ውትድርና በግዳጅ እንዲዘምቱ ስለተደረገ› ብለው መቧለታቸው አይቀርም፡፡ አሊያማ ‹‹ምኒሊክ ኤርትራ ድረስ ዘልቀው ለምን አልገቡም›› በማለት የሚከስሰው ድርጅታቸው፤ ወደ ደቡብ እና ኦሮሚያ ያደረጉትን ዘመቻ ‹‹የቅኝ ግዛት›› ብሎ በድፍረት ሲኮንን፣ ምላሻቸው ዝምታ ባልሆነ ነበር፡፡
ግና፣ እውነት እውነት እላችኋለሁ፡- በርካታ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች እና የማንነት ጭፍለቃዎች የማንክደው የታሪካችን አካል ቢሆኑም፣ ሀገር በመታደግ ዘመቻው በመሰለፍ ዛሬ ኢትዮጵያችንን-ኢትዮጵያ ያደረጓት ከራስ አሉላ አባነጋ እስከ ራስ ጎበና ዳጬ፤ ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ እስከ ፊታውራሪ ገበየሁ፤ ከራስ መኮንን እስከ አሚር አብዱላሂ፤ ከደጃዝማች ባልቻ ሰፎ እስከ ራስ መንገሻ ዮሐንስ… በዐድዋ የፈጸሙት አኩሪ ጀብዱ ነው፡፡ በአናቱም እነዚህን ጀግና አባቶች ለአንድ ዓላማ አንድ ግንባር ያዋላቸው ሀገራዊ አጀንዳ እንጂ፣ ንጉሳዊ ፍቅር ወይም አድርባይነት አለመሆኑ ከማናችንም ባይሰወርም፤ በህወሓት የኑፋቄ ስብከት ተነድተን በአንድነት የሚያቆሙንን መስተጋብሮች አፍርሰን፣ የተናጥል ማንነትን የምንሻ ከሆነ፣ አባቶቻችንን አሰናብተን፣ አዲስ ማንነት ፈጥረን ወደ ገደሉ አፋፍ መገፋታችን የጊዜ ጉዳይ ብቻ ከመሆን የሚታደገው አለመኖሩን ማስታወስ እወዳለሁ፡፡
በ1928ቱ ዳግማዊ የጣሊያን ወረራም ቢሆን የታየው ሀገር የመታደግ ትብብር እና መነቃቃት፣ በአኖሌ ሐውልት በኩል ሊተላለፍ ከተፈለገው ኢህአዴጋዊ የጥላቻና የበቀል ፖለቲካ የተሻገረ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ከጃጋማ ኬሎ እስከ ዘርአይ ደረስ፤ ከአቡነ ጴጥሮስ እስከ አብረሀ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም፤ ከበላይ ዘለቀ እስከ ራስ ስዩም መንገሻ፤ ከደጃዝማች መሻሻ እስከ ራስ ደስታ ዳምጠው…. እያልን ዘርዝረን የማንዘልቃቸው የሀገር ባለውለታዎች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ሆኖም ሁሉንም መጥቀስ ባይቻልም ወረራውን በመፋለም ታሪካቸውን በደማቁ ቢጽፉም፣ የአበርክቶአቸውን ያህል ያልተዘመረላቸው ሁለት ጀግኖችን ለአብነት አስታውሳለሁ፡፡ አብዲሳ አጋ እና አብቹ፡፡
ሰኔ 7 ቀን 1911 ዓ.ም ወለጋ ነጆ ከተማ የተወለደው አብዲሳ አጋ ተገቢውን ክብር አለማግኘቱ አከራካሪ አይመስለኝም፡፡ ይህ ሰው በጠላት ጦር ተማርኮ ወደ ጣሊያን ሀገር ከተወሰደ በኋላ በናፖሊ ከተማ ከሚገኘው አኞኖ እስር ቤት አንስቶ፣ ቦጆያሊ፣ ካምቦ አንተርናቴ እና ካራ ቤኜር በተባሉ ማጎሪያዎች ከፍተኛ ስቃይ ደርሶበታል፡፡ ይሁንና በእስር ላይ በነበረበት ጊዜያት ካጋጠሙት ሁሉ የሚያስደንቀው ከለታት በአንዱ ቀን፣ ከእስረኛ ጠባቂ ወታደሮች አንዱ በጫማው ሲረግጠው፤ በምላሹ በቡጢ መትቶ መሬት ላይ መጣሉን ተከትሎ፣ በርካታ ዘቦች ተረባርበው ከፍተኛ ድብደባ ካደረሱበት በኋላ፣ ከፎቅ ላይ በጭካኔ ወርውረውት ለጉዳት መዳረጉን አስመልክቶ በአንድ ወቅት ለኢትዮጵያ ሬዲዮ እንዲህ በማለት የገለፀው ነበር፡-
‹‹እኔስ ማን ነኝና? ኢትዮጵያውያን ለክብራችን ከርሱ የበለጠ ስሜት እንዳለን ገና አልተገነዘበውምና ከእስር ውጪ በነበረ እጄ ትምህርት እንድሰጠው ኢትዮጵያዊነቴ አስገደደኝ፡፡ …በዚያን ጊዜ የደረሰብኝን የዚያን ቁስል ጠባሳ እስከዛሬ ሳይ ሀዘንና ሐሳብ ውስጥም እገባለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ፡፡››
ለኢትዮጵያዊነቱ ቅድሚያ የሰጠው ሀገር ወዳዱ አብዲሳ አጋ፣ የደቡብ ጣሊያን ተራሮች በአድናቆት የተመለከቱትን ጀብዱ የፈፀመው ከባዕድ ሀገር እስር ቤት ከዩጎዝላቪያዊው መቶ አለቃ ጁሊዮ ኢታችክ ጋር ካመለጠ በኋላ ነበር፡፡ አብዲሳና ጓደኛው በዚህ መልኩ ነፃነታቸውን አውጀው ብቻ ተሸሽገው አልተቀመጡም፡፡ ይልቁንም የተለያዩ ሀገራት ተወላጆችን አስተባብረው እስር ቤቶችን በመስበር ሐበሾችን ጨምሮ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ እና የዩጎዝላቪያ ሰዎችን እስከማስፈታት አኩሪ ጀግንነት ፈፅመዋል፡፡ እንዲሁም የቃል ኪዳኑ ጦር የሮማ መንግስትን እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ፣ ለሁለት ዓመታት ያህል በጣሊያን ተራሮች ላይ ጥቂት የማይባሉ ሀገራት ዜጐችን እየመራ ከፋሽስት ወታደሮች ጋር በአደረጋቸው በርካታ ውጊያዎች ላይ እጅግ በጣም አስገራሚ ጀብድዎችን አከናውኗል፡፡ ለዚህ ገድሉም ከቃል ኪዳኑ የጦር አዛዦች የአድናቆት እና የምስጋና ሰርተፍኬቶች ተበርክተውለታል፡፡ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀም በኋላ ዜግነቱን እንዲቀይር እንግሊዛውያን ላቀረቡለት ጥያቄ እንደሚከተለው መመለሱን ከላይ በጠቀስኩት ቃለ-መጠይቅ ላይ መናገሩ ይታወሳል፡-‹‹የሀገር ፍቅርና የራስ ጥቅም ምን እንደሆነ ስለማውቅ ጥያቄውን አልተቀበልኩም፡፡ ወደሀገሬም ገባሁ፡፡››
እነሆም ‹‹ብሶት›› የወለደው ኢህአዴግ፣ አብዲሳ ዋጋ የከፈለላትን ኢትዮጵያ፣ በአንድ ዘውግ የበላይነት የተመሰረተች አድርጎ በመቀስቀስ ለእርስ በእርስ ፍጅት ጡንቻችንን እንድናፍታታ እያመቻቸ ነው (ይህ የጀግናው ታሪክ ‹‹ተራሮቹን ያንቀጠቀጠ ቅፅ 5›› መጽሐፍ ላይ በስፋት የቀረበ መሆኑን አስታውሳለሁ)፡፡
ሌላኛው የዛን ዘመን ያልተዘመረለት ጀግና የሰላሌው አቢቹ ነው፡፡ የአቢቹ ታላቅ ገድል ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የተሰማው፣ አዶልፍ ፓርለሳክ በተባለ የቼክ ሪፖብሊክ ተወላጅ ተጽፎ፣ በተጫነ ጆበሬ መኮንን ‹‹የሃበሻ ጀብዱ›› በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ በተተረጎመው መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ በሰላሌ የወረጃርሶ ፊት-አውራሪ የነበሩ ሁለት ታላላቅ ወንድሞቹን ተከትሎ በ16 ዓመቱ ሀገሩን ከወራሪ ለመከላከል ስለዘመተው አቢቹ፣ ጻሐፊው ‹‹እነሆ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ፈረንሳይ ሀገር ለከፍተኛ ትምህርት ተጓዥ ነበር›› ሲል ገልፆአል፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረም በኋላ አንደኛው ወንድሙ በክብር ሲሰዋ፤ ሌላኛው ደግሞ የደረሰበት በመጥፋቱ ትንሹ ልጅ ከዋናው ሠራዊት ተገንጥሎ፣ ወደ 200 የሚጠጉ ትዳር ያልመሰረቱ ጎበዝ ተዋጊዎችን ብቻ አስከትሎ ጠላትን በመብረቃዊ ፍጥነት መድረሻ ማሳጣቱ ተተርኳል፡፡ በወቅቱ ንጉሠ ነገሥቱ የሰላሙ መንገድ ገና አልተቋጨም በሚል የኢትዮጵያ ጦር ከመከላከል በቀር እንዳያጠቃ ትዕዛዝ አስተላልፈው ስለነበር፣ አቢቹ የሚፈፅማቸው ጀብዶችን አቁሞ ወደእናት ጦሩ እንዲመለስ ግፊት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፡፡ በዚህም ንዴት የመንግስት ጦር እንዲዘምትበት ስለመወሰናቸው የሰላሌው ደጃዝማች አበራ መልክተኛ ልኮ ስላሳወቀው፣ ድንገት አቢቹ ወደ ጦሩ ሠፈር በመምጣት ከአቋሙ ፍንክች እንደማይል መግለፁን መጽሐፉ ይተርክልናል፡-
‹‹ደጃዝማች፣ ገና ከሰላሌ ስንነሳ ታማኝነቴን በምኒሊክ ስም ቃል የገባሁት ላንተ እንጂ ለሽማግሌዎቹ ወይም ለንጉሡ አይደለም፡፡ እኔ ንጉሥ አይደለሁም፤ ተራ ወታደር እንጂ፡፡ እና እኔ ሁለት ሶስት ወር ደሴ ተጎልቼ ጣሊያኖች እጄን እስኪይዙኝ አልጠብቅም፡፡ ላንተ ግን አሁንም በምኒሊክ ስም፣ በምኒሊክ አምላክ በድጋሚ ቃሌን እሰጣለሁ፡፡ …ተመለስ ላልከው ግን፣ የት ነው የምመለሰው? ምንስ መመለሻ ቤት አለኝና? እዚህም እዚያም እሳት እየነደደ እንዴት ቁጭ ልበል? …የሀገሬ ታማኝ ወታደር እንደሆንኩ አስረዳልኝ፡፡›› (234)
ከዚህ በኋላም ጦሩን፡- በሀብቶም የሚመራ የሀማሴን (የኤርትራ) ልጆች ጦር፣ በተስፋፅዮን የሚመራ የትግራይ ልጆች ጦር፣ በጋሹ የሚመራ የጎጃም ልጆች ጦር እና በወርቁ የሚመራ የሰላሌ ልጆች ጦር በማለት ከፋፍሎና በዕዝ አዋቅሮ ሲያበቃ፤ ጠላት ካምፕ ድረስ ዘልቆ በመግባት አያሌ ጀብዶችን አከናውኗል፡፡ መላው ዘማች ሠራዊት ከእነ አዛዡ ‹‹የልጁ ጦር›› እያለ አድናቆቱን ሲገልፅለት፤ ንጉሡ ራሳቸውም ‹‹ይቺ አንድ ፍሬ ደጃዝማች ከኛም በላይ ትልቅ ጀብዱ እየሰራች እንደሆነ እንሰማለን›› (288) እስከማለት ተገድደዋል፡፡ በዘመቻው ላይ የተሳተፉ አዝማሪዎችም ከዋናው ባለታሪክ ተገንጥሎ ዛሬም ድረስ ተወዳጅ መሆን በቻለች ዜማ እንደሚከተለው ያወድሱት እንደነበር የቼኩ ሰው ነግሮናል፡-
‹‹አቢቹ ደራ ደራ
አቢቹ ደራ ደራ››
አቢቹ ደራ ደራ››
የመጽሐፉ ደራሲ በዛው በጦር ሜዳ አንድ የከንባታ ልጅ አጫወተኝ ብሎ ያሰፈረው ደግሞ እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹የከንባታው ጦር በጣሊያን ሠራዊት ተከቦ፣ መውጫው ጠፍቶት፣ አጥፍተህ ጥፋ አይነት ውጊያ ላይ እያለ ከየት መጡ ሳይባል እነዚያ የአቢቹ ፈጥኖ ደራሽ ደቦል አንበሶች ከጣሊያኑ ጦር ብብት ውስጥ ገብተው ሲኮረኩሩት፣ ደመሰስኩ ብሎ የሚኩራራው የጣሊያኑ ጦር ሳያስብ አደጋ ደርሶበትና በተራው ሲያፈገፍግ የከንባታውን ጦር ከዚያ ካለቀለት ውጊያ ውስጥ እነአቢቹ መንጥቀው አወጡት፡፡›› (289-290)
‹‹የከንባታው ጦር በጣሊያን ሠራዊት ተከቦ፣ መውጫው ጠፍቶት፣ አጥፍተህ ጥፋ አይነት ውጊያ ላይ እያለ ከየት መጡ ሳይባል እነዚያ የአቢቹ ፈጥኖ ደራሽ ደቦል አንበሶች ከጣሊያኑ ጦር ብብት ውስጥ ገብተው ሲኮረኩሩት፣ ደመሰስኩ ብሎ የሚኩራራው የጣሊያኑ ጦር ሳያስብ አደጋ ደርሶበትና በተራው ሲያፈገፍግ የከንባታውን ጦር ከዚያ ካለቀለት ውጊያ ውስጥ እነአቢቹ መንጥቀው አወጡት፡፡›› (289-290)
በማይጨው ጦርነትም ቢሆን በምኒሊክ ስም ምለውና ፎክረው ለሀገር አንድነት ከወደቁ ስም የለሽ ጀግኖቻችን መካከል የሰላሌ ተወላጆችን በተመለከተ ከመጽሐፉ ላይ አንድ ሃሳብ ልጥቀስ፡-
‹‹በዚህ ጦርነት ሶስት አራተኛው የሰላሌዎቹ አሉ የሚባሉት ቆራጦች፣ ጀግኖቹና ደፋሮቹ ልጆች ከማይጨው የጦር ሜዳ ከአምባ በሆራ አልተመለሱም፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስ ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው በየምሽጉ ወድቀዋል፡፡›› (296)
እነሆም ላለፉት ሁለት አስርታት ከራስ ጎበናና ባልቻ ሶፎ፤ ከአብዲሳና አቢቹ ኢትዮጵያዊነት ይልቅ የዘውግ ማንነት ቅድሚያ ተሰጥቶት፣ አባቶችን ከታሪክ ባህረ-መዝገብ የማሰናበት ተልዕኮው ከጫፍ እየደረሰ ነው፡፡ በርግጥም ይህች ሀገር ከሰቅጣጭ ሞት ፊት ደጋግማ በቆመችበት ጊዜ ሁሉ፣ በመስዋዕትነት የታደጓት እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውያን አባቶች ቢሆኑም፣ ዛሬ ልጆቻቸው በማንነት ብያኔ እንዲነጣጠሉ እየተገፉ ስለመሆኑ በድፍረት መናገር እችላለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ የሥርዓቱ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች የህወሓት መጠቀሚያ የሆነው ኦህዴድን ያህል፣ በዚህን መሰሉ የኑፋቄ ታሪክ ተወስውሰው ጥላቻን ሲሰብኩ፤ ልዩነትን ሲቀሰቅሱ መመልከቱ ምን ያህል ከአባቶቻችን እንደተነጠልን ያረዳናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ዘጽአት…
(ከ2 ሺህ ዓመት በፊት ቀይ ባሕርን ተሻግረው፣ ሞትን ተራምደው፤ ከግብፃውያን የባርነት ቀንበር ነፃ የወጡ ዕብራውያንን በተመለከተ ቅዱስ መጽሐፍ በ‹‹ኦሪት ዘጽአት›› ላይ በስፋት ያትታል)
ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያችን፣ የአገዛዙን የሥልጣን ዕድሜ ለማረዘም ሆን ተብሎ ዘውግን ሰበብ አድርጎ ለተቀነባበረው የመበታተን አደጋ ተጋልጣለች፡፡ እናም ይህንን ሀገሪቷን በደም ውቅያኖስ የማጥለቅለቅ አቅም ያለው ከባድ ችግር ለማምከን፣ በቅድሚያ ከተጫነብን የታሪክ ሒሳብ ማወራረድ መንፈስ ሙሉ ለሙሉ ልንላቀቅ ይገባል፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት የአንድ ሀገር ሕዝብን በማዕከላዊ መንግስት ሥር ወደ አንድነት ለማምጣት የተደረገውን ታላቅ ተጋድሎ አኮስሶ፣ ተያይዘው የተከሰቱ ዘመኑና ነባራዊ ሁኔታዎች የፈጠሯቸው ስህተቶችን ነጥሎ ማስጮሁ፣ ‹‹ዜግነት-ኢትዮጵያዊ›› በሚል ፓስፖርት ከሀገር ሀገር የሚዘዋወሩ የግንባሩንም ሆነ የተቃዋሚውን ጎራ ልሂቃን የማንነት ቀውስ ከትቶ ከንቱ እንዳያስቀራቸው እሰጋለሁ፡፡ በአናቱም የህወሓት፣ የኦሮምኛና አማርኛ ቋንቋ ክንፍ ሆነው የሚያገለግሉት ኦህዴድና ብአዴንም በትውልድ ፊት በ‹አድርባይነት› የሚያስከስስ ታሪክ ተጋርተው እስከመጨረሻው በሕዝባዊ ማዕበል እስኪጠረጉ ድረስ መጓዛቸው በምንም መልኩ ስርየት የማያገኝ ጥፋት እንደሆነ በአፅንኦት ላሳስባቸው እፈልጋለሁ፡፡
ስለሆነም ከሀገሪቱ ቀጣይ ሕልውና ፊት የተጋረጠውን ይህን የመበታትን አደጋን ያዘለ የእርስ በእርስ ግጭትን ተሻግሮ፣ የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለማቆየት ብሎም ልጆቿ በዕኩልነት ይኖሩባት ዘንድ ለማመቻቸት፣ ዘመኑን ካለፈ ታሪክ ይልቅ ጊዜው በሚፈቅደው የሠለጠነ ፖለቲካ መዋጀት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ በይበልጥ ወደ ፍጥጫው እየተገፉ ያሉት ሰፊ ቁጥር ያላቸው የኦሮምኛና አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከአኖሌ መታሰቢያም ሆነ፤ በቅርቡ በተማሪዎች የስፖርት ውድድር ላይ በባሕር ዳር ስታዲዮም ከተሰማው ዘውግ-ተኮር ነውረኛ ቅስቀሳ ጀርባ ያደፈጠውን ዕኩይ የፖለቲከኞች ሴራ ለመበጣጠስ ፊት-አውራሪ መሆን ይኖርባቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ የተቀደሰ ተግባር ከትውልድና ከታሪክ ተወቃሽነት ብቻ ሳይሆን ከዘገየ ፀፀትና መብከንከንም መታደጉ በግልፅ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች›› በሚል ርዕስ ባለፈው ዓመት ባሳተመው መጽሐፍ ላይ በግንባር ቀድምትነት ኦሮምኛ፣ አማርኛ እና ትግርኛ ተናጋሪዎች ሀገሪቱን ከአይቀሬው ሞት ይታደጉ ዘንድ በማለት ያሰፈረውን ለዘጽአት ሃሳብ ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ እንደሚከተለው እጠቅሳለሁ፡-
ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች›› በሚል ርዕስ ባለፈው ዓመት ባሳተመው መጽሐፍ ላይ በግንባር ቀድምትነት ኦሮምኛ፣ አማርኛ እና ትግርኛ ተናጋሪዎች ሀገሪቱን ከአይቀሬው ሞት ይታደጉ ዘንድ በማለት ያሰፈረውን ለዘጽአት ሃሳብ ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ እንደሚከተለው እጠቅሳለሁ፡-
‹‹በተቃዋሚው ጎራ፣ ብዙ ሲንቀሳቀስ የማላየው የኦሮሞና የአማራ ልሂቃን ፖለቲካ ነው፡፡ የሁለቱም ልሂቃን ፖለቲካ በዋናነት በሁለት ጫፎች ላይ ቆሞ ገመድ ከመጓተት ወደ መሐል መጥቶ የጋራ ዲሞክራቲክ አጀንዳ መቅረጽ አልተቻለውም፡፡ ብዙዎቹ ሂሳብ የመወራረድ ፖለቲካን የዛሬ 30 እና 40 ዓመታት ብቻ ሳይሆን፤ የዛሬ 130 እና 140 ዓመታት በፊት የነበረውም ጭምር እንተሳሰብ የሚሉ ይመስሉኛል፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን ዋናው ችግራቸው የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ ለመቅረጽ ከመጣር ይልቅ ለብቻ የሚደረገው ትግልን የመንግስተ-ሰማያት አስተማማኝ መንገድ አድርገው ማምለካቸው ነው፡፡ የአማራው ልሂቃን በሽታቸው በዋናነት በአማራ ልሂቅ የተፈጠረች የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንደዛው ትቀጥል ነው፡፡ እምነታቸው መቀጠልም ትችላለች ነው፡፡ …በመጽሐፌ መደምደሚያ ላይ ለታሪክም ለሕዝብም አስቀምጬ ማብቃት የምፈልገው መሰረታዊ ነጥብ፣ አብዛኛው የትግራይ ልሂቃን ‹ሥልጣን ወይም ሞት› ብለው ሥልጣን ላይ የሙጥኝ እስካሉ ድረስ፤ አብዛኛው የአማራ ልሂቃን በአፄዎች ዘመን የነበረውን የበላይነት መልሼ አገኛለሁ ብሎ የሚገፋውን የሕልም ፖለቲካ እስካልተወ ድረስ፤ ብዙሃኑ የኦሮሞ ልሂቅ ኦሮሚያን ለብቻ የማውጣቱን ሕልም እስካልተወ ድረስ ሀገራችን ከአደጋ ቀጠናና ቀውስ የምትወጣ አይመስለኝም፡፡›› (ገፅ 261፣ 262 እና 263)
እንደ ዶ/ር መረራ ያሉ ልሂቃን ሀገርና ህዝብን ለመታደግም ሆነ አባቶቻችንን አሰናብተን ወደ እልቂት እንዳናመራ ለሚያራምዱት ከታሪክ ጥላቻ የፀዳ ሃሳብ ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌ አክብሮቴን እገልፃለሁ፡፡ ይህንን አጀንዳም በቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ዜማ ጥቂት ስንኞች እቋጨዋለሁ፡፡
‹‹ዘጽአት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ
ባሕሩን የሚያሻግር አንድ ሙሴ ይዞ
ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵ ያ ትንሳኤ
በአንድነት ከገባን የፍቅር ሱባኤ!››
ባሕሩን የሚያሻግር አንድ ሙሴ ይዞ
ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵ ያ ትንሳኤ
በአንድነት ከገባን የፍቅር ሱባኤ!››
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen