April 24/2014
ፖለቲካ አንድ ሰው በአንድ ሃገር ወይም ህብረተሰብ ያለው ስርዓት ወይም የመንግስት ፖሊሲዎችንና አገዛዝን በተጨባጭ በመተንተንና በመገምገም ከአመለካከቱና ከዕምነቱ ጋር አገናዝቦ በመደገፍ ሥርዓቱ ወይም ሁኔታው እንዲቀጥል ለማድረግ ወይም በመቃወም ሥርዓቱ ወይም ሁኔታው እንዲቀየር ለማድረግ አቋም ይዞ አቋሙንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀስበት የሥራ ዓይነት (Business) ነው፡፡
ስለዚህም ትክክለኛ ፖለቲከኞች የመንግስት ሥልጣን የያዘውም አካልም ሆነ ያልያዙት እና ሌላ አማራጭ ፖሊሲ የሚያራምዱ የፖለቲካ ሃይሎች ወይም ፖርቲዎች የሚያራምዱትን ፖሊሲዎች ከመቃወምና ከመደገፍ በፊት ስለ ፖሊሲዎቻቸውና አማራጭ ሃሳቦቻቸው ተጨባጭ መረጃዎችንና እውቀትን ሊጨብጡና እነዚህንም መረጃዎች ለድጋፍም ሆነ ለተቃውሞ አቋማቸው መነሻ ሊያደርጉ ይገባል ማለት ነው፡፡ ካለተጨባጭ መረጃ እና እውቀት የሚካሄድ ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ ግን ተራ ወሬ ወይም አሉባልታ እንጂ ትክክለኛ ፖለቲካ ሊሆን አይችልም፡፡ በአሉባልታ የሚመራ ወይም የሚገፋ ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ ደግሞ አስመሳይ ፖለቲከኛ እንጂ እውነተኛ ፖለቲከኛ ሊሆን አይችልም፡፡
ምሁርነት ደግሞ በተለያዩ የእውቀት ዘርፎች ጥልቀት ያለው መረጃ የማግኘት የመተንተንና የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ በጥልቅ ጥናት ላይ የተመሰረቱ የመፍትሄ ሐሳቦችን ለማፍለቅ በመብቃት የሚደረሰበት ክቡር የሰው ልጅ ስብእና እንጂ በዘፈቀደ መሰረተቢስ አሉባልታ በመፃፍና በማውራት የሚገኝ ስብእና አይደለም፡፡
እነዚህን ሁኔታዎች ለመንደርደሪያነት ለመግለጽና በዚህ ጉዳይ ላይ የራሴን አስተያየት እንድጽፍ ያነሳሳኝ ጉዳይ ኘሮፌሰር መሳይ ከበደ በመድረክ ላይ መሰረተቢስ ኘሮኘጋንዳ በጥላቻ ስሜት ተነሳስተው ካለተጨባጭ መረጃ ለማሰራጨት ‹‹ መድረክ የፖለቲካ አስመሳይነት መጨረሻ?›› በሚል ርእስ ሚያዝያ 10 ቀን 2006 ዓ.ም በታተመው ‹‹ ነገረ ኢትዮጵያ ›› በሚባል ጋዜጣ የጻፋትን ከእውነት እጅግ የራቁና ከተጨባጩ የመድረክ አቋም ጋር ምንም ግኙኝነት የሌላቸውን መሰረተቢስ የኘሮፓጋንዳ አስተያየቶቻቸውን ስላነበብኩ ነው፡፡ እኒህ ሰው በአካዳሚክ ትምህርታቸው እስከኘሮፌሰር ማዕረግ ድረስ የደረሱ መሆናቸውንና በእድሜያቸውም አንቱ በሚያሰኝ እድሜላይ የሚገኙ ሰው መሆናቸውን ስረዳ ደግሞ ተጨባጭነት የሌላቸውን ወሬዎች በጥላቻ ስሜት ተነሳስቶ ማሰራጨታቸው እጅግ አስገርሞኛል፡፡ ይህም በጥላቻ ስሜት ተነሳስቶ ፖለቲካን ማራመድ ምን ያህል ሰውን ከመልካም ስብእና ውጪ እንደሚያደርግ እንድረዳ አድርጎኛል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ከላይ በተጠቀሰው ጽሁፋቸውም ኘሮፌሰር መሳይ ያነሱዋቸውን አንዳድ ነጥቦች ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማነጻጸር ለአንባቢያን ለማቅረብ እፈልጋለሁኝ፡፡ ኘሮፌሰሩ መድረክን ባጥላሉበት ጽሁፋቸው አጽኖት ሰጥተው የገለጹት ‹‹የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል መብት›› ነው፡፡ የመገንጠል መብትን ስራ ላይ ለማዋልና ለማራመድ የተነሱትን ሐይሎች ከፖለቲካ ኘሮግራማቸውና ከሚያራምዱት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎቻቸው ተነስተውና ለይተው በማቅረብ ይህንን በማውገዝ ኘሮፌሰር መሳይ ቢጽፋ ኖሮ ይህ መብታቸው መሆኑን ከመቀበሌም በላይ በአቋም ደረጃም ጭምር እኔም በደገፍኳቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም እኔም የመገንጠልን ፖለቲካ ስቃወም የኖርኩኝና አሁንም የምቃወም ኢትዮጵያዊ ነኝና፡፡ ከዚህም ሌላ መድረክ በፖለቲካ ኘሮግራሙም ሆነ በተግባራዊ እንቅስቃሴው ያሳያቸውን ተጨባጭ ነገሮች አንስተው የራሳቸውን አስተያየት ቢሰጡ ኖሮ መብታቸውና ተቀባይነትን የሚያገኝ ይሆን ነበር፡፡ እጅግ የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ግን ይህንን እስከመገንጠል አቋም የሚያራምዱት የብሄርም ሆኑ የሕብረብሄራዊ ፖርቲዎች የትኞቹ እንድሆኑ እንኳን በአግባቡ ሳይለዩ በተለይም በፖለቲካ ኘሮግራሙ መገንጠልን እንደሚቃወምና የኢትዮጵያ አንድነትን በጽናት እንደሚደግፍ በግልጽ ያረጋገጠውን መድረክን የዚህ አላማ አራማጅ የሆነ ይመስል የትችታቸው ኢላማ አድርገው መሰረተቢስና አሳሳች ኘሮኘጋንዳ ማሰራጨታቸው ነው፡፡
መድረክ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነትን በሚመለከት በኘሮግራሙ አንቀጽ 5 የሚከተለውን ሃሳብ በግልጽ አስፍሮአል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ዳር ድንበር፣ ነፃነት፣ አንድነትና ሉአላዊነት የተጠበቀና የተከበረ ይሆን ዘንድ በጋራ እንቆማለን፡፡ እያንዳንዱ ብሔርብሔረሰብና ህዝብ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር፣ ነፃነት አንድነትና ሉአላዊነት የሌሎች ብሔርብሔረሰቦችን መብት መከበርን ጨምሮ የጋራ ለሆኑት ጥቅሞችና እሴቶች እንዲቆሙ እንታገላለን፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ለሚደቀኑ ፈተናዎች መፍትሔው በአንድነት ዙሪያ ሆኖ ድሞክራሲን ማስፈን እንጂ መገንጠል እንዳልሆነ እናምናለን፡፡ በዚህ መሰረት ሁላችንም ለኢትዮጵያ አንድነት እና ብሔርብሔረሰቦች መብት መከበር በጽናት እንቆማለን፡፡›› ይላል የመድረክ መስራች ድርጅቶች በጋራ ያጸደቁት ኘሮግራም፡፡
መድረክ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነትን በሚመለከት በኘሮግራሙ አንቀጽ 5 የሚከተለውን ሃሳብ በግልጽ አስፍሮአል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ዳር ድንበር፣ ነፃነት፣ አንድነትና ሉአላዊነት የተጠበቀና የተከበረ ይሆን ዘንድ በጋራ እንቆማለን፡፡ እያንዳንዱ ብሔርብሔረሰብና ህዝብ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር፣ ነፃነት አንድነትና ሉአላዊነት የሌሎች ብሔርብሔረሰቦችን መብት መከበርን ጨምሮ የጋራ ለሆኑት ጥቅሞችና እሴቶች እንዲቆሙ እንታገላለን፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ለሚደቀኑ ፈተናዎች መፍትሔው በአንድነት ዙሪያ ሆኖ ድሞክራሲን ማስፈን እንጂ መገንጠል እንዳልሆነ እናምናለን፡፡ በዚህ መሰረት ሁላችንም ለኢትዮጵያ አንድነት እና ብሔርብሔረሰቦች መብት መከበር በጽናት እንቆማለን፡፡›› ይላል የመድረክ መስራች ድርጅቶች በጋራ ያጸደቁት ኘሮግራም፡፡
የመድረክ አቋም መገንጠልን የሚቃወምና ለአንድነት በጽናት የቆመን እንዲሆን መድረክን የመሰረቱት አባል ድርጅቶች ተስማምተው ያጸደቁት ሲሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብና የአለም ህብረተሰብም እንዲያውቁት ለማድረግ በጋራ ኘሮግራማቸው በግልጽ ማስፈር ብቻ ሳይሆን ከመድረክ ምስረታ በኋላ ወደ መድረክ ለመቀላቀል የሚፈልጉ ፖርቲዎችም ይህንኑ አቋም መቀበላቸውን በጠቅላላ ጉባኤአቸው አማካኝነት በግልጽ እንዲያረጋግጡ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደውነቱ ከሆነ በአሁኑ ወቅት አንድም የመድረክ አባል የሆነ የብሔርም ሆነ ሕብረብሔራዊ የሆነ ፖርቲ የብሔርብሔረሰቦችን መብት እስከመገንጠል የሚል ሐሳብ በኘሮግራሙ ያስቀመጠም ሆነ የሚያራምድ በፍጹም የለም፡፡ መድረክ የአባልነት ጥያቄ የሚያቀርቡለትን ፖርቲዎች ኘሮግራም ፈትሾና ገምግሞ ከራሱ አቋም ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ የማይቃረን ኘሮግራም ያላቸው መሆኑን እያረጋገጠ ነው በአባልነት እየተቀበለ ያለው፡፡
እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ኘሮፌሰር መሳይ በመድረክ ላይ ካላቸው የጥላቻ ስሜት ተነሳስተው በመድረክም ሆነ በአባል ድርጅቶቹ አላማና ኘሮግራም ላይ የሌለውን እስከመገንጠል አቋም ከመድረክ ጋር በማያያዝ መድረክን ‹‹የአስመሳይነት ፖለቲካ መጨረሻ›› በሚለው ጹሁፋቸው መሰረተቢስ በሆነ ኘሮፓጋንዳቸው የእስከመገንጠልን ትችት ማቅረባቸው የትክክልኛ ምሁርነትም ሆነ ፖለቲከኛነት ስብእናን የሚገልጽ አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ ተግባራቸው እራሳቸው አስመሳይና ህዝብን የሚያሳስት ውዥምብር ነዥ መሆናቸውን የሚያጋልጥ ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህም ኘሮፌሰሩ ለኢትዮጵያ አንድነት ተቆርቋሪ ከሆኑ መጀመሪያ የመገንጠል መብት አራማጅ ፖርቲዎች እነማን እንደሆኑ መረጃ ማሰባሰብ እና ምሁራዊ ትንተና መስጠት እንጂ በመድረክም ሆነ በአባል ድርጅቶች ኘሮግራምና አላማ ውስጥ የእስከመገንጠል ሃሳብ ሳይኖር በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በመድረክ ላይ ጣትን መቀሰር እና አሉባልታ መንዛት ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ መንከራተት ነውና ለትዝብት የሚያጋልጥ ፋይዳ ቢስ ድካም ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ተግባራቸው በመሰረተቢስ ኘሮፓጋንዳ በመድረክ ላይ ጥላቻን መግለጽ ከሆነ ደግሞ የአስመሳይ ፖለቲከኛነት እና ምሁርነት ተጨባጭ እና ግልጽ ምሳሌ መድረክ ሳይሆን እራሳቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከርሳቸው በላይም እሳቸው ላነሱት ያስመሳይ ፖለቲከኛነት ጥሩ ምሳሌ ሊኖር አይችልም ማለት ነው፡፡
ኘሮፌሰሩ በዚሁ ጽሁፋቸው ስለመገንጠል መብት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንደተናገሩ የጠቀሱ ሲሆን ዶ/ር ነጋሶ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የመድረክ አባልም ሆኑ አመራር አይደሉም፡፡ ሊቀመንበር የነበሩትም በአሁኑ ወቅት ከመድረክ በዲስኘሊን ምክንያት ታግደው የሚገኘውና እርሳቸው ጠንካራ ፖርቲ ብለው ያወደሱት የአንድነት ፖርቲ እንደነበሩ እራሳቸውም በጽሁፋቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ እሳቸው ያነሱትን ሐሳብ ከመድረክ ላይ በመለጠፍ መድረክ የዶ/ር ነጋሶን የግል አስተያየት እንደ አቋም ይዞ የሚከተል ይመስል መድረክ የማይደግፈውንና የሚቃወመውን ሃሳብ በመድረክ ላይ በመለጠፍ አሉባልታ ለማሰራጨት መነሳታቸው በመድረክ ላይ ያላቸውን የጥላቻ ስሜትና ኢ ምክንያታዊነታቸውን ብቻ ነው የሚያሳየው፡፡ ይህም የዶ/ር ነጋሶ የግል አስተያየትና የመድረክ አቋም የተለያዩ መሆናቸውን ከመድረክ ኘሮግራም ተነስተው መረዳት የሚችሉ ሆነው ሳለ ሆን ብለው በክፋት ስሜት ያሰራጩት ማደናገሪያ ነው፡፡
ሌላው ኘሮፌሰር መሳይ ከላይ በተጠቀሰው ጽሁፋቸው ሆነ በተለያዩ ወቅቶች በጻፋቸው ጽሁፎች የሚያነሱት ነጥብ በአሁን ወቅት በሃገራችን የሚገኙትን ብሔርብሔረሰቦች ‹‹ጎሳዎች›› ናቸው ብለው በመፈረጅና በኢትዮያ አንድነት ጥላ ስር የብሔርብሔረሰቦችን እኩልነት እና መከባበርን ለማረጋገጥ የሚታገሉትን ፖርቲዎች የመገንጠልን መብት ከሚያራምዱት ፖርቲዎች ሳይለዩ በማደበላለቅ ፖርቲዎቹ በኢትዮጵያ አንድነት እና ዳር ድንበር ዙሪያ ያላቸውን የአቋም ልዩነት በተጨባጭ ለይተው በማጥናት እንደምሁርነታቸው ትክክለኛ መረጃ አሰባስበው በመተንተን ከመተቸት ይልቅ ሁሉንም የብሔርብሔረሰብ ፖርቲዎች የጎሳ ፓርቲዎች ብለው ለአንድነት ጸር የሆኑ ሐይሎች አድርጎ በጅምላ በመፈረጅ መተቸታቸው ነው፡፡ እውነቱ ግን የኢትዮጵያ ብሔርብሔረሰቦች በሌሎች ሐገሮች እንደሚገኙት ብሔሮችና ብሔረሰቦች የተለያዩ በርካታ ጎሳዎች ተዋህደው የጋራ ማንነትን የሚገልጹ ህልውናዎችን (Identities) በመፍጠር የተከሰቱ ብዙ ጎሳዎችንም በውስጣቸው ያቀፋ ትላልቅ ማህበረሰቦች እንጂ በዘር ሐረግ ወይም በስጋ ዝምድና ላይ ብቻ በተመሰረተ ጎሳ (Clan) የሚፈረጁ አይደሉም፡፡ ይህንን ውነት ለማረጋገጥ ደግሞ መፍትሔው ጭፍን ፍረጃ ሳይሆን ቀረብ ብሎ የብሔርብሔረሰቦችን አመጣጥና አሁን የደረሱበትን የማንነት ደረጃ እንዴት ሊያገኙ እንደቻሉ ታሪካዊ እና ባህላዊ መረጃዎቻቸውን ማሰባሰብና በሐቅ ላይ ተመስርቶ መተንተን ብቻ በቂ ነው፡፡ በእኔ እምነት ይህንን እውነት ለማወቅ ወደምዕራባዊያንም ሆነ ወደምስራቃዊያን ርዕዮተአለም መጓተት ተገቢነትም ሆነ ፋይዳ የለውም፡፡ አንድ የኢትዮጵያ ብሔርም ሆነ ብሔረሰብ ለናሙና ወስዶ በውስጡ ያሉትን ጎሳዎች በዝርዝር በማጥናትና ጎሳዎቹ በጋራ ብሔሩን ወይም ብሔረሰቡን ማለትም የጋራ ማንነታቸውን የፈጠሩበትን ሂደትና የደረሱበትን ደረጃ አጥንቶ ሐቁን ከማወቅ ፋንታ ወደ ርዕዮተ አለማዊ ፍረጃ መቿከል የበሳል ምሁርነትም ሆነ ፖለቲከኛነት መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡
ኢትዮጵያ አገራችን ብዙ ብሔርብሔረሰቦችን ያቀፈች አገር (Multinational state) መሆኑዋም በአለማችን የተለየች የሚያደርጋት ሳይሆን በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ ብሔርብሔረሰቦችን አቅፈው በአለማችን ከተመሰረቱት ሐገራት (multinational states) ውስጥ አንዷ መሆኑዋን ብቻ ነው የሚያሳየው፡፡ ይህም የምንከፋበት ወይም እንደችግር አድርገን የምንወስደው ጉዳይ ሳይሆን የአገራችንና የህብረተሰባችን የታሪክ ሂደት እንደሌሎቹ አገሮች ሁሉ የፈቀደልን እድል አድርገን ልወስደውና በደስታም ልንቀበለው የሚገባን ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይልቁንም ችግራችን እንደነ ኘሮፌሰር መሳይ ያሉ ሊህቃን እና አንዳንድ የፖለቲካ ፖርቲዎች ኢትዮጵያችንን የብዙ ብሔርብሔረሰቦች የጋራ ሐገር መሆኑዋን ባለመቀበል በመሬት ላይ ካለው እውነት ጋር እየተላተሙ የሚፈጥሩብን ውዥምብር ነው፡፡ ሌላው ችግራችን ደግሞ ብዙህነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ የእኩልነት መብታችን የተከበረባትን አንዲት የጋራ አገር ከመገንባት ፋንታ የእስከመገንጠል መብትን ዋና ኩረታቸው አድርገው የሚያስተጋቡ እና ለተግባራዊነቱም የሚጮሁ የፖለቲካ ፖርቲዎች እና ሊህቃን ጉዳይ ነው፡፡ መድረክ እነዚህን ለሐገራችን ብሔርብሔረሰቦች ለጋራ ህልውናና ለጋራ እድገት የማይጠቅሙ ጫፍ ረጋጭ የፖለቲካ አቋሞችን በይፋ ውድቅ ያደረገና ብዙሕነታችንን ተቀብሎ ለአንድነታችን ደግሞ በጽናት በመታገል ላይ ያለ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊነት የእኩልነት መብትን ለማረጋገጥና በመከባበር ላይ በተመሰረተ ግንኙነት እንጂ ብዙሕነታችንን በመካድም ሆነ የመገንጠልን ሃሳብ በማራገብ የሚረጋገጥ ጉዳይ አይደለም ብሎ መድረክ በጽናት ያምናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ኘሮግራሙ እና በተግባራዊ እንቅስቃሴው ያሳየው ጽኑ አቋሙ ምስክሮቹ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት እና የብሔርብሔረሰቦቹዋን እና ህዝቦቹዋን በእኩልነት እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መድረክ ነጣጥሎ የማያያቸውና ፈጽሞ ለድርድር የማያቀርባቸው ጽኑ አቋሞቹ ናቸው፡፡
በመድረክ ውስጥ የታቀፋ ብሔራዊም ሆኑ ሕብረብሔራዊ ፖርቲዎችን በሚመለከትም አንዳቸውም የጎሳ (Clan) ፖርቲዎች አይደሉም፡፡ ጎሳዎች በኢትዮጵያ ብሔርብሔረሰቦች ውስጥ መኖራቸው እውነት ቢሆንም ፖርቲዎቹ የተመሰረቱት ግን ጎሳዎችን መሰረት አድርገው ሳይሆን ህብረብሔራዊ ወይም ብሔራዊ ሆነው ብቻ ነው፡፡ ኘሮፌሰር መሳይ ጎሳ እያሉ የሚፈርጁትን እነዚህን የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በየንዳንዳቸው ውስጥ ስንት ጎሳዎች እንዳሉና እነርሱ ደግሞ እንዴት በርካታ ጎሳዎችን በውስጣቸው አቅፈው የብሔር ብሔረሰብ ህልውና እንዳገኙ አጥንተውም እውነቱን ሲረዱ ፖርቲዎቹም የብሔርብሔረሰብ ወይም ህብረብሔራዊ እንጂ የጎሳዎች አለመሆናቸውን በተጨባጭ ይረዳሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ እውነት ላይ ለመድረስ የሚያስፈልገው ደግሞ በስሜታዊ ኘሮፓጋንዳ መመራትን አቁሞ ሐቁን ለመረዳት እራስን ማዘጋጀትና በተጨባጭ እውነት ላይ የተመሰረት ጥናትን ማካሄድ ብቻ ነው የሚገባው፡፡
በመድረክ ውስጥ የታቀፋት ብሔራዊ እና ሕብረብሔራዊ ፖርቲዎች ለኢትዮጵያ አንድነት ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ውህደትና አንድነትም ተገቢውን ጥረትና እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሰረት ከዚህ በፊት እንደተገለጸው አራት የመድረክ አባል ፖርቲዎች ውሕደት ፈጥረው በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት ፖርቲነት የተለወጡ ሲሆን በውሕደት የተፈጠሩት ሁለቱ ፖርቲዎችም አገር አቀፍ ፖርቲዎች ሆነው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በተዋሄዱትና በቀሩት የመድረክ አባል ፖርቲዎች መካከልም ውህደትን ለመፈጸም ጥረትና እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ቀጥሎአል፡፡ የመድረክ አባል ድርጅቶች ውህደት በጥልቅ መግባባትና የጋራ አቋም ላይ ሲደረስ የሚፈጠር ግንኙነት መሆኑን ስለተገነዘቡና ውሕደትን በስሜታዊነት መፈጸም ስለማይቻል ጥቂት ጊዜያትን ሊወስድ ይችላል እንጂ መፈጸሙ የማይቀርና ባስተማማኝ መግባባት እየተካሄደ ያለ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስለዚህም ኘሮፌሰር መሳይ ‹‹ አሁን ላይ አገር አቀፍ ፖርቲዎችን እና የጎሳ ፖርቲዎችን በአንድ አቀናጅቶ ጠንካራ መድብለ ፖርቲ የመፍጠሩ ጉዳይ ከገብራዊነት የሸሸ ምንም ሆኖአል፡፡›› በማለት በጽሁፋቸው ያስቀመጡት ሃሳብ መሰረተቢስ የሆነና ከክፋ አስተሳሰብ የመነጨ ሟርት ከመሆን ሊያልፍ አይችልም፡፡ መድረክ በውህደትም ሆነ በግንባር ቢንቀሳቀስ የቆመለት የኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ የራሱ የአባል ፖርቲዎች አንድነት ተጠናክሮ ጠንካራ አማራጭ መድብለፖርቲ የመሆኑ ጉዳይ ደግሞ በርሳቸው ሟርት የሚጨናገፍ ጉዳይ አይሆንም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
የግለሰብና የቡድን መብት ጉዳይንም ኘሮፌሰር መሳይ መድረክን ለማጥላላት በጻፋት ጽሁፋቸው አንስተዋል፡፡ በዚህ አስተያየታቸውም የቡድን መብትን ከግለሰብ መብት የሚያስቀድም ወይም የበላይ አድርጎ የሚወስድ ፖርቲ ማን እንደሆነ ለይተው ሳያጠኑ በመድረክ ኘሮግራምም ሆነ የስራ እንቅስቃሴው እየተገለጸ ካለው እውነታ ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ የቡድን መብት የበላይነት አራጋቢዎችን አቋም መድረክ ላይ ለመለጠፍ የማጥላላት ዘመቻቸው አካል አድርገውታል፡፡ ይህንንም ያደረጉት መድረክ በፖለቲካ ኘሮግራሙ አጠቃላይ መርሆችና አላማዎች ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ ‹‹ የግለሰብ፣ የብሔርብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና የቡድን መብቶች እኩል እንዲከበሩ ሳንታክት እንሰራለን፡፡ ›› በማለት በግልጽ ያስቀመጠውን አቋም እና በተለያዩ ወቅቶች ገዥው ፖርቲ በዜጎቻችን ላይ የሚፈጽማቸውን የግለሰብ ዜጎችን ሰበአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚጥስበትን አካሄድ በጥብቅ እየተቃወመና እየታገለ ብዙ መስዋእትነት እየከፈለ መሆኑን ስለማያውቁ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም እርሳቸው የፖለቲካ ፖርቲዎችን ሁሉ በሁለት ጎራ ማለትም የግለሰብ መብት የበላይነት አቀንቃኖችና የቡድን መብት የበላይነት አቀንቃኖች አድርገው በምዕራባዊያን ወይም በምስራቃዊያን ርዕዮተአለም ከሚፈርጁበት ጎራ በተለየ ሁኔታ መድረክ የኢትዮጵያን ሁኔታ መሰረት አድርጎ ሁለቱንም መብቶች ማለትም የግለሰብ መብትንና የቡድን መብትን በእኩልነት ተከብረው ስራ ላይ እንዲውሉ አንዳቸውም በሌላቸው ላይ የበላይነት መያዝ አስፈላጊ አለመሆኑን በአጽኖት አስቀምጦ በእኩልነት ስራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ቃል የገባና ለተግባራዊነቱም ሳይታክት በመስራት ላይ የሚገኝ ስለሆነ ይህን እያወቁ ለቡድን መብት የበላይት መቆምን በመድክ ላይ መለጠፍ ህብረተሰባችንን በመሰረተቢስ ኘሮፓጋንዳ ግራ ለማጋባት በመድረክ ላይ የሚያሰራጩት አደናጋሪ ወሬ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
ኘሮፌሰር መሳይ ከክፋ አስተሳሰብ ተነስተው የፈጠራ ኘሮፓጋንዳ በመድረክ ላይ በማካሄድ ህብረተሰባችንን ለማሳሳት እያደረጉ ያሉት ከንቱ ጥረት የማይሳካላቸው ቢሆንም በቸልታ ግን መታለፍ ስለማይገባው ይህንን ጽሁፍ ለማቅረብ የተገደድኩ መሆኔን ለአንባቢያን ከታላቅ አክብሮት ጋር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
እኩልነት፣ አንድነት እና መከባበር የሰፈነባት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን !!
ከጥላሁን እንደሻው የመድረክ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የህዝብ ግኑኝነት ኮሚቴ አባል
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen