Netsanet: የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል አንዳርጋቸው በአስቸኳይ እንዲለቀቅ አስጠነቀቀ

Donnerstag, 3. Juli 2014

የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል አንዳርጋቸው በአስቸኳይ እንዲለቀቅ አስጠነቀቀ

የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል አንዳርጋቸው በአስቸኳይ እንዲለቀቅ አስጠነቀቀ
የግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል " አንዳርጋቸው የማይጨበጥ ጽኑ መንፈስ እንጂ አንድ ግለሰብ አይደለም" በሚል ርእስ ባወጣው ጠንካራ መግለጫ " የየመን መንግሥት የፈጸመው ድርጊት እጅግ ስህተት መሆኑን ዘግይቶም ቢሆን ተረድቶ የነፃነት ታጋዩን እንዲለቅ" አስጠንቅቋል። ይህ ባይሆን ግን ይላል የግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል " አንዳርጋቸው ወያኔ እጅ ውስጥ ከገባ የትውልዱ የበቀል ሰይፍ ከዛሬ ጀምሮ ከሰገባው መውጣቱን እንዲያውቁት " ያስፈልጋል።
"ምንም አይነት ምድራዊም ይሁን ሰማያዊ መነሻ ምክንያት ለአቶ አንዳርጋቸው በየመን መንግሥት መታገት እና መታሰር ምክንያት ሊሆን እንደማይችል " በመግለጽ " የየመን መንግሥት የነፃነት ታጋያችንን ባስቸኳይእንዲለቅ ላለፉት ተከታታይ ቀናት የተደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ውጤት አለማስገኘቱን ፣ ከዚህም በመነሳት አቶ አንዳርጋቸው ለዘረኛው እና ከፋፋዩ የወያኔ ቡድን ሊሰጥ ይችላል የሚለው ስጋታችን ቀን በገፋ እና ምላሽ በራቀ ቁጥር እየጨመረ " ሄዷል ብሏል በመግለጫው።
በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል በኩል የነፃነት ታጋዩ ለወያኔ ተላልፎ መሰጠቱን መቶ በመቶ እስከምናረጋግጥበት ቅጽበት ታጋዩን የማስለቀቅ ጥረቱ መቀጠል እንዳለበት በጽኑ እናምናለን የሚለው ህዝባዊ ሃይሉ፣ "አንዳርጋቸውን ማሰር ይቻላል፤ምናልባትም በዚህ ቅጽበት ተችሏል፤ አንዳርጋቸውን ማሰቃየት ይቻላል፤ምናልባትም በዚህ ቅጽበት ተችሏል፤ አንዳርጋቸውን መግደል ይቻላል። ሞትን ፈርቶ ወደ ትግል አልገባምና አንዳርጋቸውን በማሰር የአንዳርጋቸውን እንደ እቶን የሚያቃጥል የፍትህ፣የነፃነት፣ የዴሞክራሲና የእኩልነት መንፈስ ግን ለሴኮንዶች እንኳን ማሰር አይቻልም፣ አንዳርጋቸውን በማሰቃየትያን ዘመን ተሻጋሪ የሆነ የትውልዱን መንፈስ የሚገዛ የሁላችንም የምትሆን የጋራ ኢትዮጵያን የመፍጠር ንጹህ ራዕዩን ግን ፈጽሞ ማቁሰል አይቻልም!!!አንዳርጋቸውን በመግደል ዕንቁ ዓላማውን መግደል ከቶ አይቻልም፤ የታሪክ መዛግብት ገጾች ለዚህ ሃቅ በሚመሰክሩ እውነታዎች የተሞላ ነውና" በማለት የሚያትተው መግለጫ፣ አንዳርጋቸውን በመግደል “ከአባቶቹ የማይበልጥ ትውልድ እንዳልተፈጠረ ይቆጠራል፣ ልጅ አባቱን ሩጦ መቅደም አለበት፣ስለዚህ እናንተ ወጣቶች እኛን ሩጡ እና ብለጡ ቅደሙን፣ቀናዎች ሁኑ፣ ርስ በርስ ተዋደዱ፣ ያለፉት ትውልዶች የሰሩትን ስህተት ላለመድገም ታሪክን ከስሩ ተረዱ፣ ያለማወቅ ጠንቅ ከሚያመጣው ጥፋት ለመዳን ሁሌም ለእውቀት ጉጉዎች ሁኑ። ለማወቅ ጣሩ፣የማይቀረው ሞታችሁ ለፍትህ፣ለዴሞክራሲ እና ለነፃ ኢትዮጵያ ይሁን” እያለ ላለፉት በርካታ አመታት ያስተማራቸው እና የኮተኮታቸው የነፃነት ታጋይ አርበኛ ወጣቶችን እና እሳት መንፈሳቸውን መግደል አይቻልም:" ሲል ያክላል።
"አንዳርጋቸውን በአንድ ካቴና በማሰር፤ በአንድ ክፍል ውስጥ በመዝጋት ወይም በአንድ ጥይት በመግደል “መገላገል” የሚቻል አንድ ግለሰብ አይደለም:: አንዳርጋቸው ለሽህ ካቴናዎች የማይታጠፉ እጆች፤ ለሽህ ማጎሪያዎች የገዘፈ ገላ፤ ለሽህ ጥይቶች የሰፋ እና ሽህ ጥይቶችን የሚተፋ ግንባር እና ደረት ያለው ብርቱ ታጋይ ነው። አንዳርጋቸው አንድ ግለሰብ አይደለም፤ የማይጨበጥ ጽኑ መንፈስ እንጅ!!!" ሲል ለመሪያቸው ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
አንዳርጋቸው ይላል መግለጫው በማስከተል " ለአርባ አመታት በሚጠጋ የፖለቲካ ሕይወቱ ሁሉ በረሃ የሚወረወረው አፈር ላይ የሚንከባለለው፤ በእሱ እድሜ በማይታሰብ ሁኔታ እንኳን የበረሃ ሃሩር፣ ጥም እና ረሃብ የሚያንገላታው ነገ ኢትዮጵያን በፕሬዝዳንትነት ወይ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስቴርነት ለመምራት ካለው ሰዋዊ ፍላጎት አይደለም:: የሱ ምኞት የሁላችንም የሆነች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት ነው!!! አንዳርጋቸው ሁሌ ለሚያልማት ንጽህት ኢትዮጵያ መሥራት የነበረበትን ፈታኝ እና ታሪካዊ ሥራዎች ቀድሞ አከናውኗቸዋል:: ላለፉት 6 እና 7 ዓመታት ከጥልቅ የፖለቲካ ተሞክሮው እየቀዳ ለወጣት ኢትዮጵያውያን በየበረሃው እየዞረ አስተምሯል:: እያማጠ አደራ ብሏል:: እያለቀሰ ምኞቱን፣ፍላጎቱን እና ራዕዩን ከውስጡ አውጥቶ መዳፉ ላይ በማስቀመጥ ልቡን ለታዳጊዎች አሳይቷል:: ንጹህ ዓላማው ሽህ ባለ ራዕዮችን ፈጥሯል የተግባር ሰዎችን አምርቷል::የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል አንዳርጋቸው እንደመጥምቁ ዮሃነስ በበረሃ እየዞረ ሲያስተምር እና ሲሰብክ ከፈጠረው ንጹህ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ላይ የበቀለ ኃይል ነው:: "
መግለጫው በመጨረሻም " ዛሬ አንዳርጋቸው በአካል አብሮን ላይኖር ይችላል::ነፍሳችን ውስጥ ያሰረፀው ዘላለማዊ መንፈስ ግን እስከመጨረሻ ህቅታችን ድረስ አብሮን ይዘልቃል::አንዳርጋቸውን በማስቆም ትግሉን አቆማለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ ዓለምን እና ሁኔታዎችን መገንዘብ የማይችል ከራሱ የተጣላ የወያኔ አይነት ቂል ብቻ ነው::አንዳርጋቸውን በማስቆም ትግሉን ማስቆም አይቻልም::መንፈስን ማስቆም ከቶ ማን ይቻለዋል??አንዳርጋቸው እኮ መንፈስነው::ሁሉም ቦታ፣ሁሉም ጫፍ፣ሁሉም ልብ ውስጥ የሚገኝ እና የሚንሳፈፍ መንፈስ::" ካለ በሁዋላ " የየመን መንግሥት የፈጸመው ድርጊት እጅግ ስህተት መሆኑን ዘግይቶም ቢሆን ተረድቶ የነፃነት ታጋያችንን ባስቸኳይ ይለቀው ዘንድ አሁንም ደጋግመን እንጠይቃለን::ይህ ሳይሆን ቀርቶ ታጋያችን ወያኔ እጅ ውስጥ ከገባ ግን የትውልዱ የበቀል ሰይፍ ከዛሬ ጀምሮ ከሰገባው መውጣቱን እንዲያውቁት እንፈልጋለን::ወያኔም ይህ የቂል ድርጊት የነፃነት ታጋዮችን የበለጠ ቁጭት እና የበቀል እርምጃዎች ውስጥ የሚከት መሆኑን አብሮ ሊገነዘበው ይገባል::ለዚህ ቃላችን ታሪክ ምስክር ይሁንብን::" በማለት መግለጫውን አጠቃሏል።
የየመን መንግስት በአተፐ አንዳርጋቸው ዙሪያ እስካሁን የሰጠመው መግለጫ የለም። ኢሳት የተለያዩ የአገሪቱን ባለስልጣናት ለማነጋገር ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen