ምላሹን አልቀበልም በማለቱም በፖስታ ቤት ተልኮለታል ህገ መንግስቱ እውቅና የቸረው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ሳይሸራረፍ መተግበሩን እንዲከታተል በአዋጅ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መጋቢት 28/2006 ዓ.ም መነሻውን ፓርቲው ከሚገኝበት ቀበና በማድረግ በአራት ኪሎ አደባባይ በመዞር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ፊት ለፊት የሚጠናቀቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ ለኦፊሰሩ ደብዳቤ አስገብቶ የነበረ ቢሆንም መስተዳድሩ በአዋጅ የተሰጠውን ጊዜ ገደብ አሳልፎ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ኦፊሰሩ በደብዳቤያቸው ‹‹በርካታ ትምህርት ቤቶች ዩኒቨርስቲና ፣የመንግስት ተቋማት በሚገኙበት አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የማይቻል በመሆኑ የተጠየቀውን የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ጥያቄ ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን እንገልጻለን፡፡››ብሏል፡፡ የአገሪቱ ፓርላማ ‹‹ስለ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ስነ ስርዓት ባወጣው አዋጅ ‹‹የከተማው ወይም የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው ምን ግዜም በየትኛውም ቦታ ሊካሄድ አይችልም ማለት አይችልም››(አዋጅ ቁጥር 3/1983 )በማለት ያወጀውን በአዋጁ ስር የተቋቋመው ጽ/ቤት በማን አለብኝነት በመሻር የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄውን አልተቀበኩትም ብሏል፡፡ አንድነት አዋጁን የጣሰውን ደብዳቤ እንደማይቀበል በመግለጽ ለኦፊሰሩ ደብዳቤ በመጻፍ በአካል ቢሯቸው በመገኘት ለመስጠት ቢሞክርም በአስገራሚ ሁኔታ ኦፊሰሩ ደብዳቤውን አልቀበልም ብለዋል፡፡
የኦፊሰሩ ድርጊት ህገ ወጥ መሆኑን የተገነዘበው ፓርቲያችን ደብዳቤውን ቢሯቸው ጠረጴዛ ላይ ትቶ ከመውጣቱም በላይ በሪኮማንዴ እንዲደርሳቸው አድርጓል፡፡ ኦፊሰሩ እየሰሩ የሚገኙት ነገር ህገ ወጥ መሆኑን እንዲገነዘቡም ለፌደራል ፖሊስ፣ለአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ በግልባጭ ደብዳቤው እንዲደርሳቸው መደረጉን የአንድነት የአዲስ አበባ ዋና ጸሐፊ አቶ ነብዩ ባዘዘው ተናግረዋል፡፡ በህገ ወጥ ደብዳቤ የሚሰረዝ ሰላማዊ የህዝብ ጥያቄ ባለመኖሩም ሰላማዊ ሰልፉ በተያዘለት ቀነ ገደብ እንደሚደረግ አቶ ነብዩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen