Netsanet: ኢትዮጵያ በሕግ ነው ወይስ በዉስጣዊ የአፈና አዋጅ የምትተዳደረው ? ግርማ ካሳ

Freitag, 4. April 2014

ኢትዮጵያ በሕግ ነው ወይስ በዉስጣዊ የአፈና አዋጅ የምትተዳደረው ? ግርማ ካሳ

April 3/2014
«ዴሞክራሲ የለም! ሰልፍ ማድረግ አይቻልም! አርፋችሁ ተቀመጡ ! » የሚሉን ከሆነ ይንገሩን ። የአገሪቷ ሕግ የሚለው ግልጽ ነው። ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሙሉ መብት አላቸው። አስተዳደሩ በይፋ ሕግ ወጥ ተግባር ነው እየፈጸመ ያለው።
ሕጉ እንዲህ ነው የሚለው ፡
“ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ህዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው በሌላ ጊዜ ወይም በሌላ ስፍራ ቢደረግ ይሻላል የሚል አስተያየት ካለውም ምክንያቱን በመግለፅ ይህንኑ ጥያቄው በደረሰው በ12 ሰዓት ውሳጥ በፅሁፍ ለአዘጋጁ የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት ………ሆኖም የከተማው ወይም የአውራጃው አስተዳደር ፅ/ቤት ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ህዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው ምንጊዜም በየትኛውም ቦታ ሊካሄድ አይችልም ማለት አይችልም”
በመጀመሪያ አንድነት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ፊት ለፊት ሰልፉን እንደሚያጠናቅቅ አሳወቀ። አዲስ አበባ አስተዳደር «እውቅና አልሰጥም» አለ። እንደገና ሌሎች ሶስት አማራጮችን ( ማዘጋጃ ቤት፣ ጥቁር አንበሳ ያለው አደባባይና መስቀል አደባባይ) አንድነት አቀረበ። አስተዳደሩ ግን እንደገና ሶስቱም ስፍራዎc የተከለከሉ ናቸው ሲል « የተጠየቀዉን የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ጥያቄ ተቀባይነት ያላገኝ መሆኑን እንገልጻለን» አለ።
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያለው አደባባይ፣ ከዚህ በፊት ለሰማያዊ ፓርቲ የተፈቀደ አደባባይ ነበር። መስቀል አደባባይ ደግሞ ኢሕአዴግ በርካታ ጊዜ ሰልፍ የጠራበት ቦታ ነው። አደባባዮቹ ለተወሰኑት ተፈቅደው ለሌላዉ ለምን እንደሚከለከሉ ግራ የሚያጋባ ነው።
በሕጉ መሰረት የቀረቡ ቦታዎችን አስተዳደሩ ካልፈቀደ፣ «በዚህ ቦታ አድርጉ» ብሎ አማራጭችን ማቅረብ ሲገባው፣ ከከተማዋ ዉጭ ባሉ ጫካዎች ሰልፍ እንዲደረግለት ፈልጎ ነው መሰለኝ ፣ አስተዳደሩ ሕገ ወጥ በሆነ አቋሙ ጸንቷል። «በአጭሩ በሕግ ያልተሰጠዉን ፣ ፍቃድ ሰጭ ፣ ይመስል፣ «አልፈቅድም» አለ። በሌላ አባባል « ሕግ ቢፈቅድላችሁም፣ እኔ ካልኩት ዉጭ ካደረጋችሁ፣ እኔ ከሕግ በላይ ስleሆንኩኝ፣ ትታሰራላችሁ» ማለቱ ነው። ሕገ አራዊት ይሉታል ይሄ ነው !!!!!!
የአንድነት ፓርቲ ከዚህ በፊት በርካታ ሰልፎችን ከአዲስ አበባ ውጭ አድርጓል። በቅርቡ በባህር ዳር የተደረገዉና ኢቲቪ እራሱ ሳይቀር የዘገበውn ሰልፍ፣ ሁላችንም የምናስታዉሰው ነው። በዚያ ሰልፍ፣ የጠፋ ወይንም የወደመ ንብረት የለም። አንዲት ጠጠር አልተወረወረችም። ከሰማኒያ ሺህ በላይ የባህር ዳር ነዋሪ በሰላም ወጥቶ ነው በሰላም የገባው። ፓርቲው ምን ያህል የሰለጠነ፣ ሰላማዊ መሆኑን በገሃድ በድጋሚ ያስመሰከረበት ስልፍ ነበር።
ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ እያደረገ እንዳለው፣ ለምን በዚህ መልክ የዜጎችን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እንደሚጋፋ ሊገባኝ አልቻለም። ለምን ሕዝብን እንደሚፈራ ሊገባኝ አልቻለም። ባለስልጣናቱ ለምን ሕዝቡን ማፈን፣ አገሪቷን ወደ ባስ ችግር ሊከታት እንደሚችል መረዳት እንዳካታቸው ሊገባኝ አልቻለም ?
«በቅርቡ ድሪባ ኩማ ጅዳ (ሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሚያ) ሄዶ የትውልድ መንደሩን ውሃ አስመርቆ ነበር» ሲል ሰለሞን ስዮም ጽፏል። ከንቲባ ድሪባ፣ በተወለዱበት መንደር እንዳደረጉት፣ ለሚያስተዳድሩት የአዲስ አበባ ህዝብ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የኔትዎርክ ፣ የትራንስፖርት የመሳሰሉት አገልግሎት በሚገባ እንዲያገኝ ማድረጉ ላይ ማተኮርና መስራት ሲገባቸው፣ ሕግን እየጣሱ ፣ ዜጎችን ማፈን መምረጣቸው አሳዛኝና አሳፋሪ ነው። ይሄ አያዋጣቸውም። አርፈው በትክክል፣ ሕግን አክብረው፣ ስራቸዉን ይስሩ !!!! ሕዝቡም ሕጉ የፈቀደለትን መብት ተጠቅሞ ድምጹን ያሰማ !
አክሊሉ ሰይፉ፣ ሰለሞን ፀሃይ፣ ኤፍሬም ሰለሞን፣ ታሪኬ ኬፋ፣ ወጣት ወርቁ ፣ ሀብታሙ ታምሩ፣ አሸናፊ ጨመዳ፣ መቶ አለቃ አንዳርጌ መስፍን እንዲሁም ሌሎች፣ ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀማቸው ፣ ሕግ ወጥ በሆነ መልኩ የታስሩ ሰላማዊ ዜጎች አሉ። በአስቸኳይ ይፈቱ።
ከንቲባ ድሪባን ጨምሮ፣ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ልብ እንዲገዙ እመክራለ ! ለነርሱም፣ ለኛም ለሁላችንም፣ ለአገራችን፣ ለመጪው ትዉልድ ስንል ሕግን አክብረን፣ ተከባብረን፣ ተቻችለን ብንኖር ይሻለናል ! በፍቅር አገራችንን ብንገባ ይሻለናል !
ጆሮ ያለው ይስማ ! ልብ ያለው ያስተዉል !
http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/13798

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen