Netsanet: ሰማያዊ – የወላይታ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ታሰሩ

Mittwoch, 2. April 2014

ሰማያዊ – የወላይታ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ታሰሩ

April 2/2014

መጋቢት 20/ 2006 ዓ.ም የወላይታ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ሶዶ ውስጥ ስብሰባ ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ በነበረበት ወቅት ፖሊስ ምንም አይነት ምክንያት ሳይሰጥ ሰብስቦ እንዳሰራቸው ከአካባቢው የፓርቲው ተወካዮች ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት አመራሮቹ ድል በትግል በተባለው የፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ፡፡በአሁኑ ወቅትም እስር ላይ ከሚገኙት መካከልም፡-
1. ወጨፎ ሳዳሞ የወላይታ ዞን ምክትል ሰብሳቢ
2. ታደመ ፍቃዱ የወላይታ ዞን አደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ
3. አቶ ጻድቁ ወ/ስላሴ የወላይታ ዞን የፋይናንስ ኃላፊ
4. አቶ ቴዎድሮስ ጌታ የዞኑ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ
5. ቦጋለ የፓርቲው አባል
ይገኙበታል። እነዚህ አመራሮች መታሰራቸውን ተከትሎ የዞኑ የፓርቲው ሌሎች አመራሮችና አባላት፣ ድል በትግል ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ታሳሪዎችን ለመጠየቅም ሆነ የታሰሩበትን ምክንያት ለማጣራት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን ማወቅ ተችሏል፡፡
ጠዋት 4 ሰዓት ላይ የታሰሩት የዞኑ አመራሮች ምግብ፣ ውሃና ልብስ እንዳይገባላቸው መከልከሉንም የአካባቢው አመራሮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት የፓርቲው አመራሮች ለስብሰባ ወደ አካባቢው በሄዱበት ወቅት በተመሳሳይ ሁኔታ ታስረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ከታሰሩት የፓርቲው ኃላፊዎች መካከል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ በወላይታ ዞን በተቃዋሚዎች በተለይም ሰማያዊ ፓርቲ ላይ የሚደረገው አፈና መጠናከሩን በመጥቀስ፣ ይህንን አፈና በመቃወም ፓርቲው በቅርብ ጊዜ በአካባቢው ህዝባዊ ንቅናቄ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በዞኑ የሚደረገው አፈና ህገ ወጥ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት እስር ቤት ውስጥ የሚገኙት የዞኑ የፓርቲያቸው አመራሮችም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen