Netsanet: ሁለቱ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች 10 ቀን ተቀጠረባቸው

Montag, 17. November 2014

ሁለቱ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች 10 ቀን ተቀጠረባቸው



የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ለህዳር 7/2007 ዓ.ም ጠርቶት ለነበረው የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ አርብ ህዳር 5/2007 ዓ.ም በቅስቀሳ ላይ እንደነበሩ የታሰሩት ሁለት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች 10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡ በቅስቀሳ ላይ በነበሩበት ወቅት የታሳሩት የብሄራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ዮሴፍ ተሻገር እንዲሁም አቶ ሲሳይ በዳኔ ዛሬ ሾላ አካባቢ በሚገኝ ችሎት ቀርበው የ10 ቀን ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ 

ፖሊስ በታሳሪዎቹ ላይ ‹‹ላልተፈቀደ ስብሰባ ህገ ወጥ ወረቀት ሲበትኑ ተገኝተዋል፡፡ ለህዝብ አሰራጭተዋል፡፡ የእውቅና ደብዳቤ ብንጠይቃቸው ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ ቋሚ መኖሪያም የላቸውም፡፡ ሌሎች የምናጣራቸው መረጃዎች አሉ፡፡›› በሚል የ14 ቀን ቀጠሮ እንዲሰጥለት ጠይቆ የነበር ሲሆን ታሳሪዎቹ በበኩላቸው ፖሊስ የእውቅና ወረቀቱን ተቀብሎ መደበቁን፣ ቋሚ መኖሪያና ቤተሰብ እንዳላቸው፣ የህጋዊ ፓርቲ አመራሮች በመሆናቸው በየትኛውም ጊዜ ቢጠሩ እንደሚመጡ ጠቅሰው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ቢከራከሩም ዳኛው የ10 ቀን ቀነ ቀጠሮ ሰጥቶባቸዋል፡፡ ታሳሪዎቹ ሲቀሰቅሱ በነበሩበት ወቅት ፓርቲው ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰበባ ያሳወቀበትን ደብዳቤ ይዘው እንደነበር የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ 

በተመሳሳይ ቅስቀሳ ላይ የታሰሩት የአዲስ አበባ ከተማ ም/ሰብሳቢና የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ማቲያስ መኩሪያ እና የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ሳምሶን ግዛቸው ‹‹በሽብርተኝነት›› ክስ የ7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንደተሰጠባቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ዮሴፍ ተሸገርና አቶ ሲሳይ በዳኔ በአሁኑ ወቅት ቤላ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen