Netsanet: አረንጓዴ ኢኮኖሚና መለስን ምን አገናኛቸው?

Dienstag, 16. September 2014

አረንጓዴ ኢኮኖሚና መለስን ምን አገናኛቸው?

ጌታቸው ሺፈራው
የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተጣጣመ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ የኢኮኖሚክስ መርህ በበርካታ ምሁራን የተነሳ ቢሆንም መንግስታት ለጊዜያዊ ጥቅማቸው ሲያምታቱት ይስተዋላል፡፡ በአብዛኛው አረንጓዴ ኢኮኖሚ ሲባል እንደ ጸሃይ ብርሃንና ባዮ ጋዝን እንዲሁም የአየር ንብረትን ለመከላከል የሚያስችሉ (ለምሳሌ በኤሌክትሪክ መኪናዎችን) ቴክኖሎጅ መጠቀም ያካትታል፡፡ የውሃ ንጽህናን መጠናከርና ብከላን ማስወገድ፤ የፍሳሽ አገልግሎትን በማዘመንና ቆሻሻን እንደገና በመጠቀም አካባቢን ከብክለት መከላከል የዢሁ ስልት አንድ አካል ነው፡፡ ደንን ማልማት፣ መሬትን ከመከላት መከላከልና የመሳሰሉትን ከባቢ አየርን ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎችን መጠቀም ላይ የሚያተኩር ፖሊሲም ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጋር ሲያያዝ ይታያል፡፡
በእርግጥ ምሁራንም ቢሆን አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚለውን ትርጉም እንደ የራሳቸው የሚተሩሙት መሆኑን ተከትሎ እስካሁን ግልጽ ትርጉም እንዳልተሰጠው የሚናገሩት በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚባል ነገር የለም ከሚሉት ጀምሮ ከአፈጻጸሙ፣ ለመጠቀሚያነት ብቻ የሚውል መሆኑ፣ በትርጉም ልዩነትና በመሳሰሉት ተቃውሞዎች ይገጥሙታል፡፡
  Meles Zenawi
Meles Zenawi

አረንጓዴ ኢኮኖሚ እንደ መለስ ራዕይ
ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ኢህአዴግ አዲስ አባዜ የተጠናወተው ይመስላል፡፡ ሁሉም የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስኬቶች በአቶ መለስ የተወጠኑ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲያወራ ይደመጣል፡፡ ተቋማት፣ ምሁራንና ሰራተኞች የሌሉ ያህል አቶ መለስ የሁሉም የአገሪቱ ፖሊሲና ስትራቴጅዎች ቀያሽና የመጽሐፎች ሁሉ ደራሲ ተደርገዋል፡፡ ልማታዊ መንግስትና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተባሉት በውል ያልተተረጎሙ እና በመልካም ተሞክሮነት ከሌሎች የተለበጡ የስልጣን መወጣጫ መርሆች ሳይቀር አቶ መለስ የፈጠሯቸው ተደርገው እየተወሩ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲም ሆነ ልማታዊ መንግስት አቶ መለስ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ሌሎች ስርዓቶች ተግባራዊ ያደረጓቸው ቢሆንም በኢህአዴግ መንደር ግን የአቶ መለስ ግኝቶች ተደርገው እየቀረቡ ነው፡፡
በቅርቡ ደግሞ ኢህአዴግ አቶ መለስ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን መርህ ለዓለም አማራጭ ማቅረባቸውን እየነገረን ነው፡፡ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ባዮ ጋዝና የጸሀይ ብርሃን መጠቀም፣ ቆሻሻን እንደገና መጠቀም፣ ደን እንክብካቤ፣ የአካባቢ ጥበቃ ጋር ምቹ የሆኑ ምርቶች (አረንጓዴ ምርቶች) ማምረትና የመሳሰሉትን የሚያጠቃልል በመሆኑ ስሙ ተሰጥቶትም ሆነ ሳይሰጠው በርካታ የዓለም አገራት አቶ መለስ ከመወለዳቸው በፊት ጀምሮ ተጠቅመውበታል፡፡ ለአብነት ያህል የጸሃይ ብርሃንን በታዳሽ ምንጭነት ለመጠቀም የሚያስችለው የመጀመሪያው የዘርፉ (የአረንጓዴ) ቴክኖሎጅ የተሰራው እ.ኤአ በ1883 ቻርለስ ፍሪት በተባለ ግለሰብ ነው፡፡ ምንም እንኳ ይህ ቴክኖሎጅ በተለይ ኤሌክትሪክ ማመንጨት የቻለው ዘግይቶ ቢሆንም ይህም ቢሆን አቶ መለስ ስልጣን ከመያዛቸው 6 አመት ቀድሞ እ.ኤ.አ በ1985 ነው፡፡ ምዕራባዊያን አገራት ይህን ታዳሽ ሀይል አቶ መለስ ምኒልክ ቤተ-መንግስት ከመግባታቸው በፊት ወደ ሀይል ቀይረው ተጠቅመውበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳቡ ከመነሳቱ በፊት የሰሜን አፍሪካ አገራትና ጎረቤታችን ኬንያን ጨምሮ በርካቶቹ አገራት ተጠቅመውበታል፡፡
ለአረንጓዴ ቴክኖሎጂ እንደ አንድ ግብዓት የሚጠቀሰው ኢታኖል ነው፡፡ የኢታኖል ሳይንሳዊ ቀመር የተገኘው እ.ኤ.አ በ1840 ዎቹ ነው፡፡ አሜሪካውያን ይህ የኢታኖል ሳይንሳዊ ቀመር ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ለመብራትነት ሲገለገሉበት ኖረዋል፡፡ እንግዲህ አቶ መለስ ከመወለዳቸው ከሁለት መቶ አመት በፊት መሆኑ ነው፡፡ አረንጓዴ ቴክኖሎጂ የአሁኑ ትርጉም ተሰጥቶት ተግባራዊ መሆን በጀመረበት ወቅትም ቢሆን ለአቶ መለስና ኢህአዴግ ሩቅ ነው፡፡ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በተደራጀ መልኩ በተለይም በተቋማት አነሳሽነት የጀመረው እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል እ.ኤ.አ በ1980 ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ህብረት አገራት ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ እንዲችሉ ለማድረግ በሚል ይህን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው በጥናቱ ላይ እስቀምጧል፡፡
ከ12 አመት በኋላ እ.ኤ.አ በ1992 (አቶ መለስ ስልጣን በያዙ ከአንድ አመት በኋላ ሲሆን በስብሰባው አልነበሩም) በብራዚሏ ሪዮ ዲጀኔሮ በተካሄደው ስብሰባ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ አቶ መለስ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለዓለም በአማራጭነት ያቀረቡ በሚል የሚያቀርበው ሙገሳ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ አቶ መለስ በቅርብ አመታት አፍሪካን ወክለው በተለያዩ መድረኮች ስለ አየር ንብረት ድርድር አድርገዋል፡፡ ይህም ቢሆን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ያላት መቀመጫና ተደማጭነትንም ጭምር ያገናዘበ ነው፡፡
አቶ መለስ በዓለም አቀፍ መድረክ የማሳመን ብቃት ስላላቸው ነው ቢባል እንኳ በድርድሩ ወቅት የሚያቀርቡት ማሳመኛ የአፍሪካ አገራት ባለሙያዎች፣ መሪዎችና ሌሎች አካላት ተወያይተው የተስማሙበትን ሀሳብ ነው፡፡ በአንድ ወቅት አቶ መለስ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ መድረክ አፍሪካ ልታገኝ ይገባት የነበረውን 30 ቢሊዮን በላይ ዶላር ጥቅም 10 ቢሊዮን እንዲሆን አድርገዋል በሚል ከሱዳንና ከሌሎች ልዑካን ተቃውሞ እንደደረሰባቸው ስናስታውስ ደግሞ አዲስ ፈጠራ ማበርከት ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያን የተስማሙበትንም እንዳላስፈጸሙ እንመለከታለን፡፡ በ2005 ዓ/ም አፍሪካን የወከለችው ኢትዮጵያ ስለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለተባበሩት መንግስታት አቅርባ ተቀባይነት ማግኘቷ ተዘግቧል፡፡ ይህም ቢሆን ጥቃቅን ማሻሻያ ረቂቅ እንጂ የአጠቃላይ አረንጓዴ ኢኮኖሚው ጠንሳሽ ሊያደርጋት አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በርካታ አገራት አጀንዳና ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ማሻሻያና የመሳሰሉትን በማቅረባቸው ግን ራሳቸውን የዋናው ሀሳብ አመንጭ አድርገው ሲያቀርቡ አይታዩም፡፡
በነገራችን ላይ ህወሓት በርሃ በወጣባቸው በመጀመሪያ አመታት ደርግ ‹‹አረንጓዴ ልማት›› በሚል ሰፋፊ እርሻዎች ልማት ጀምሮ እንደነበር ይነገራል፡፡ በወቅቱ አሁን ለአቶ መለስ መታሰቢያ የየመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ አትክልት ከሚተክለውም በላይ ኢትዮጵያውያን በግድ ምግባቸው ብቻ እየተቻላቸው ያለሙ ነበር፡፡ ይህ ኢትዮጵያውያን ተገደው ያሉሙት የነበረው ልማት ለደርግ ‹‹አረንጓዴ ኢኮኖሚ›› መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግም ይህን ያህል ተግባር ቢፈጽም ከደርግ ያልተናነሰ ራዕይ ጨምሮበት ለፕሮፖጋንዳ ሊጠቀምበት እንደሚችል የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ይህን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተግባዊ እያደረጉ ከሚገኙ አገራት መካከል በመጨረሻዎቹ ረድፍ የተመደበች አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው 40ና 50 አመት ከ40 በመቶ በላይ የደን ሽፍን እንደነበራት ይነገራል፡፡ በህዝብ ብዛትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ከ20 አመት በፊት ይህ የደን ሽፋን ከ3-4 በመቶ ይሆን እንደነበር በመስኩ የተደረጉ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ አሁን ከዚህም በታች ወርዷል፡፡ ለ99 አመት ለአረብ፣ ህንድና ቻይና ባለሀብቶች እየተሰጠ ያለው በደን የተሸፈነ መሬት ሲመነጠር ድግሞ ይህን የደን ሀብታችን በእጅጉ እንደሚያመናምነው አያጠራጥርም፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመርህ ደረጃ እፈጽማለሁ ቢልም ተግባራዊነቱ ግን ገና በእንጭጭ ላይ ነው፡፡ ከተቋማቱ ጀምሮ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ አለብነት ያህል፣ አብዛኛዎቹ ክልሎች የደን ልማት በግብርና ሚንስትር ስር የሚገኝ ነው፡፡ በመሆኑም የግብርና ሚንስተር በተቻለ መጠን አገሪቱን መሬት እንዲታረስ ማድረግ ነው፡፡ የደን ጥበቃ ደግሞ ደንን ማሰጠበቅ፡፡ እነዚህ ሁለቱ የሚጋጩ ለጥዕኮዎች አላቻው ናቸው፡፡ በተለይ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በሚል ለኢንቨስተሮች ሰፋፊ መሬቶችን የሚሰጡት የክልል ቢሮዎች ለደን ልማትና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ምንም ዝግጅት የላቸውም፡፡ ለምሳሌ ያህል ጋምቤላ ብንወስድ፤ ለውጭ ባለሀብቶች እየተሰጠ ያለው መሬት ታርሶ የማያውቅና በደን የተሸፈነ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እስካሁን በጋምቤላ ብቻ ከሲውዘርላንድ የሚበልጥ የቆዳ ስፋት ያለው መሬት ለውጭ ባለሀብቶች ተሰጥቷል፡፡ እነዚህ የውጭ ባለሀብቶች የሚጠቀሙበት ኬሚካል የአካባቢውንና የአገሪቱን የአየር ንብረት ይበክላል፡፡ ይህ ሰፊ ደንን እያስመነጠሩ መሬትን በሲጋራ ዋጋ መሸጥ፣ በኬሚካል ማስበከል አቶ መለስ ጀምረውት ሌሎቹ በ‹‹ራዕይ›› እያስቀጠሉት ነው፡፡ እንዲህ ደን እየወደመ፣ የአየር ንብረት እየተበከለ፣ አፍሪካውያን ለተበከለው ይከፈለን የሚሉትን ሰያስፈጽሙ አቶ መለስና ኢህአዴግ ከአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ጋር ምን እንደሚያገናኛቸው አይገባኝም፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen