Netsanet: በሕገ ወጡ መጅሊስ ውስጥ መፈንቅለ ስልጣን መደረጉ ተነገረ!

Donnerstag, 1. Mai 2014

በሕገ ወጡ መጅሊስ ውስጥ መፈንቅለ ስልጣን መደረጉ ተነገረ!

May 1/2014

በሕገ ወጡ መጅሊስ ውስጥ መፈንቅለ ስልጣን መደረጉ ተነገረ!
ፕሬዚዳንቱ በሌሉበት ሥልጣናቸውን ተነጥቀዋል!
ረቡእ ሚያዝያ 22/2006

በዶ/ር ሽፈራው እና በደህንነት መስሪያ ቤቱ አማካኝነት የሚመሩት የአዲስ አበባ እና የአማራ መጅሊስ አመራሮች መፈንቅለ ሥልጣን ዛሬ መፈጸማቸውን የቅርብ ምንጮች ገለጹ! ይኸው መፈንቅለ ስልጣን የፌዴራል መጅሊስና የአዲስ አበባ መጅሊስን ያመሰ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በዛሬው መፈንቅለ ስልጣን የፌዴራል መጅሊስ ፕሬዚዳንት ሸኽ ኪያር ሸኽ መሀመድ አማን፣ የፌዴራል መጅሊስ ዋና ጸሀፊ አቶ ሙሀመድ አሊ፣ ከአዲስ አበባ መጅሊስ ደግሞ ኢንጂነር ተማምና ሌላ አንድ ሀላፊ መነሳታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከስልጣናቸው ተነሱ የተባሉት ፕሬዝደንቱ ሸኽ ኪያር በአሁኑ ሰአት ከአገር ውጪ በሳኡዲ አረቢያ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በዛሬው መፈንቅለ ሥልጣን በሸኽ ኪያር ቦታ የኦሮሚያ ክልል ተወካዩ መተካታቸው ሲገለጽ፣ የአማራው ክልል ተወካይም የኡለማ ም/ቤቱን መረከባቸው ተሰምቷል፡፡

በዚህ ዛሬ ተጠናቀቀ በተባለው መፈንቅለ ስልጣን ታጋይ የነበሩት የትግራይ ተወካይና ም/ፕሬዝደንት ሸኽ ከድር፣ የአዲስ አበባው መጅሊስ ፕሬዝደንት ዶ/ር አህመድ እና የአማራ መጅሊስ ተወካይ አይነተኛ ሚና እንደነበራቸው የታወቀ ሲሆን ከኋላቸውም ዶ/ር ሽፈራውና የደህንነት ሀላፊዎች ሲመሩት ቆይቷል፡፡ የስልጣን ሽኩቻው ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው ጉባኤ ላይም ፈንድቶ እስከመውጣት ደርሶ ነበር፡፡ የሽኩቻው ዋነኛ ምክንያትም ከመንግስት በኩል በግዳጅ ህዝበ ሙስሊሙ ላይ ለመጫን ሲሞከር የነበረው የአህባሽ አስተሳሰብ ዳግም በህዝበ ሙስሊሙ ላይ መጫኑ እንዲቀጥል በሚፈልጉት ወገኖች እና ‹‹ህዝበ ሙስሊሙ ሲቃወመው የነበረው የግዳጅ ጠመቃ ቆሞ መጅሊሱ ሁሉንም ሙስሊም በአንድነት ሰብስቦ እና አቻችሎ መቀጠል አለበት›› በሚሉት ዛሬ ከስልጣን በተወገዱት ሀላፊዎች መካከል ያለው የአቋም ልዩነት መሆኑ ታውቋል፡፡

እስካሁን በነበረው ሂደት የመጅሊሱ ፕሬዝደንት ‹‹መጅሊሱ ህዝበ ሙስሊሙን የሚጠቅም እና በሰላም እንዲኖር የሚያደርግ እንጂ ችግር ውስጥ የሚያስገባ አካል መሆን የለበትም›› የሚል ፅኑ አቋም ይዘው የነበረ ሲሆን በሸኽ ከድር በሚመራው ቡድን እየተደረገ ያለውን ህዝበ ሙስሊሙን ዳግም ወደ ተቃውሞ ሊያስገባ የሚችል ትንኮሳ በመቃወምም ለተለያዩ የመንግስት አካላት ደብዳቤ መፃፋቸው ታውቋል፡፡

በሕገ ወጡ መጅሊስ ውስጥ ከላይ እስከታች የሚታየው የስልጣን ሽኩቻ የተቋሙን አመራር ሕገ ወጥነት አመላካች ከመሆኑም በላይ በመንግስት የተሰጠውን የቤት ስራ ለመፈጸም የተሰባሰበ ቡድን መሆኑንም ክስተቱ እማኝነት ሰጥቷል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃዎችና ማብራሪያዎች በነገው እለት ይኖሩናል - ኢንሻአላህ!

ትግላችን እስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen