Netsanet: ስርአቱን ለመለወጥ ያለንን አንድነትና ፍላጎት በተግባር እናሳይ! መልከት ከተክሌ በቀለ (የአንድነት ም/ሊቀመንበር)

Samstag, 3. Mai 2014

ስርአቱን ለመለወጥ ያለንን አንድነትና ፍላጎት በተግባር እናሳይ! መልከት ከተክሌ በቀለ (የአንድነት ም/ሊቀመንበር)

May 3/2014
ጤና ይስጥልኝ!
Bekele-Tekele
ኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን!
ተክሌ በቀለ እባላለሁ፡፡ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት ነኝ፡፡ የአንድነት የፖለቲካ አላማ ብዝሃነቷ የተጠበቀ፣ የግለሰብና የቡድን መብቶች የተከበሩባት፣ የበለጸገች፤ የአለምን ስልጣኔ እና እድገት የተቀላቀለች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነዉ፡፡ ለዚህ አላማ መሳካትም የምንከተለዉ ስልት ፍፁም ሰላማዊና ህጋዊነትን የተላባሰ አካሄድ ነዉ፡፡ በእዉቀት እና ጥበብ ላይ የተመሰረተ አማራጭ ይዞ በመቅረብ የህዝባችን ድጋፍ በማሰባሰብ ስርአተ መንግስቱን መለወጥ ነዉ፡፡
በስልጣን ላይ ያለዉ ገዥ ቡድን የተለያዩ በስህተት የተሞሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፖሊሲወችን እንደሚከተል ይታወቃል፡፡ የነዚህ የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ዉጤት ደግሞ ዜጎችን ለማፈናቀልና መሬት አልባ መሆን፣የመልካም አስተዳደርና ፍትህ እጦት፣ነፃነት የሰበኩ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎች ለእስር መዳረግ፣በሙስና የበሰበሱ ባለስልጣናትን ማየት፣የእምነት ነፃነት ማጣት፣ለስርአቱ ያላደሩ ሙህራንና ነጋዴዎች ለባይተዋርነት መጋለጥና በሃገራችን የሃሳብ ንጥፈት፣ የወጣቶች ስደትና ስራ አጥነት ወ.ዘ.ተ. መሆኑ ተመዝግቧል፡፡
እኛ ዲሞክራሲ፤ አስተማማኝ ሰላምና ዘላቂ ልማት የሚያስፈልገንና የሚገባን ህዝብ ነን፡፡ የአምነተት ነጻነት፤ጠመጻፍና የመናገር እንዲሁም የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰለፍ የመድረግ መብት ይገባናል፡፡ፍትህና እኩል ተጠቃሚ መሆን የዜግነት ኢትየጵያዊ መብታችን ነዉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒዉ የኢህአዴግ አገዛዝ ከተሳሳቱ ፖሊሲዎቹ ከሚመነጩት ችግሮች የተነሳ አገሪቱንና ህዝቧን ወደ አለመረጋጋት እየመራት በመሆኑ በቃህ ልንለዉ ይገባል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በይበልጥ እየተባባሰ ለመጣዉ ቀዉስ ተጠያቂዉ ኢህአዴግ ነዉ፡፡
ህዝቡ በአደባባዮች በነቂስ በመዉጣት ያለዉን ተቃዉሞ እንዲያሰማ አንድነት ሰላማዊ፤ ህጋዊና የተፈቀደ የሰላማዊ ሰልፍ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ እሁድ ሚያዚያ 26 ቀን በመዲናችን በአዲስአበባና በደቡብ ክልል በደራሼ ወረዳ ጊዶሌ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል፡፡ በከተሞች ዉስጥና በአካባቢዉ የሚኖረዉ ህዝብ በነቂስ በመዉጣት ብሶቱን እንዲያሰማ በአክብሮት ጥሪ አቀርባለሁ፡፡
ከተለያየን የነፃነት ዋጋዉ ከፍ ይላል፤የነፃነት ጊዜዉም ይረዝማል፡፡ ከተዋሃድን፤ከተባበርንና ከተቀናጀን ሸክሙ ይቀላል፡፡ አዎ! ፍቅር ያሸንፋል! በየማዕዘኑ በገዥዉ ቡድን በትር የምንቀጠቀጥ ሁሉ እንተባበርና ስርአቱን ለመለወጥ ያለንን አንድነትና ፍላጎት በተግባር እናሳይ! ሚያዚያ 26/2006 ዓ.ም በተጠቀሱት የሰልፍ ቦታዎች ላይ ይገኙ ዘንድ ደግሜ የክብር ጥሪ አስተላልፋሁ፡፡
ፈጣሪ አገራችንና ህዝባችንን ይባርክ!!
ተክሌ በቀለ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen