May 2/2014
(ርዕሰ አንቀጽ)
May 3/2014
May 3/2014
አሁን ከኢህአዴግ ጋር ገድለሃል አልገደልክም የሚል ክርክር የለም። ራሱ ባንደበቱ “ገድያለሁ” ብሏል። ነፍስ ማጥፋቱን አውጇል። ያልገለጸው በጸጥታና በስም እንጂ አንጋቾቹ ህይወት መቅጠፋቸውን አረጋግጧል። ግድያው በዚህ ስለማብቃቱ ማረጋገጫ አልተሰጠም። ተቃውሞውም እየቀጠለ ነው። ከዚያስ? በደም እየታጠቡ፣ ወንጀልን እያባዙና የደም ጎርፍ እየጎረፈ “ህግ” ማስከበር እስከመቼ ያስኬዳል። ያዋጣልስ? የህዝብ እንባስ እንዲሁ ከንቱ ይቀራል?
በርግጥ ህግ ማፍረስ አይደገፍም። ህግ መከበር አለበት። ከሁሉም በላይ ደግሞ ህገመንግስት ክቡር የመተዳደሪያ ዋስትና በመሆኑ ሊናድ አይገባውም። ህግን የማክበርና የማስከበር ጥያቄ አይለያዩም። ኢህአዴግ እንዳሻው የሚምልበትን ህገ መንግሥት እየጨፈላለቀና እየጎራረደ ሌሎች ህግ እንዲያከብሩ መጠየቅ ለምዶበታል። ሰዎች መብታቸውን እንዲለማመዱ አይወድም። ይህ ችግሩ በደም የታጠበ፣ የደም እዳ ያለበት፣ ታሪኩ ሁሉ ከደም ጋር የተሳሰረ እንዲሆን አድርጎታል። እስኪ ወደ ዛሬው ጉዳይ እናምራ!
አልታደልንም
ህዝብን የሚያከብር፣ ለህዝብ ቅድሚያ የሚሰጥ፣ በህዝብ የሚምል፣ ህዝብ ውስጥ የሚኖር፣ ህዝብ እውቅና የሰጠው፣ ህዝብ የሚያምነው፣ ሲፈልግ የሚቀጣው፣ ሲፈልግ የሚያሞግሰው አስተዳደር አጋጥሞን አያውቅም። የቀደመውን ኮንኖ የሚመጣው ከቀደመው የማይሻል፣ ደም የጠማው፣ ጠመንጃ አምላኩ የሆነ አገዛዝ ነው። አገሪቱም፣ ትውልዱም፣ የወደፊቱ እንግዳ ዘርም ሁሉም በስህተት ቅብብል በርግማን ይኖራሉ። ነፍጠኛ፣ ትምክተኛ፣ ጎጠኛ፣ ጠባብ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ አንጃ … ቃላት እንደ ፋብሪካ ምርት እየተፈበረኩልን ስንሰዳደብ እንኖራለን። የሁሉም አስተሳሰብ አንድ ብቻ ነው – የራሱን ህልውና ለማስፈን የሚቃወሙትን ሁሉ መደምሰስ! “በጠላቶቻችን መቃብር ላይ …” የሚለው መፈክር ደርግ ቢለውም የራሱ በማድረግ አንግቦ የሚዞረው ግን እጅግ በርካታ ነው፡፡
ኢህአዴግ ተቃውሞና የተቃውሞ ድምጽ ያስበረግገዋል?
አዎ!! ኢህአዴግ የተቃውሞ ድምጽ ሲሰማ ይርዳል። የተቃውሞ ድምጽ ሲሰማ ይንቀጠቀጣል። ሲቃወሙት የበረሃ ወባው ይነሳበታል። ከድንጋጤው የተነሳ ይበረግጋል። ይደነብራል። ለምን? ቢባል በደም የተለወሰ ፓርቲ ስለሆነ ነው። ኢህአዴግ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ነፍስ ያላጠፋበት ስፍራ የለም። በመሀል አገር ክቡር የሰው ልጆችን ገሏል። የሚደመደም ነገር ባይኖርም በበላዮቹ ትዕዛዝ ኢህአዴግ ባፈሰሰው ደም መጠን ጠላት አፍርቷል። ወዳጁና አጋሩ ጠብመንጃና በደም የለወሳቸው አባላቱ ብቻ ናቸው። ሌላ ወዳጁ እንዳሻው የሚዘራው የአገሪቱ ሃብት ነው። የህዝብ ሃብት ህዝብን ለማፈን ማዋል!! ሌላው ስጋቱን ለመጥቀስ እንጂ ከዝርፊያ ጋር የተቆራኘውን ታሪኩን ለመዘርዘር አይደለም። ስለዚህ ህዝብ ሲቃወም ያጥወለውለዋል። ይጓጉጠዋል። አውሬ ይሆናል። ህግና ስርዓት አፍርሶ የጫካ ደንብ ይተገብራል። ባጭሩ ይገላል!!
ኢህአዴግ በበረገገ ቁጥር እንሰጋለን!!
ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ገዢ ነኝ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ህዝብን ያስቀየሙ፣ ያሳዘኑና፣ ያሳፈሩና ቂም ያስቋጠሩ ተግባራትን በግልጽና “በድብቅ ግን የሚታወቅ” አከናውኗል። በተለያዩ ጊዜያት በተግባሩ የተነሳበትን ተቃውሞ ለማፈን ሃይል ተጠቅሟል። አልሞ ተኳሾችን አሰማርቶ ዜጎችን ልባቸውና ግባራቸው አየተመታ እንዲገደሉ አድርጓል። የሚችለውን ያህል አስሯል። ገርፏል። ራሱ ክስ መስርቶ ራሱ እየፈረደ ወህኒ ወርውሯል። ነጻ ፕሬስን ሰቅሎታል። ሃሳብን በነጻ ማራመድን በህግና ህግ በማይጠቀስበት አግባብ አግቷል።
አሁን ኦሮሚያ ላይ የተነሳውን የተቃውሞ አመጽ ተከትሎ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ በጥበብ ከማስተናገድ ይልቅ ብረት አንስቶ መግደልን መርጧል። ኢህአዴግ በገደለ ቁጥር አገሪቱ ስጋቷ እየጨመረ፣ የህዝብ ስሜት እየተበላሸ ነው። ይህ እንደሚዲያ ያስጨንቀናል። ኢህአዴግ የዘራው የቂም ዘር በየአቅጣጫው ፍሬው እየጎመራ መሄዱ ያሳዝነናል። ከሁሉም አቅጣጫ መፍትሔ የሚፈልግና ችግር የሚያረግብ አይታይም። አገሪቱ አስተዋይ በማጣቷ በስጋት ደመና እየነፈረች ነው። የአንዱ ለቅሶ ለሌላው ደስታ እየሆነ ነው። ከዚህ በላይ የሚያስጨንቅ ምን አለ? አማራው፣ ደቡብ ክልል ያሉ ዜጎች፣ ኦጋዴን፣ ሶማሌ፣ ሁሉም ጋር ብሶት አለ። የኑሮ ችግር የጠበሳቸው የበይ ተመልካቾች መሯቸዋል። ያልመረራቸው ቢኖሩ ከቁጥር የማይገቡ ባለጊዜዎች ብቻ ናቸው። ይህም ታላቅ ስጋት ነው!!
ምን ይደረግ?
አሁን በኦሮሚያ የተነሳውን የባለቤትነት ጥያቄ ማክበር አማራጭ የለውም። ጸረ ሰላም ሃይሎች ከአመጹ ጀርባ አሉ በሚል መፎከርና ችግሩን ማድበስበስ አያዋጣም። የድሃውን መሬት መቀራመትና መቸብቸብ ይቁም። አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ብቻ የተመሰረተው የመኖር ተስፋው ይከበርለት። ይህ ሁሉ የኢህአዴግ የመሬት ፖሊሲ ጣጣ ያመጣው ነውና ይታሰብበት። ኢህአዴግ የድሃውን ገበሬ መሬት ከመሸጥ ይቆጠብ። መቃወም ህጋዊ መብት ስለሆነ ኢህአዴግ ተቃውሞን ከመፍራትና እመራቸዋለሁ የሚላቸውን ወገኖች ከመግደል ይልቅ ህዝብን የሚያስቆጣ ተግባር ከመፈጸም ራሱን ያቅብ። “አዲስ የልማት ዘዴ ዘይጃለሁ” ሲል የጉዳዩን ባለቤት በቅድሚያ ያሳምን። ህዝብ ተቃውሞውን ሲገልጸ እየበረገጉ በደም መታጠብ ቆይቶም ቢሆን ዋጋ ያስከፍላልና ይታሰብበት። የጠብ መንጃ ሰላም ዋስትና ቢኖረው ኖሮ ኢህአዴግ እስካሁን ያፈሰሰው ደም በበቃው ነበር። እናም ቅድሚያ ለህዝብ ክብርና ለህግ!! ታሪክ በግልጽ መስክሯል – አውሬነት ለማንም አይበጅምና!!
ጎልጉል
ጎልጉል
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen