May 15/2014
የአሜሪካ የዕርዳታና የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ኤድስ ሪሶርስ ሴንተር (ኤአርሲ) ተግባራዊ ያደርጋቸው ለነበሩ ፕሮጀክቶች ይለቅ የነበረውን ፈንድ በግብረ ሰዶማዊያን ላይ አይሠሩም በሚል በድንገት ማቋረጡን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በፈንዱ መቋረጥ ምክንያት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎችን ሕይወት የሚያስቃኘውና ቤተኛ የተሰኘውና ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሆኑ የኅብረተሰብ ክፍል ወጣቶች ላይ የሚያተኩረው ዳጉ የሬዲዮ ፕሮግራሞች በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ የተቋረጡ ሲሆን፣ ሌሎችም የኤድስ ሪሶርስ ሴንተር ፕሮግራሞች እየታጠፉ መሆናቸውን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
የኤአርሲ ፕሮጀክቶች እ.ኤ.አ. እስከ 2016/17 መዝለቅ ሲጠበቅባቸው የፈንዱ በድንገት መቆም እስከዛሬ የኤችአይቪ ሥርጭትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ፕሮግራሞችን ማቋረጡ ለረዥም ጊዜ የተገኘውን ውጤት ወደኋላ መመለስ እንደሚሆን ምንጮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በለጋሾች በኩል የኤችአይቪን ሥርጭት ለመግታት የሚሠሩ ሥራዎችን በሚመለከት የትኩረት አቅጣጫ ለውጥ መኖሩን፣ እዚህ ደረጃ የደረሱ ፕሮጀክቶችን ከዚህ ወዲያ መንግሥት ተረክቦ ያስቀጥል የሚል አቋም መኖሩን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ፕሮጀክቶቹን መንግሥት የራሱ እንዲያደርግ ተገቢ የሽግግር ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ በዩኤስኤአይዲና በፌደራል የኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያና ጽሕፈት ቤት (ሀፕኮ) ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ቢሆንም በድንገት በዩኤስኤአይዲ ብዙዎቹ የኤድስ ሪሶርስ ሴንተር ፕሮጀክቶች ባለፈውና በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ማብቂያ ላይ እንዲቋረጡ ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ የፕሮጀክቶች ሽግግር በዕቅድ የተመራ፣ ስትራቴጂካዊና የአገሪቱን ፍላጐት ያገናዘበ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያና የአሜሪካ መንግሥት የተፈራረሙት የአጋርነት ማዕቀፍ ላይ የተቀመጡ ስምምነቶችን የሚፃረር መሆኑን ምንጮቹ ያስረዳሉ፡፡
የኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት መንግሥት ፕሮጀክቶቹን ለመቀበል ዝግጁ አለመሆኑንና የፕሮጀክቶቹን ሽግግር በሚመለከትም ግልጽ የሆነ ዕቅድ ማስፈለጉን ለለጋሾቹ አሳውቆም ነበር፡፡
ዩኤስኤአይዲ ኤችአይቪን በሚመለከት ከሚሠሩ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት ትኩረት የሚሰጠው አጠቃላይ ሕዝብን ሳይሆን ተጋላጭ የሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ለሚያደርጉ መሆኑን፣ በዚህ ረገድ ተለይተው የተቀመጡት ሴተኛ አዳሪዎችና ግብረ ሰዶማዊያን መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የኤችአይቪ ድጋፍ (PEPFAR) ፕሮግራሞች የኤችአይቪን የሥርጭት አቅጣጫ ተከትለው ይሄዱ ዘንድ ግፊት እየተደረገ መሆኑን፣ የፔፕፋር የኢትዮጵያ ቢሮ ለሀፕኮ አሳውቆ ነበር፡፡ የፕሮግራሞችን መቋረጥ በሚመለከት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሽያ ሀስላክና የሀፕኮ ኃላፊዎች ረዥም ውይይት ቢያደርጉም ምንም ዓይነት ውጤት ላይ መድረስ አለመቻሉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹን ተግባራዊ ያደርግ የነበረው የኤድስ ሪሶርስ ሴንተር ኃላፊ አቶ ጋሻው መንግሥቱ ቢሯቸው በገንዘብ እጥረት ምክንያት ብዙ ፕሮጀክቶችን መዝጋቱንና በርካታ ሠራተኞችን መቀነሱን ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡ ታጥፈው እንዲቀጥሉ እየተደረጉ ያሉ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም ከአንድ ዓመት በላይ የሚዘልቁ አይደሉም፡፡
እ.ኤ.አ. በ2002 በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ሥራ የጀመረው ኤድስ ሪሶርስ ሴንተር በአገሪቱ የሚካሄዱትን የኤችአይቪ ፕሮግራሞች ለማገዝ ከ18 በላይ ፕሮጀክቶች የነበሩት ቢሆንም፣ አሁን ብዙዎቹ በመዘጋት ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 952 ወገን ኤድስ ቶክላይን ሰዎች መረጃና የምክር አገልግሎት የሚያገኙበት ነፃ የስልክ ጥሪ መስመሮች የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አቅሙን ቀንሶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ፈንዱ በድንገት በመቋረጡ ምክንያት ሠራተኞቹም በግማሽ መቀነሳቸው ታውቋል፡፡
ፕሮጀክቶቹን በድንገት ለማቆም በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው የኤችአይቪ ሥርጭት አቅጣጫ በቀጣይ ለሚሠራው ሥራ መሪ መሆን አለበት የሚል መከራከሪያ በዩኤስኤአይዲ በኩል መቅረቡን የሀፕኮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፈይሣ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ የፕሮጀክቶቹን መቋረጥ በሚመለከት ሚኒስትሩ የተገኙበት ሰፊ ድርድር ስለመደረጉ ግን የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ቢገልጹም፣ ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች ድርድሩ በእርግጥም ስለመካሄዱ ያስረዳሉ፡፡ ጉዳዩን በሚመለከት ማብራሪያ የተጠየቁት የአሜሪካ ኤምባሲ የኢንፎርሜሽንና ሚዲያ ጉዳዮች ኦፊሰር ካትሪን ዲዮፕ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ጋር በተደረገ ውይይት ብዙዎቹን ኤችአይቪን የሚመለከቱ ፕሮጀክቶች ለመንግሥት ለማስረከብ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ቤተኛንና ሌሎች የኤድስ ሪሶርስ ሴንተርን የመሰሉ ውጤታማ ፕሮጀክቶችን መንግሥት ያስቀጥላቸዋል ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት የአሜሪካ መንግሥት በፔፕፋር በኩል በኢትዮጵያ ኤችአይቪን ለመዋጋት ሁለት ቢሊዮን ዶላር መለገሱ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቤተኛ የተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራም ቀደም ሲል ፕሮግራሙ ላይ ይሠሩ በነበሩ ጋዜጠኞች የግል ጥረት በሌላ ስፖንሰር ድጋፍ መቀጠል ችሏል፡፡ Reporter Amharic.
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen