Netsanet: በጨው ባህር በተቆፈረ ጉድጓድ ነዳጅ አልተገኘም

Sonntag, 25. Mai 2014

በጨው ባህር በተቆፈረ ጉድጓድ ነዳጅ አልተገኘም

May 25/2014
በደቡብ ኦሞ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ በማካሄድ ላይ የሚገኘው ታሎ ኦይል በጨው ባህር አካባቢ በቆፈረው የፍለጋ ጉድጓድ ነዳጅ አለማግኘቱ ታወቀ፡፡
ታሎ ‘‘ሺመላ 1’’ ተብሎ የተሰየመውን የፍለጋ ጉድጓድ ባለፈው መጋቢት ወር ነበር መቆፈር የጀመረው፡፡ ይህ በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመርና በና ፀማይ ወረዳዎች የተቆፈረው የፍለጋ ጉድጓድ 1,940 ሜትር ጥልቀት አለው፡፡ ኩባንያው በቅርቡ በጉድጓድ ውስጥ ባካሄደው ሙከራ ነዳጅ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
ታሎ ባለፈው ዓርብ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ በሺመላ ጉድጓድ ውስጥ ያገኘው ውኃ አቋሪ ማጠራቀሚያዎች (Resevoirs) እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የጨው ባህር አካባቢ የነዳጅ ክምችት መኖሩን ለማወቅ በተቆፈረው የፍለጋ ጉድጓድ ውስጥ ላከስትራይን፣ የእሳተ ገሞራ አለቶች፣ 100 ሜትር ውፍረት ያላቸው አሸዋማ አለቶች (Sand Stone Resevoir) እና የሸክላ ድንጋዮች ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ኩባንያው በ1,900 ሜትር ጥልቀት ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ ምልክት መታየቱን ገልጿል፡፡ በቀጣይ ‘‘ጋርዲም 1’’ የተሰኘ ጉድጓድ ለመቆፈር መዘጋጀቱንና የመቆፈሪያ ማሽኑንም ወደዚያው እንደሚያንቀሳቅስ ታሎ አስታውቋል፡፡
የታሎ ኦይል ኤክስፕሎሬሽን ዳይሬክተር ሚስተር አንገስ ማኮስ፣ ‹‹ምንም እንኳ በሺመላ ጉድጓድ ውስጥ የጋዝ ምልክት ብቻ ቢታይም፣ ስለጨው ባህር አካባቢ የከርሰ ምድር አፈጣጠር ግንዛቤ እንዲኖረን የሚረዱ ጠቃሚ መረጃዎች አግኝተናል፤›› ብለዋል፡፡ የሺመላ ጉድጓድ የተቆፈረው በጨው ባህር ቤዚን ሰሜን ምዕራብ ሲሆን ጋርዲም 1 የሚቆፈረው በጨው ባህር ቤዚን ደቡብ ምሥራቅ ክፍል ይሆናል፡፡ በሺመላ የተገኘው ውጤት በጋርዲም 1 ቁፋሮ ሥራ ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ሚስተር ማኮስ አስረድተዋል፡፡
ጋርዲም 1 ለታሎ አራተኛው የፍለጋ ጉድጓድ ይሆናል፡፡ ቀደም ሲል ኩባንያው በደቡብ ኦሞ ኦኮራቴ ከተማ አቅራቢያ ሳቢሳ 1 እና ቱልቱሌ 1 የተሰኙ ሁለት ጉድጓዶች መቆፈሩ ይታወሳል፡፡ በሳቢሳ 1 የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ምልክቶች የታዩ ቢሆንም፣ በቱልቱሌ 1 ግን ምንም ዓይነት የነዳጅ ምልክት ሳይታይ ቀርቷል፡፡
ታሎ እስካሁን ለነዳጅ ፍለጋ ሥራው ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዳወጣ ይገመታል፡፡ ኩባንያው በኬንያ ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ የተፈጥሮ ዘይት ክምችት አግኝቷል፡፡ በተመሳሳይ በኡጋንዳና በጋና ከፍተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ዘይት ክምችት ያገኘ በመሆኑ፣ ኩባንያው ካለው ውጤታማ የነዳጅ ፍለጋ ታሪክ አንፃር በደቡብ ኦሞ ነዳጅ ያገኛል የሚል ከፍተኛ እምነት ተጥሎበት ነበር፡፡ እስካሁን በቆፈራቸው ሦስት ጉድጓዶች ምንም ዓይነት የነዳጅ ክምችት አለማግኘቱ ባለሙያዎችን እያነጋገረ ነው፡፡
ኩባንያው በቀጣይ በሚቆፍረው ጉድጓድ ውስጥ ነዳጅ ካላገኘ የፍለጋ ሥራውን አቋርጦ ሊወጣ እንደሚችል አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የፔትሮሊየም ባለሙያ በሦስት ጉድጓድ ውስጥ ነዳጅ አልተገኘም ማለት በደቡብ ኦሞ ነዳጅ የለም ብሎ ማጠቃለል እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከወጪና አቅም ጋር በተያያዘ ኩባንያው በጋርዲም 1 ነዳጅ ካላገኘ በኮንሴሽኑ (የነዳጅ ፍለጋ ይዞታ) ላይ ያለውን ድርሻ ሸጦ ሊወጣ እንደሚችል ባለሙያው አክለዋል፡፡ ‹‹ሁለተኛው አማራጭ አዲስ የሴስሚክ መረጃዎችን በመሰብሰብ ተጨማሪ የፍለጋ ጉድጓዶች መቆፈር ነው፤›› ብለዋል ባለሙያው፡፡ ኩባንያው በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
ታሎ ኦይል ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በደቡብ ኦሞ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ታሎ በደቡብ ኦሞ የነዳጅ ፍለጋ ይዞታ 50 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ አፍሪካ ኦይል የተሰኘው የካናዳ ኩባንያ 30 በመቶ፣ ማራቶን ኦይል የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ 20 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ የፍለጋ ሥራውን በዋነኝነት የሚያካሂደው ታሎ ኦይል እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቅርቡ የማዕድን ሚኒስቴር ባዘጋጀው የሁለት ቀናት ዓውደ ጥናት ላይ በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ማብራሪያ የሰጡት የፔትሮሊየም ፈቃድ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቀፀላ ታደሰ፣ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ጊዜ የሚወስድ ፈታኝ ሥራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በጐረቤት ኬንያ ነዳጅ የተገኘው ታዋቂ የሆኑት እነ ሞቢል ኤክሶን፣ አሞኮና ብሪቲሽ ፔትሮሊየም ኬንያ ውስጥ ነዳጅ የለም ብለው ተስፋ ቆርጠው ከወጡ በኋላ ነው፤›› ሲሉ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ውስብስብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ስድስት ኩባንያዎች (ታሎ ኦይል፣ አፍሪካ ኦይል፣ ኒው ኤጅ፣ ፋልከን ፔትሮሊየም፣ ሳውዝ ዌስት ኢነርጂና ፖሊ ጂሲኤል) የነዳጅ ፍለጋ ሥራ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ 
Reporter Amharic, 
25 MAY 2014 ተጻፈ በ ቃለየሱስ በቀለ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen