May 3/2014
ሃብታሙ አያሌው እባላለሁ። የአንድነት ለዲምክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙንተ ክፍል ሃላፊና የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ነኝ። የሚሊዮን ድምጽ ንቅናቄ በአንድነት ፖርቲ ቢጀመርም ንቅናቄው የሚሊዮኖች ንቅናቄ ነው። የዴሞክራሲ፣ የስላም፥ የፍትህ፣ የነጻነትነ የአገር አንድነት ጥያቄ የአንድነት ፓርቲ ብቻ ሳይሆነ የእያንዳንዱ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነው።
በአገራችን ኢትዮጵያ የመጻፍና የመናገር ነጻነት፣ የሃይማኖት ነጻነት፣ የመሬት ባለቤትነት ነጻነት የመሳሰሉት መሰረታዊ የሰብባአዊ መብቶች የሚናዱባትና የማይከበሩባት አገር ናት። በየቦታው ያለዉን ችግር እያንዳንዳች እናውቀዋለን። የተሳሳቱ የአገዛዙ ፖሊሲዎችን እናውቃቸዋለን። ለምን ቢባል ፣ በፖሊሲዎች ምክንያት፣ እየተፈናቀል፣ ወደ ወህኒ እየተወረወርን፣ ከስራችን እየተባረርን፣ በኑሪ ዉድነት እየተቃጠልን፣ ስቃይ እየደረሰንብን እያለው እኛው በመሆናችን። አዎን፣ ኢትዮጵያ ለጥቂቶች ገነት ለብዙዎቻችን ግን ሶሆል የሆነችበት አገር ናት።
ይህ መቆም አለበት። አንገታችንን ደፍተን ተዋርደን፣ በአገራችን ተንቀን የምንኖርበት ዘመን ማቆም አለበት። ይሄንን የግፍ ቀንበር ማቆም የሚችለው፣ ሌላ ማንም አይደለም፣ እኔና እናንተ ነን። እኛ ኢትዮጵያዉያን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ ባለስልጣናትን ተጠያቂ ማድረግ ስንጀርም፣ ያኔ የአምባገነንነት መጨረሻ ይሆናል። እኛ መብታችንን ለማስከበር በፈራንና በዘገየን ቁጥር ፣ ያኔ የግፍ አገዛዙ ይቀጥላል።
የአንድነት ፓርቲ፣ በሕዝብ ጉልበት የሚያምን እንደመሆኑ፣ ህዝቡ ድምጹን እንዲያሰማ፣ መድረክ ያገኝ ዘንድ፣ ሁለት ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎችን በአዲስ አበባ እና በደራሼ/ጊዶሎ አዘጋጅቷል። ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት አስፈላጊዉን የእውቃን ደብዳቤም አግኝቷል።
እንግዲህ የነጻነትን ጉዞ አብረን እንድንጀምር በትህትና እጠይቃለሁ። ለአመታት የተከናነብነውን የፍርሃት ካባ አዉልቀን፣ ሚያዚያ 26 ቀን በአዲስ አበባ እና በጊዶሌ በሚደረጉ ሰላማዊና ሕዝባዊ ሰልፍች በነቂስ እንዉጣ። ድምጻችንን እናሰማ። ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን።
ነጻነት ነጻ አይደለችም። ዝምታን የምንመርጥ ከሆነ፣ የድርሻችንን ለማበርከት እጆቻችንን ካልዘረጋን፣ ነጻነት በራሷ ተራምዳ ወደ እኛ እንድትመጣ አንጠብቅ።
እንግዲህ ለሃያ አመታት ከባለስልጣናት ብቻ ስንሰማ ኖረናል። አሁን ባለስልጣናት ከሕዝቡ የሚሰሙብት ፣ ሕዝቡም ቀና ብሎ የሚናገርበት ጊዜ ይሁን። የነጻነት ደዉል የሚደወልበት ጊዜ ይሁን።
እግዚአብሄር አገራችንን ይባርካት !
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen