Netsanet: በኢትዮጵያ 97.8 በመቶ ዜጎች ኢንተርኔት አያገኙም።

Mittwoch, 8. Oktober 2014

በኢትዮጵያ 97.8 በመቶ ዜጎች ኢንተርኔት አያገኙም።

ኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ በዋለባቸው ያለፉት ሁለት ዐሠርተ- ዓመታት ውስጥ በዓለም ሕዝብ ፤ መንግሥታትና ተቋማት የርስ በርስ ግንኙነት ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ፈጥሯል። ቴክኖሎጂው አዳዲስ ግኝቶችንና ፈጠራዎችን በማበረታታት ሃገራት ዓመታዊ የምርት መጠናቸውን (GDP) እንዲያሳድጉ በር ከፍቷል።
ሁሉም ሃገራት፤የዓለም ሕዝብና ተቋማት ግን ከዚህ ቴክኖሎጂ ትሩፋቶች የመቋደስ እድልን እኩል አላገኙም። በዓለም ዙሪያ የሃገራትን የኢንተርኔት አገልግሎት አስመልክቶ ማኪንዜይ የተሰኘ ኩባንያ ሰሞኑን ዘገባ አቅርቦዋል።
ተቀማጭነቱን በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ያደረገውና የአስተዳደርና የማማከር ሥራዎችን የሚሠራው ማኪንዜይ የተሰነ ኩባንያ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት ከዓለም ሕዝብ 4.4 ቢሊዮን ያህሉ አሁንም የኢንተርኔት አገልግሎትን ማግኘት እንዳልቻለ ይጠቁማል።ከእነዚህ ሰዎች መካከል 25 በመቶው ህንዳውያን ናቸው።በዚህ ሪፖርት መሰረት በቻይና 730 ሚሊዮን፤በኢንዶኔዥያ 210 ሚሊዮን በባንግላዴሽ 150 ሚሊዮን እና በብራዚል 100ሚሊዮን ሰዎች ይህን አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም።
ከአንድ ሃገር አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር አንጻር ደግሞ ማይናማር እጅግ ዝቅተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ያላት መሆኗን የማኬንዚ ኩባንያ ሪፖርት ይጠቁማል። ከደቡብ ምስራቅ እስያዋ ሃገር ዜጎች 99.5 በመቶው ይህን የዘመናዊ ዓለም ቴክኖሎጂ የመጠቀም እድል የላቸውም። ከማይናማር ቀጥሎ በዝቅተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ኢትዮጵያ ሠፍራለች። በኢትዮጵያ 97.8በመቶ ዜጎች ኢንተርኔት አያገኙም።
አቶ ዮሴፍ አባተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣ «ክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሳይንቲፊክ ኮምፒውቲንግ» ማዕከል ኀላፊ ናቸው። ኀላፊው የማኪንዜይ ኩባንያ ያወጣውን ሪፖርት ከዓለም አቀፉ የቴሌኮምዩንኬሽን ማሕበርና የኢትዮጵያ መንግሥት መረጃዎች ጋር አነጻጽረውት ነበር።
ኢትዮ-ቴሌኮም በኢትዮጵያ ብቸኛው የአገልግሎት አቅራቢ ሆኖ ዘልቋል። መንግስት አገልግሎቱን ለማሳደግ የማስፋፊያ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ቢናገርም እስካሁን ጠብ የሚል ነገር አልታየም።
የሃገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት በአቅርቦት ጥራትና ፍጥነት በርካታ ትችት ሲሰነዘርበት ይደመጣል። የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮም ገበያውን ለውድድር ክፍት እንዲያደርግ ቢወተውቱም ሰሚ ያገኙ አይመስልም። የኢንተትኔት አገልግሎትን በመላ ሃገሪቱ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት አለመስፋፋት በሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ላይ ተጽዕኖ እንዳለው አቶ ዮሴፍ አባተ ይናገራሉ።
የኢንተርኔት አገልግሎት አዎንታዊም አሉታዊም ጥቅም አለው የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ አቶ ዮሴፍ አባተ አዲሱ ትውልድ አገልግሎቱን በአግባቡ መጠቀም ከቻለ በሌላው ዓለም የሚታዩ ሥራዎች መሥራት ይቻላል ይላሉ።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen