Netsanet: አንድነት በፖለቲካ እስረኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አወገዘ

Donnerstag, 30. Oktober 2014

አንድነት በፖለቲካ እስረኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አወገዘ



• ‹‹ማዕከላዊ የታሰሩት የፓርቲው አመራሮች መጸዳጃ ቤት ተከልክለዋል››

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጥቅምት 20/2007 ዓ.ም በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በፖለቲካ እስረኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ኢ-ሰአብአዊ ድርጊት አወገዘ፡፡ ‹‹የኢህአዴግ አገዛዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰብአዊ መብት በመጣስና ዜጎችን በማሰቃየት ወደር የሌለው ሆኗል›› ያለው መግለጫው፣ ስርዓቱ ለስልጣኑ ያሰጉኛል ያላቸውን የፖለቲካ አመራሮች፣ ጦማሪያንና ጋዜጠኞችን ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ክስ በመመስረት ማሰሩ ሳያንስ እነዚህን ዜጎች ሰብአዊ ክብራቸውን በመድፈር ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል ብሏል፡፡

መግለጫው አክሎም የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አቶ ሀብታሙ አያሌውና ም/ድርጅት ጉዳይ ኃላፊው አቶ ዳንኤል ሺበሺ በማዕከላዊ እስር ቤት አንድ ሰው ይፈጽመዋል ተብሎ የማይጠበቅ ኢሰብአዊ ድርጊት እየተፈጸመባቸው ነው ሲል ስርዓቱን ወቅሷል፡፡ 

‹‹ሀብታሙ አያሌው ለአንድ ሳምንት የታሰረበት ክፍል ውስጥ እንዲጸዳዳ በማድረግና ለሶስት ቀን ጨለማ ክፍል ውስጥ በማሰር የበቀል በትራቸውን እያሳረፉበት እንደሆነ አውቀናል፡፡ ....አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከከፍተኛ ዛቻና ስድብ በተጨማሪ የታፈነ ክፍል ውስጥ እንዲቀመጥ በመደረጉ ለተቅማጥና ለሌሎች በሽታዎች መዳረጉ፣ ወደ መጸዳጃ ቤት እንዳይሄድ›› መከልከሉን በመግለጽ ማዕከላዊ ታስረው የሚገኙ የአንድነት አመራሮች እየደረሰባቸው ያለውን በደል አስረድቷል፡፡ 

አዲሱ የአንድነት ፕሬዝዳንት አቶ በላይ ፍቃዱ ይህ በእስረኞቹ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በጥላቻ የሚፈጸምና ትውልዱ ሊወርሰው የማይገባ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ይህን የበደል ዘመን ለማሳጠር እንዲቻል ህዝቡ በቁጭት ለለውጥ እንዲነሳ›› ሲልም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen