Netsanet: ኢትዮጵያ ከመከላከያ ኢንዱስትሪና ከኃይል ማመንጨት ውጪ ያሉ ዘርፎችን ክፍት እንድታደርግ አይኤምኤፍ አሳሰበ

Donnerstag, 9. Oktober 2014

ኢትዮጵያ ከመከላከያ ኢንዱስትሪና ከኃይል ማመንጨት ውጪ ያሉ ዘርፎችን ክፍት እንድታደርግ አይኤምኤፍ አሳሰበ

በቅርብ ዓመታት የገንዘብ እጥረት ይገጥማታል አለ
-ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ገበያ ቦንድ ልትሸጥ ነው
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሲገመግም የቆየው የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቡድን ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለግሉ ዘርፍና ለውጭ ባለሀብቶች ብትከፍት አሁን ካለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የበለጠ ተጠቃሚ እንደምትሆን አስታወቀ፡፡

የግምገማውን ይፋዊ ሪፖርት ያወጣው አይኤምኤፍ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ዘርፍንና የመከላከያ ኢንዱስትሪን ለጊዜው በመያዝ፣ ሌሎቹን የኢኮኖሚ ዘርፎች ክፍት ብታደርግ ተጠቃሚ ትሆናለች የሚል ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል፡፡
አይኤምኤፍ ከዚህ ቀደም የቴሌኮሙዩኒኬሽንና የባንክ ዘርፍ ነፃ እንዲሆን በተደጋጋሚ የጠየቀ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሪፖርቱ ግን ተጨማሪ ዘርፎችንም አካቷል፡፡ የትራንስፖርት፣ የሎጂስቲክስ፣ የስኳር ዘርፎች ለግል ባለሀብቶችና ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡ ይህ ተግባራዊ ቢሆን አገሪቱ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስገባትና የአገር ውስጥ አቅምና ጥረትን በማጎልበት ረገድ ተጠቃሚ እንደምትሆን አስረድቷል፡፡
የአይኤምኤፍ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቡድን በኢትዮጵያ ቆይታው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወደፊትም በጥንካሬው የሚቀጥል ቢሆንም፣ የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሚገጥሙት ባወጣው ሪፖርት ይገልጻል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለከፍተኛ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የሚውል የገንዘብ እጥረት እንደሚገጥመው፣ በዓለም አቀፍ የገበያ አለመረጋጋቶች በሚፈጥሩት የዋጋ መቀነስ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሊገጥም እንደሚችልና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል አትቷል፡፡
ከፍተኛ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የፋይናንስ እጥረት ሊገጥማቸው ይችላል ካለባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ የመንግሥት የመሠረተ ልማት ተቋማት በራሳቸው እያገኙት ያለው የአገር ውስጥና የውጭ ብድር የሚፈጥረው ጫና ነው፡፡
ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከሁለት የቻይናና የቱርክ ኩባንያዎች ጋር የ3.9 ቢሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ስምምነት መፈራረሙን፣ በተመሳሳይም ኢትዮ ቴሌኮም 1.6 ቢሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ስምምነት ከቻይና ቴሌኮም ኩባንያዎች ጋር መፈራረሙን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ እነዚህና ሌሎች የመሠረተ ልማት ተቋሞች በብድር ለኢንቨስትመንት የሚያወጡት ከፍተኛ ገንዘብን መንግሥት እንደ ራሱ የውጭ ዕዳ ቆጥሮ መከታተል ካልተቻለ፣ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ መገንዘብ ያስቸግራል ሲል አሳስቧል፡፡
ከአይኤምኤፍ ቡድን አባላት ጋር የተወያዩት የመንግሥት ባለሥልጣናት ከግብርና ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሽግግር ፍጥነት አዝጋሚነቱ ላይ መግባባታቸውን፣ ይህንን ለመቀየርም በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት በማድረግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ መግለጻቸውን ሪፖርቱ ያትታል፡፡
በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ በሚኖረው ኢኮሚያዊ ሚና ላይ መግባባታቸውን፣ በተለይም ስትራቴጂካዊ ከሚባሉት ዘርፎች ውጪ ያሉትን ዘርፎች ለግሉ ዘርፍ ክፍት ለማድረግ እየሠሩ መሆናቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
ይሁን እንጂ በመንግሥት የመሠረተ ልማት ተቋማት የአገር ውስጥና የውጭ ብድር ክምችት በሚፈጥረው ተፅዕኖ ላይ መግባባት አለመቻላቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡  እነዚህ ተቋማት ለሚያገኙት ብድር የኢትዮጵያ መንግሥት ዋስትና እንዳልሰጠና ተቋማቱ እንደ ንግድ ድርጅት በማትረፍ ላይ ተመሥረተው የሚሠሩ በመሆናቸው፣ በራሳቸው ዕዳውን እንደሚከፍሉና እንደ መንግሥት ዕዳ ሊታይ አይገባውም የሚል ክርክር በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አማካይነት መቅረቡን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
ነገር ግን የእነዚህ ተቋማት አጠቃላይ ሀብትና ዕዳን የሚቆጣጠር ኤጀንሲ ለማቋቋም መስማማታቸውን፣ እንዲሁም እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ አትራፊ የመንግሥት ተቋማት ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት ለመንግሥት እንዲያቀርቡ መስማማታቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
በተያያዘ ዜና አሁን ያለው የመንግሥትም ሆነ የመንግሥት ተቋማት የአገር ውስጥና የውጭ ብድር ክምችት ተፅዕኖ እንደማያመጣ የሚገልጸው መንግሥት፣ ዓለም አቀፍ ቦንድ (ሶቨሪን ቦንድ) ለመሸጥ መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል፡፡ መንግሥት ውሳኔውን የወሰነው የአገሪቱን የፋይናንስ ምንጭ ለማስፋፋትና አገሪቱ እምነት የሚጣልባት መሆኑን በመግለጽ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በማቀድ መሆኑን፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድ ባለፈው ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከሁለት የውጭ ባንኮች ጋር ድርድር እየተደረገ መሆኑንና እስከ ታኅሳስ ወር ድረስ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡ አቶ ሱፍያን እንደሚሉት የመንግሥትን ሉዓላዊ ቦንድ ለዓለም አቀፍ ገበያው በማቅረብ የሚገኘው ብድር ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ ይውላል፡፡ ይሁን እንጂ ለየትኞቹ የመሠረተ ልማት ዘርፎች እንደሚውል አልገለጹም፡፡
መንግሥት ወደ ዓለም አቀፍ የቦንድ ገበያው ለመግባት የወሰነው በሦስት ታዋቂ ዓለም አቀፍ ተቋማት የአገሪቱ ብድር የመሸከምና የመክፈል ደረጃ ተመዝኖ በአማካይ የ‹‹B›› ደረጃ ከተሰጠው በኋላ ነው፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት መንግሥት በሁለትዮሽ ድርድር ሲያገኝ ከነበረው የአገሮች ብድር በመውጣት ተጨማሪ አማራጮችን እየፈለገ ይገኛል፡፡ ከላይ ከተገለጸው ዓለም አቀፍ የቦንድ ሽያጭ በተጨማሪ የፖታሽ ማዕድን እምቅ ሀብቱን በዋስትና በማስያዝ የመበደር እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen