Netsanet: ይህ አያሳፍርም ? ወይ ፓርላማ!!

Donnerstag, 12. Juni 2014

ይህ አያሳፍርም ? ወይ ፓርላማ!!

Jun 12/2014
የኢትዮ-ጅቡቲ የውሃ አቅርቦት ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ሳያፀድቀው የውሃ ቁፋሮው መጠናቀቁ አነጋጋሪ ሆነ
* ኢትዮጵያ በዓመት ለጅቡቲ የወደብ አገልግሎት ከ 7 መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች ተብሎ ይገመታል።
.......................................................................................................
በኢትዮጵያና በጅቡቲ መንግስታት መካከል በውሃ አቅርቦት መስክ ትብብር ለማድረግ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይፀድቅ የውሃ ቁፋሮው ስራ ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁ ተገለፀ።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል aበሽንሌ ዞን በኩሊ ሸለቆ ልዩ ስሙ ዋሮፍ በተባለ ቦታ ላይ CGCOC የተባለ የቻይና ኩባንያ ለጅቡቲ መንግስት የሚቀርበውን የውሃ መጠጥ የከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮን ማጠናቀቁ ለማወቅ ተችሏል። ቀጣይ የውሃ መስመር ዝርጋታውን ለማከናወን በሸለቆው ውስጥ የወራጅ ውሃ የሚፈስበትን መስመር በመከተል ለውሃ ዝርጋታው ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል።
የውሃ ዝርጋታው የሚከናወንባቸው ቦታዎች በቅደም ተከተል ከሺንሌ - ሚሎ - ሐረዋ - አዲጋላ - ለአስራት - አይሻ - ደወሌ - በመጨረሻም ጅቡቲ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው ስሜ አይጠቀስ ያሉ ከሥራው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ግለሰብ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ “በሁለቱ ሀገሮች መካከል በውሃ አቅርቦት መስክ የተደረገው የስምምነት ሰነድ ወደ ተግባር ከመለወጡ በፊት የስምምነቱ ረቂቅ ሰነድ (አዋጅ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መፅደቅ ነበረበት። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የውሃ ቁፋሮ መጠናቀቁ ለፓርላማው የውሳኔ ኀሳብ የተሰጠውን ዝቅተኛ ደረጃ ያሳያል። የአስፈፃሚው አካል ሥልጣን ከፓርላማው እንደሚመነጭ እየታወቀ የፓርላማውን ውሳኔ ሳያገኝ የውሃ አቅርቦቱ የስምምነት ረቂቅ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉ መሠረታዊ የሕግ ስህተት በመሆኑ በይፋ ፓርላማው ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ተገቢውን ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል” ብለዋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ለውሃው አቅርቦት የሚያስከፍለው ክፍያ አይኖርም በሚለው ነጥብ ላይ ያነጋገርናቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያ በሰጡን አስተያየት፤ ከጅቡቲ ጋር ወደብን በተመለከተ ያለን ስምምነት አገልግሎት ብቻ ማግኘት ነው። በኢንቨስትመንት መልኩ ሃብት አፍስሰን በወደቡ የአገልግሎት ሥራ ላይ መሰማራት አንችልም። ይህ በሆነበት ሁኔታ ለጅቡቲ መንግስት የነፃ ውሃ አቅርቦት ስምምነት መፈፀማችን ለእኔ ግልፅ አይደለም። የረቂቅ ስምምነቱም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በተመለከተ የሚለው አንዳች ነጥብ የለም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሽንሌ ዞን ለጅቡቲ የውሃ ማሰራጫ 20 ሔክታር መሬት በነፃ የምትሰጥ መሆኗንና ከዚህ በተጨማሪ የውሃ ልማቱ ለሚካሄድበት ደግሞ አራት ሺ ሔክታር መሬት እንደምትከልል ሰፍሯል። የውሃ አቅርቦቱ ስምምነት ለ30 ዓመታት እንደሚፀና ረቂቅ አዋጁ ይገልፃል።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሣምንት የቀረበው በኢትዮጵያና በጅቡቲ መንግሥታት መካከል በውሃ አቅርቦት መስክ ትብብር ለማድረግ በሁለቱ መንግሥታት የተፈረመው የኢኮኖሚ ስምምነት ሰነድ ላይ እንደተጠቀሰው ጅቡቲ ለሕዝቧ ከምታቀርበው ውሃ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው ከጉድጓድ የሚገኝ መሆኑ እና በከፍተኛ ደረጃ ጨዋማ መሆኑን ይጠቅሳል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረገው ጥናት በኢትዮጵያና በጅቡቲ ድንበር በሚገኘው በሽንሌ ዞን ከፍተኛ የመሬት ውሃ መኖሩ የተረጋገጠ ሲሆን፤ በዚህ አካባቢ የተገኘው የውሃ ክምችት ከፍተኛ በመሆኑ ከአካባቢው አልፎ ለጅቡቲ ከተማ የውሃ አቅርቦት ሊውል እንደሚችል ጥናቱ ማረጋገጡን ይጠቅሳል።
በአንፃሩ ኢትዮጵያ በዓመት ለጅቡቲ የወደብ አገልግሎት ከ 7 መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች ተብሎ ይገመታል። sendeknewspaper.

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen