Netsanet: መቅዲሹ፤ የምክር ቤት አባል በቦምብ ጥቃት ተገደሉ፤

Montag, 21. April 2014

መቅዲሹ፤ የምክር ቤት አባል በቦምብ ጥቃት ተገደሉ፤

April 21/2014
አንድ የሶማሊያ የምክር ቤት አባል በዛሬዉ ዕለት መቅዲሾ ዉስጥ በደረሰ የቦምብ ጥቃት ተገደሉ። አንድ ሌላ የምክር ቤት አባልና አንድ ሲቪል ደግሞ ቆሰሉ። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲዋሊ ሼኽ አህመድ ሶማሊያ ያለመታከት ሕዝብ የሚያገለግሉ እና ሀገሪቱን መልሶ ለመገንባት የሚደክሙ ቁርጠኛ የምክር ቤት አባል አጣች ብለዋል። ኢሳቅ ሞሐመድን የገደለዉ ጥቃት የደረሰዉ መንግስት ከአሸባብ ታጣቂዎች የሚሰነዘረዉን ጥቃት መከላከል ላይ ያተኮረ የሶስት ቀን የፀጥታ ጉባኤ በሚያደርግበት ወቅት እንደሆነ የፈረንሳይ የዜና ወኪል አመልክቷል። ትናንት ጉባኤዉን የከፈቱት የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሀሰን ሼኽ ሞሀመድ  ሶማሊያን ዉስጥ ላለፉት 23 ዓመታት የተንሰራፋዉ የሕገወጥነት ባህል ማክተሚያ ተቃርቧል ማለታቸዉ ተሰምቷል። የምክር ቤት አባሉ የተገደሉት መኪናቸዉ ላይ በተጠመደ ፈንጂ ሲሆን ፍንዳታዉ ባስከተለዉ ቃጠሎ ህይወታቸዉ ማለፉ ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈሪ ዱላ ያሉት ጥቃት በዋና ከተማዋና በመላዉ ሶማሊያ የተከናወነዉን ለዉጥ ሊያሰናክል አይችልም ማለታቸዉ ተዘግቧል። አሸባብ ከሶማሊያ ትላልቅ ከተሞች በአፍሪቃ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል እየተገፋ ቢወጣም፤ አሁንም ተደጋጋሚ የቦምብና የሽምቅ ዉጊያ ዓይነት ጥቃት ማድረሱን ቀጥሏል። ይህን ጥቃትም ያደረስኩት እኔዉ ነኝ ማለቱን ዘገባዎች አመልክተዋል።

http://www.dw.de/%E1%8B%AD%E1%8B%98%E1%89%B5/s-11646

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen