Netsanet: ፍርድ ቤቱ አንድ ሺህ ብርና የመንግስት ሰራተኛ ዋስ ጠየቀ

Donnerstag, 10. April 2014

ፍርድ ቤቱ አንድ ሺህ ብርና የመንግስት ሰራተኛ ዋስ ጠየቀ

April 10/2014
Dawit Solomon
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሶስት አባላት መቶ አለቃ አንዳርጌ መስፍን፣ሐብታሙ ታምሩና አሸናፊ ጨመዳ በዛሬው ዕለት የካ ምድብ ችሎት ቀርበው አስገራሚ ዋስትና ተጠይቆባቸዋል፡፡
ፓርቲው የ‹‹እሪታ ቀን› በማለት ለሰየመው ሰላማዊ ሰልፍ መገናኛ አካባቢ በራሪ ወረቀት ሲበትኑ የዛሬ ሳምንት በህገ ወጥ መንገድ የተያዙት የፓርቲው አባላት በዛሬው ዕለት ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡የፓርቲው አመራሮችና አባላት የትግል አጋሮቻቸውን ጉዳይ ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በመምጣታቸው ጉዳያቸው በግልጽ ችሎት መታየት ይገባው የነበረ ቢሆንም በቢሮ በኩል ጉዳያቸው እንዲታይ ተደርጓል፡፡
የአንድነት አባላትን ጉዳይ ይመለከቱ የነበሩት ዳኛ ማሞ ሞገስ ተቀይረው ዳኛ ሬድዋን ጀማል ተሰይመዋል፣የዛሬው ቀጠሮ ፖሊስ ቀረኝ የሚለውን ምርመራ አጠናክሮ እንዲያቀርብ ካልሆነም በነጻ እንዲሰናበቱ ለመወሰን የነበረ ቢሆንም ‹‹ተጠርጣሪዎቹ አመጽ ለማስነሳት በማቀድ ወረቀት በትነዋል›› የሚለውን ክሱን የሚያስረዳ ማስረጃ ሊያቀርብ አልቻለም፡፡ተጠርጣሪዎቹ ‹ለሰላማዊ ሰልፉ እውቅና መስጠት ይገባው የነበረ አካል በመዘግየቱ እንጂ ወረቀት መበተናችን ህገ ወጥ አያሰኘንም› በማለት ከክሱ በነጻ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡
ዳኛው በስተመጨረሻ እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ ብርና የመንግስት ሰራተኛ በዋስትና እንዲያቀርቡ በማዘዝ ፋይሉን ወደ መዝገብ ቤት እንዲመለስ አድርገዋል፡፡ገንዘብ በዋስትና እንዲያቀርቡ ከተጠየቁ በኋላ የመንግስት ሰራተኛ በዋስትናው ላይ እንዲጨመር መደረጉም አስገራሚ እንደሆነ በስፍራው የነበሩ አባላት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆነ ሰው ሲታሰር የመንግስት ሰራተኛ ዋስ እሆናለሁ ቢል ከስራው ሊያፈናቅሉት እንደሚችሉ ስለሚገምት ለተቃዋሚዎች የመንግስት ሰራተኛን ዋስ አድርጎ መጠየቅን ፍርድ ቤቱ እንዲለውጥ የፓርቲው አመራሮች ለዕለቱ ዳኛ አቤት ብለዋል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen