Netsanet: ሚሊዮኖች ድምጽ – የባልቻ አባ ነፍሶ ልጆች እንሁን !

Samstag, 12. April 2014

ሚሊዮኖች ድምጽ – የባልቻ አባ ነፍሶ ልጆች እንሁን !

April 12/2014
አቦጊዳ _ ነጻነት ዋጋ ያስከፍላል። አገር ቤት ያሉ ወገኖቻችn እጅግ በጣም ከባድና ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት ፣ ለነጻነትና ለኢትዮጵያ አንድነት፣ እልህ አስጨራሽ ትግል እያደረጉ ነው። «ሽብርተኞች ናቸው» በሚል በቃሊት ፣ በቂሊንጦ፣ ዝዋይ በመሳሰሉ ዘግናኝ እሥር ቤቶች እየማቀቁ ያሉ ፣ የሰላምና የዴሞክራሲ አርበኞች የሆኑ፣ ብርቅዬ የኢትዮዮጵያ ልጆችን መመልከቱ ይበቃል። አንዱዋለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋ ፣ ርዮት አለሙ እያለን ብዙ መዘርዘር እንችላለን።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአንድ በሩጫ ላይ «ረብሻቹሃል» በሚል ፖሊሲ ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ፣ ሰባቱን የ«ጣይቱ ልጆች» አስሮ ማንገላታቱ በስፋት ተዘግቦ ነበር። በዚህ ሳምንትም፣ የአዲስ አበባ ፖሊሲ፣ ሕዝብን ለመጠበቅና ለማገለገል ሳይሆን፣ ሕዝብን ለማወክና ለማሸበር የተሰማራ እንደሆነ በድጋሚ ያረጋገጠበት ሁኔታ ነዉ የነበረው።
ዘጠኝ የአንድነት አባላት፣ ሕገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት፣ መጋቢት 28 ቀን ሊደረግ ታስቦ ለነበረው ሰላማዊ ሰልፍ፣ በራሪ ወረቀት በማደል ቅስቀሳ ያደርጋሉ። አልፈሩም። አልደነገጡም። «ሰው ያለ ነጻነቱ ምንድን ነው ?» በሚል፣ ጀግንነታቸውን አሳዩ። አራቱ ወንድሞቻችን ከፍተኛ ድብደባ ሲደርስባቸው፣ ሁለቱ የረሃብ አድማ አድርገው ከአምሰት ቀናት እሥር በኋላ ይፈታሉ። ሶስቱ፣ ምንም እንኳን ፍርድ ቤቱ ምንም ወንጀል አልተገኘባቸው የሚል ድምዳሜ ቢደርስም፣ አንድ ሺህ ዶላርና የመንግስት ሰራተኛ ዋስ አቅርቡ በማለቱ፣ እስከአሁን በእሥር ላይ ናቸው።
እነዚህ ዘጠኙ የአንድነት አባላት፣ በድፍረታቸውና በቆራጥነታቸው በርግጥ የባልቻ አባ ነፍሶ ልጆች መሆናቸውን በገሃድ አሳይተዋል። ባደረጉት ሥራ እና በከፈሉት መዋእትነት ትግል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አሳይተዉናል።
አዎን ነጻነት ዋጋ ያስከፍላል። አገራችን ኢትዮጵያ ሕግ የበላይ የሆነባት፣. ዜጎቿ በሁሉም የአገሪቷ ክፍል ሳይፈሩ፣ ሳይሸማቀቁ የሚኖሩባት፣ ሰብአዊ መብት ያለ ገደብ የሚከበርባት፣ አንድነቷና ሉአላዊነት የተጠበቀና የበለጸገች ኢትዮጵያ እንድትሆን ከፈለግን፣ ዘጠኝ አይደለም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጥይቱ ልጆች፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የባልቻ አባ ነፍሶ ልጆች ያስፈልጋሉ።
የሚሊዮኖች ድምጽ እንቅስቃሴ ተጀጀመረ እንጂ አላለቀም። በባህር ዳርና በደሴ፣ የታየው ጅማሬ እንጂ ፍጻሜ አይደለም። ከአገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ሁሉ መነቃነቅ እንዳለብን ለማሳሰብ እንወዳለን። ባለለንበት ቦታ እንደራጅ። እንዴት መሳተፈ፣ እንዴት መርዳት እንዳለብን እንመካከር። ትግሉ የአንድነት ድርጅት ሳይሆን የሚሊዮኖች ነው። ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን። የጣይቱ ልጆች፣ የባልቻ አባ ነፍሶ ልጆች እንሁን።
የአዲስ አበባዉ ቅስቀሳ ከተጀመረ ከመጋቢት 25 ቀን ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 2 ድረስ የነበረዉን ፣ በባልቻ አባ ነፍሶ ልጆች የደረሰዉን ለማንበብ ከታች ይመለከቱ። በገንዘብ መርዳት የምንፈልግ http://www.andinet.org በመሄድ በፔይፓል መርዳት አስተዋጾ ማድረግ እንችላለን። ተጨማሪ ማብራሪ ካስፈለገም millionsforethiopia@gmail.com በሚለው አድራሽ ኢሜል ቢያደርጉልን ሊያገኙን ይችላሉ።
ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዚያ 2 የባልቻ አባ ነፍሶ ልጆች ሁኔታ እንደሚከተለው ይከታተሉ
ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2006 ዓ.ም
በለገሃር አካባቢ ሲቀሰቅሱ የነበሩ፣ ወጣት አክሊሉ ሰይፉና ሰለሞን ፀሐዬ፣ በለገሃር ፖሊስ ጣቢያ ከፍተኛ ድብደባ ይፈጸምባቸዋል። ሲ.ኤም.ሲ አካባ፣ ኤፍሬም ሰለሞን እና ታሪኬ ኬፋ በተመሳሳይ ሁኔት በፖሊስ ይደበደባሉ። በየካ ክፍል ከተማ፣ እውቁ ደራሲ መቶ አለቃ አንዳርጌ መስፍን፣ ሃብታሙ ታምሩና አሸናፊ ጨመዳም ሕግ መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን መብት ተጠቅመው ሰላማዊ የቅስቀሳ በራሪ ወረቀት ሲያሰራጩ በፖሊስ ይታሰራሉ።በቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ በካሳንሺስ አካባቢ፣ ወርቁ እንድሮ እና አክሊሉ ሰይፉ በተመሳሳይ ሁኔታ ታስረዉ ወደ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ይወሰዳሉ። በዚችዉ አንድ ቀን ብቻ አራት የአንድነት አባላት ሲደበደቡ አምስት ወደ ወህኒ ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ ተወስደዋል።
ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2006 ዓ.ም
የአንድነት አመራር አባላት ፖሊሶች የታሰሩት እንዲፈቱ፣ ታሳሪዎቹ ሕግን አክብረዉ በሰላማዊ መንገድ ፓርቲው መመሪያ ሰጧቸው የቀሰቀሱ እንደሆነ ለማስረዳት ቢሞክሩም እስረኞቹ «ከአዲስ አበባ ፖሊስ መምሪያ በስማችን ደብዳቤ ካልተፃፈልን አንለቃቸውም» በሚል፣ ፍርድ ቤት ሳይወስዷቸው፣ ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ ዜጎች ለሁለተኛ ቀን በወህኒ እንዲቆዩ አድርገዋል።
ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2006 ዓ.ም
አሁንም እስረኞች ክስ ሳይመሰረትባቸው ለሶስተኛ ቀን በእስር እንዲቆዩ ይደረጋል።
እሁድ መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም
እስረኞቹ ለአራተኛ ቀን ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ ፣ በእስር አሁን ይቆያሉ።
ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2006 ዓ.ም
አንድነት ፓርቲ ለመጋቢት 28/2006 ጠርቶት በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ለህዝብ የተዘጋጀ በራሪ ወረቀት ሲበትኑ በህገ ወጥ መንገድ በቁጥጥር ስር ከዋሉት የአንድነት ፓርቲ አባላት መካከል በስድስተኛ ፖሊስ ጣብያ የሚገኙት፣ አክሊሉ ሰይፉና ወርቁ እንድሮ መታሰራቸውን በመቃወም የርሃብ አድማ ይመታሉ።
አክሊሉን እና ወርቁ ጨምሮ በየካ ክፍለ ከተማ የታሰሩ ሌሎች ሶስት የአንድነት አባላትም ለአምስተኛ ቀን እንዲታሰሩ ይደረጋል።
ማክሰኞ መጋቢት 30 2006 ዓ.ም 
‹‹የእሪታ ቀን›› ሰላማዊ ሰልፍ ለህዝብ የተዘጋጀ በራሪ ወረቀት ሲያሰራጩ ከተያዙት አምስት የአንድነት አባላት መካከል ስድስተኛ ፖሊስ ጣብያ የነበሩትና የርሃብ አድማ የመቱት ወርቁ እንድሮና አክሊሉ ሰይፉ ፖሊስ በትናንትናው ዕለት፣ ከአምስት ቀናት እሥር በኋላ ያለምንም ዋስትና ይለቃቸዋል።
በየካ ክፍል ከተማ የታሰሩ መቶ አለቃ አንዳርጌ፣ ሃብታሙ ታምሩና አሸናፊ ጨመዳ ግን ለስድስተኛ ቀን በ እሥር እንዲቆዩ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በ እስር እኒቆዩ ይደረጋል።
ረእቡ ሚያዚያ 1 2006 ዓ.ም
የካ ፖሊስ ጣብያ የታሰሩት መቶ አለቃ አንዳርጌ መስፍን፣ ሃብታሙ ታምሩና አሸናፊ ጨመዳ በማለዳዉ የካ ምድብ ችሎት ቀርበው ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጣቸዋል።
የየካ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ክስ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ ያለ ፓርቲው ፈቃድ ወረቀት በመበተን አመጽ እንዲነሳ አድርገዋል፣ሌሎች ተባባሪዎቻቸውም ስላልተያዙ እነርሱን በመያዝ ምርመራዬን እንዳጠናክር ተጨማሪ የሰባት ቀን ቀጠሮ ይፈቀድልኝ ››ብሏል፡፡ችሎቱን ለመከታተል በቦታው ተገኝተው የነበሩት የአዲስ አበባ የአንድነት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ነብዩ ባዘዘው፣ ፍርድ ቤቱን በማስፈቀድ‹‹እነዚህን ሰዎች ወረቀት እንዲበትኑ አመራር የሰጠናቸው እኛ ነን፡፡ፖሊስ እነርሱን ፈትቶ እኛን ይሰር ››ከማለታቸውም በላይ‹‹የአዲስ አበባ መስተዳድር ላቀረብንለት የእውቅና ጥያቄ የዘገየ ምላሽ በመስጠቱና ቀኑ እየተቃረበ በመምጣቱ ህዝብ የማስተባበር ስራ እንዲሰራ አድርገናል፡፡መስተዳድሩ የሰልፉን ቀን እንድንቀይር የጠየቀን አርብ ዕለት ነው፡፡አባላቶቻችን ግን የታሰሩት ሐሙስ ዕለት ነው ፡፡ወረቀቱ ከደረሰን በኋላ የቅስቀሳ ስራችን አቁመን ህጉን አክብረናል፡፡ፖሊስ ግን ወገንተኛ ሆኖ አባላቶቻችንን አስሮ እያጉላላ በመሆኑ ያለምንም ዋስትና እንዲፈቱልን እንጠይቃለን››ብለዋል፡፡
ዳኛ ማሞ ሞገስ ፖሊስ ከአዲስ አበባ መስተዳድር የተጻፈውን ደብዳቤ በመመልከት እንዲወስን አመጽ እንዲነሳ ስለመስራታቸው መረጃ አለኝ የሚል ከሆነም ለነገ እንዲያቀርብ ያዛሉ። እስረኞች ለሰባተኛ ቀን በወህኒ እንዲቆዩ ይደረጋል።
ሐሙስ ሚያዚያ 2 ቀን 2006 ዓ.ም
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሶስት አባላት መቶ አለቃ አንዳርጌ መስፍን፣ሐብታሙ ታምሩና አሸናፊ ጨመዳ በዛሬው ዕለት የካ ምድብ ችሎት ቀርበው አስገራሚ ዋስትና ይጠየቅባቸዋል።
ፓርቲው የ‹‹እሪታ ቀን› በማለት ለሰየመው ሰላማዊ ሰልፍ መገናኛ አካባቢ በራሪ ወረቀት ሲበትኑ የዛሬ ሳምንት በህገ ወጥ መንገድ የተያዙት የፓርቲው አባላት በዛሬው ዕለት ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡የፓርቲው አመራሮችና አባላት የትግል አጋሮቻቸውን ጉዳይ ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በመምጣታቸው ጉዳያቸው በግልጽ ችሎት መታየት ይገባው የነበረ ቢሆንም በቢሮ በኩል ጉዳያቸው እንዲታይ ተደርጓል፡፡
የአንድነት አባላትን ጉዳይ ይመለከቱ የነበሩት ዳኛ ማሞ ሞገስ ተቀይረው ዳኛ ሬድዋን ጀማል ተሰይመዋል፣ የዛሬው ቀጠሮ ፖሊስ ቀረኝ የሚለውን ምርመራ አጠናክሮ እንዲያቀርብ ካልሆነም በነጻ እንዲሰናበቱ ለመወሰን የነበረ ቢሆንም ‹‹ተጠርጣሪዎቹ አመጽ ለማስነሳት በማቀድ ወረቀት በትነዋል›› የሚለውን ክሱን የሚያስረዳ ማስረጃ ሊያቀርብ አልቻለም፡፡ተጠርጣሪዎቹ ‹ለሰላማዊ ሰልፉ እውቅና መስጠት ይገባው የነበረ አካል በመዘግየቱ እንጂ ወረቀት መበተናችን ህገ ወጥ አያሰኘንም› በማለት ከክሱ በነጻ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡ዳኛው በስተመጨረሻ እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ ብርና የመንግስት ሰራተኛ በዋስትና እንዲያቀርቡ በማዘዝ ፋይሉን ወደ መዝገብ ቤት እንዲመለስ አድርገዋል፡፡
ገንዘብ በዋስትና እንዲያቀርቡ ከተጠየቁ በኋላ የመንግስት ሰራተኛ በዋስትናው ላይ እንዲጨመር መደረጉም አስገራሚ እንደሆነ በስፍራው የነበሩ አባላት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆነ ሰው ሲታሰር የመንግስት ሰራተኛ ዋስ እሆናለሁ ቢል ከስራው ሊያፈናቅሉት እንደሚችሉ ስለሚገምት፣ ለተቃዋሚዎች የመንግስት ሰራተኛን ዋስ አድርጎ የጠየቀዉን ፍርድ ቤቱ እንዲለውጥ፣ የፓርቲው አመራሮች ለዕለቱ ዳኛ አቤት ብለዋል፡፡

ሐሙስ ሚያዚያ 2 ቀን 2006 ዓ.ም
ዳኛው የአንድነት አመራር አባላትን ጥያቄ አልተቀበለም። እስረኞቹ አንድ ሺህ ብር ከፍለው፣ የመንግስት ሰራተኛ ዋስ አቅርበው ይፈታሉ። እስረኞቹ የደረሰባቸው ነገር ወደ ኋላ እንደማይጎትታቸው፣ ትግሉን የበለጠ እንደሚያጠናክሩ ይናገራሉ።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen