Netsanet: የቶሮንቶና የነቀምት ግንባር፣ የአንድነት የሶስት ወር ዘመቻ

Donnerstag, 10. April 2014

የቶሮንቶና የነቀምት ግንባር፣ የአንድነት የሶስት ወር ዘመቻ

April 10, 2014

ተክለሚካኤል አበበ፤ ቶሮንቶ

የማርቆስ ብዙነህ ደብዳቤ፤
1-     “በርካታ ትምህርት ቤቶች፤ ዩኒቨርስቲና የመንግስት ተቋማት በሚገኙበት አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የማይቻል በመሆኑ፤ የተጠየቀው የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ጥያቄ ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን እንገልጻለን” ይላል፤ በአዲስ አበባ መስተዳድር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቅ ክፍል ሀላፊ፤ በአቶ ማርቆስ ብዙነህ ማንደፍሮ፤ መጋቢት 23 ቀን 2006/2014 የተፈረመው ደብዳቤ፡፡ አንድነት፤ ሰልፉን ለማድረግ ያቀረባቸው መስመሮች 3 ሲሆኑ፤ ሶስቱም መስመሮች ከቀበናው የአንድነት ጽ/ቤት ይነሳሉ፡፡ አንደኛው መስመር በአራት ኪሎና በፒያሳ አድርጎ፤ ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ጽ/ቤት ያመራል፡፡ ሁለተኛው አማራጭ በአራት ኪሎ ተጉዞ፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አልፎ መስቀል አደባባይ ያበቃል፡፡ ሶስተኛው አማራጭ፤ በአራት ኪሎ ፒያሳ፤ ቸርችልን ይዞ ድል ሀውልት ጋር ያበቃል ነበር የሚለው፡፡ ከላይ እንደተመለከታችሁት፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር፤ ሶስቱም አማራጮች አልተመቹትም፡፡ የተመረጡት መስመሮች በርካታ ትምህርት ቤቶች የትምህርትና የመንግስት ተቋማት ስለሚገኙበት፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ግንባታ ያለባቸው መንገዶች ስለሆኑ፤ እንዲሁም በእለቱ የህዳሴው ግድብ ግንባታን የተመለከቱ ዝግጅቶች ስላሉ፤ መስተዳድሩ ሰልፉን ሳይፈቀድ ቀረ፡፡
2-    አንድነት ክልከላው ሕገወጥ ነው፤ ሰልፋችንን እንቀጥልበታለን ብሎ አቋሙን ሲያሳውቅ፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ዘግይቶም ቢሆን፤ ተለዋጭ ቀንና መንገድ እንደሚቀበል ጠቆመ፡፡ ወትሮም ቢሆን የአዲስ አበባ መስተዳድር የተከተለው ስልት የማዳከም፤ የማበሳጨት፤ የማሰናከልና ተስፋ የማስቆረጥ እንጂ ጨርሶ የመከልከል አይመስልም፡፡ ስለዚህም ድርጅቱ በተዘጋጀበትና በመረጠው ቀን ባይሆንም፤ በሌላ ቀን እንዲሆን ለመለወጥ አስገደደ፡፡ በርግጥ የአዲስ አበባ መስተዳድር የመጀመሪያውን ሰልፍ ያሰናከለበት ምክንት አግባብ ባይሆንም፤ የአንድነት ልሳን ፍኖተ-ነጻነት፤ የአዲስ አበባ መስተዳርን የዘገየ እሺታ አስጩሆ የዘገበበት መንገድ ብልሀት ይጎድለዋል፡፡ ፍኖት ነጻነት፤ “በመጨረሻ የአዲስ አበባ መስተዳድር እጅ ሰጠ” ነው ያለው፡፡ ይሄ አይነቱ ረታናችሁ፤ አሸነፍናችሁ አካሄድ መንግስት የሚያሸሽ ስለሆነ፤ ፍኖተ ነጻነት ከዚህ አይነቱ አናዳጅ ርእሰ-ዜና መራቅ አለበት፡፡ ኢሳትም ይሄን አይነት ሰራንላችሁ፤ የታባታችሁ የሚል አዋራጅ አዘጋገብ አልፎ አልፎ ይተገብራል፡፡ ፈጣሪ ጊዜና ጉልበት ከሰጠኝ፤ ይሄ አይነቱ ጠላትን የማዋረድና የጽንፈኝነት አካሄድ ለምን እንደሚጎዳ እጽፋለሁ፡፡ ለጊዜው የፍኖተ ነጻነት ርእስ እንዳልተመቸኝ ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡
ስለሕገመንግስት፤ መብት ተረጋግጧል ወይስ ተረግጧል
3-   የሆነ ሆኖ፤ ወደሰልፉ ጉዳይ ስንመለስ፤ አሁን በስራ ላይ ባለው የኢትዮጵያ ሕገመንግስት መሰረት፤ ዜጎች በመሰላቸው ርእስ፤ በጣማቸው ምክንያት፤ በታያቸው ሕልም፤ በተሰማቸው ደስታ፤ ባሳዘናቸው ሰበብ፤ መንግስትን ደግፈውም ይሁን ተቃውመው፤ ሀሳባቸውን በተቃውሞ ወይም በድጋፍ የመግለጽና የመሰብሰብ መብታቸው ተረጋግጧል፡፡ ሕገ-መንግስቱ ራሱን በራሱ ያስፈጽም ይመስል፤ ሕወሀት/ኢህአዴግ ብዙውን ግዜ እንዲህ ያለው መብት በሕገ መንግስቱ ተከብሯል፤ በሕገመንግስቱ ተረጋግጧል እያለ የሚያጭበረብረው ነገር ስላለ፤ ይሄንን የተቃውሞ ሰልፍ በህገመንግስቱ ተከብሯል የሚል አረፍተነገር የተመለከተ ሰው፤ ጥንቃቄ ካላደረገ በስተቀር በሀይለኛው ይሳሳታል፡፡ በሕገ መንግስቱ መሰረት፤ ተረጋግጧል የሚለው ቃል፤ ተከብሯል በሚለው መተርጎም ቢኖርበትም፤ በኢትዮጵያ በተግባር እንደምናየው ግን፤ ተከብሯል በሚለው ሳይሆን፤ በሕገመንግስት ተረግጧል በሚለው ቢተረጎም ይቀላል፡፡ መብቱ በሰበብ አስባቡ ተሸራርፏል፡፡ በአንድነትና በሰማያዊ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ የሚደርሰውን ለተመለከተ ይሄንን መረዳት አያዳግተውም፡፡
4-   ለምሳሌ ሕገመንግስቱ ሰልፍ ከማድረግ በፊት ለሚመለከታቸው አካላት ስለማሳወቅ ብቻ ሲናገር (የአቶ ማርቆስ ብዙነህ ማህተም የሰልፍና ስብሰባ ማሳወቅ ኦፊሰር ነው ይላል)፤ ህግ አውጪዎቹና አስፈጻሚዎቹ ደግሞ፤ የለም ሰልፍ አሳውቅ ሳይሆን አስፈቅድ ነው ብለው ተረጎሙት፡፡ መተርጎም ብቻ ሳይሆን፤ ሕገ መንግስቱ ያረጋገጠውን መብት፤ ሰልፍን የተመለከቱ አዋጆችና ደንቦች አውጥተው ረጋገጡት፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ መስተዳድር የስብሰባና ሰልፍ አሰራር ስነ-ስርአት አንቀጽ 5.1 ከላይ በተጠቀሱት የመንግስትና የትምህርት ተቋማት አካባቢ ሰልፍ ማድረግ አይቻልም ይላል፡፡ በካናዳ ቢሆን፤ እነዚህን ሕገመንግስታዊ መብት የሚሸራርፉ አዋጆችና ደንቦች፤ ፍርድቤቶች ዋጋ የለሽ ህጎች ብለው ይወስኑባቸው ወይም ያመክኗቸው ነበር፡፡ እኛ አልታደልንምና፤ እስካሁን እንዳየነው፤ የኢትዮጵያ ፍርድቤቶች እንዲህ ያለውን ሕግ የመሻር ወይም፤ ሕገመንግስቱን ይጥሳል ብለው የመወሰን ስልጣንም ወኔውም አልተመለከትንባቸውም፡፡ ከተመለከትንም፤ ወይ ፍርዱ ወይ ዳኛው አይጸናም፡፡ መንግስት እንዲህ ነው ካለ፤ የኢትዮጵያ ፍርድቤቶችም አብረው እንዲያ ነው ይላሉ፡፡ ከመንግስት ጋር ይስማማሉ፡፡
የት ሄደን እንሰለፍ፤ ነው ወይስ እንሰየፍ
5-   ሰልፍ 48 ሰዓት ቀደም ብለህ አሳውቅ የሚለው ድንጋገጌ ሰልፍ አስፈቅድ በሚለው አዋጅ ተሸርፎ ብቻ አላቆመም፡፡ ከአንድነትና መኢአድ እንዲሁም ሰማያዊ ፓርቲ ስኬታማ ሰልፎች በኋላ ደግሞ ሰሞኑን የምንመለከተው፤ ጭራሽኑ ሰልፍ መሰለፊያ ስፍራ የሚያሳጣ ሁኔታ እንዳለ ነው፡፡ ቀደም ሲል ሰልፍ የተከለከለባቸው ስፍራዎች የጦር ሰራዊት ካምፖች፤ ሆስፒታሎችና መሰል ስፍራዎች ነበሩ፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ በትምህርትቤቶች ወይም ዩኒቨርስቲዎች አካባቢም ሰልፍ ማድረግ አይቻልም የሚል ደንብ ወጣ፡፡ ቀጥሎ በእምነት ተቋማት ማለትም በመስጊድና በአብያተክርስቲያናት አካባቢ አይቻልም የሚል አዋጅ/ደንብ ይመጣል፡፡ በአዲስ አበባ በሁሉም ማእዘን ቢኬድ፤ ትምህርትቤት ባይኖር፤ ሆስፒታል አለ፤ ሆስፒታል ባይኖር፤ የጦር ካምፕ አለ፤ የጦር ካምፕ ባይኖር፤ ቤተ-እምነት አለ፤ ቤተ-እምነት ባይኖር፤ ዩኒቨርስቲ አለ፤ ዩኒቨርስቲ ባይኖር መዋእለ-ሕጻናት አለ፤ ያም ባይኖር የሆነ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ሰለፍ ሊደረግ የሚችልባቸው ስፍራዎች ውሱን በጣም ውሱን ሊሆኑ ነው፡፡ ደግሞስ የተቃውሞ ሰልፍ አንድም መንግስት እንዲሰማው ለማድረግ ሆኖ ሳለ፤ በመንግስት ተቋም አጠገብ መሰልፍ አይቻልም የሚሉት ደንብ እንዴት ያለ ደንብ ነው፡፡ ተቃጠልን እኮ ጎበዝ፡፡
የአንድነት የሶስት ወር ዘመቻ
6-   እንግዲህ በዚህ ሁሉ ሕገመንግስቱን የሚሸራርፉ የተጻፉ ደንቦችና አዋጆች፤ ያልተጻፉ አፋናዎችና ትንኮሳዎች ውስጥ ተሸሎክሉከው ነው፤ አንድነቶችና ሰማያዊዎች የተቃውሞ ሰልፎችን የሚያደርጉት፡፡ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ፤ (ከዚህ በኋላ አንድነት እያልኩ ነው የምጠራው)፤ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ ከአዲስ አበባ ተጀምሮ አዲስ አበባ የሚያበቃ፤ በ15-17 ከተሞች የሚደረግ፤ የኑሮ ውድነትን፤ የሰብአዊ መብት ጥሰትና አፈናና፤ የመሬት ባለቤትንትን፤ የሚመለከቱ የተቃውሞ ሰልፎችን አሰናድቷል፡፡ አንድነት በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የሚደርጋቸውን ሰልፎች በገንዘብ ለመርዳት በውጭ አገር የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ኢትዮጵያዊያን ቃል እየገቡ ነው፡፡ መቼም ሲያትል ጎንደሬ ይበዛል፤ ጎንደርን ወስዷል፡፡ አትላንታ አንድ ከተማ ወስዷል፡፡ ላስ ቬጋስም እንደዚያው፡፡ እስካለፈው ወር መጨረሻ ድረስ የቀሩት ከተሞች አምስት ብቻ ናቸው፡፡ የቶሮንቶ አንድነት የድጋፍ ሰጪ ማህበርም የነቀምት ከተማን ሰለፍ ለመርዳት ቃል ገብቷል፡፡ ቀደም ሲል እሁድ ማርች 23 ቀን የአንዱዓለም አራጌን መጽሀፍ ለማከፋፈልና እስረኞችን ለማሰብ በተጠራ ዝግጅት ላይ የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ ታምራት ይገዙ ቶሮንቶ መቀሌንም ስፖንሰር እንደሚያደርግ አስታወቋል፡፡ ስለዚህ፤ ቶሮንቶ ሁለት ከተሞችን ስፖንሰር ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ይሄ በረከት ሲያንሰን ነው፡፡
እነሆ ቅስቀሳ፤ አጋርነት ለነቀምት፤
7-   አንድነት ቶሮንቶ፤ ለነቀምቱ ሰልፍ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ቅዳሜ ኤፕሪል 26 ቀን፤ ከሰዓት በኋላ፤ ከ3pm ሰኣት ጀምሮ፤ 2050 ዳንፎርዝ ጎዳና ላይ በሚገኘው ሂሩት ካፌ፤ የአብረን እንዋል መርሀግብር አዘጋጅቷል፡፡ ይሄ ጽሁፍ በከፊል የዚያ ዝግጅት ቅስቀሳ አካል ነው፡፡ ልቀስቅሳችሁ ተዘጋጁ፡፡ ቅስቀሳው እንዲህ የሚል ነው፤ አገር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፤ ከላይ የጠቀስናቸውን መሰናክሎች አልፈው የተቃውሞ ሰልፍ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ሲሉ፤ ሰልፋቸው በኢህአዴግ ሰራዊት ወይም ፖሊስ ወይም ደህንነቶች እንጂ፤ በገንዘብ እጦት ምክንያት እንዳይሰናከል የማድረግ ግዴታ አለብን የሚል ነው፡፡ በቶሮንቶ አካባቢ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን፤ በዚህ መደበኛ ባልሆነ፤ የአብረን እንዋል ዝግጅት ላይ በመገኘት፤ የበኩላችንን የገንዘብ ልገሳ እንድናደርግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ፤ ቅዳሜ ኤፕሪል 26 ቀን፤ 2014 ዓ.ም፤ ከሰኣት በኋላ፤ ሂሩት እንገናኝ፡፡
8-   በነገራችን ላይ፤ ቶሮንቶ በቆየሁባቸው ያለፉት 13 ወራት፤ ከገንዘብ ማሰባሰብ ጋር በተያያዘ ቶሮንቶ የሚንቀሳቀሰው ከአቅም በታች ነው ማለት ይቻላል፡፡ ትንሽ ቋጣሪ መስሎብኛል፡፡ በርግጥም በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ፖለቲካ ነክ ዝግጅቶች ላይ የሚታደሙትንና ያላቸውን የሚወረውሩት ቸሮች፤ ተመሳሳይና የተወሰኑ ሰዎች በመሆናቸው፤ የዚህ ከአቅም በታች የመንቀሳቀስ ተጠያቂዎች እነማን እንደሆኑ እንጃ፡፡ ላለፈው ስርየት ሆኖ፤ ስለሚመጣው ሳስብ ግን፤ እኔ እንዲህ ያለውን አገራዊ ዝግጅት የማየው እንደበረከት ነው፡፡ ይሄ በረከት ለሁላችሁም መድረስ አለበት፡፡ ስለዚህ የመጪው ኤፕሪል 26፤ የአንድነት በረከት እንዳያመልጣችሁ፤ ሂሩት ካፌ እንገናኝ፡፡ በእለቱ በተለያየ ምክንያት መገኘት ያልቻለም፤ የገንዘብ ልገሳውን በሰው መላክ እንደሚችል ወይንም በአንድነት ባንክ ሂሳብ Unity for Human Rights and Democracy: TD Trust; የባንክ ሂሳብ ቁጥር፡ 12682 0041 0883 5209213 መክተት እንደአማራጭ እንደተቀመጠ፤ አንድነት ቶሮንቶ ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡
ከደሴ ወደአዲስ፤ … ወደነቀምት፤ በዚህ 22 አመት እንደነቀምት የተጎዳ ማን አለ፤
9-   በርግጥ የአንድነት የአዲስ አበባ ሰልፍ በተያዘለት ቀን መጋቢት 28 አልቀጠለም፡፡ ይሄ ጽሁፍ ወደህትመት ሲላክ፤ የአዲስ አበባው ሰልፍ ሚያዚያ 5 እንደሚደረግ ቢገመትም፤ አሁን ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ሰልፉ ቅዳሜ፤ የሰልፉም አቅጣጫ ወደጃንሜዳ ካልሆነ እያለ ነው፡፡ ማደናበር፤ ማናደድ፤ ማዘናጋት ይሉታል ይሄንን ስልት፡፡ እኔ፤ ብልጥ ልጅ የሰጡትን ይዞ ያለቅሳል ነው የምለው፡፡ ፖለቲካና ሕይወት ,ባልመረጥነው መንገድ ውስጥ የመረጥነውን ለማግኘት የምናደርገው ሩጫ ነውና፡፡ መጋቢት 28 ቀን በደሴ የተደረገው ሰልፍ ደማቅና የሚያበረታታ፤ በርግጥም ለሌሎች ከተሞችም መነሳሳትን የሚያመጣ እንደሆነ አስተውያለሁ፡፡ ስለዚህ፤ ነቀምትን ከደሴ የተሻለ ለመቀስቀስና ለማሰለፍ፤ ሁላችንም መረባረብ እንዳለብን ቀስቃሽ አያስፈልገንም፡፡ ደግሞስ በዚህ 22 አመት በኦነግ ስም እንደነቀምት የተጎዳ ማን አለ፡፡ ስለዚህ ነቀምት ተሰልፎ እሪይ ይል ዘንድ ግድ ነው፡፡ ደሴ ነቅሎ ወጥቷል፡፡ ነቀምትም ነቅሎ ይወጣል፡፡ ነቀምት ነቅሎ እንዲወጣም እኛም ከዚህ ከቶሮንቶ ነቅለን እንወጣለን፡፡ ቅዳሜ፤ ሚያዚያ 26 ቀን፤ ከሰዓት በኋላ፤ ከ3 እስከ 6 ሰዓት ሂሩት እንገናኝ፡፡
10-  ለተጨማሪ የአንድነት ዝርዝር አገልግሎቶችና መረጃዎች በአካል በአንድነት በጽህፈት ቤታት፤ ወይም ከታች በተጠቀሱት የመገናኛ መንገዶች ያግኙን፡፡ አንድነትን ለማግኘት፤ ኢሜል፤ unityforhumanrights@gmail.com ፤ ድረገጽ፤ http://andnettoronto.blogspot.ca/. የጽህፈት ቤት አድራሻ፡ B2- 2017 Danforth Avenue, Toronto, ዳንፎርዝ ላይ፤ ከዉድባይን ባቡር ጣቢያ በስተምስራቅ 50 ሜትር ራቅ ብሎ፤ ከዘመን እንጀራ መደብር በተቃራኒ፤ ከትብብር መረዳጃ እድር ጎን፡፡
ተክለሚካኤል አበበ ነኝ፤ ቶሮንቶ፤ ሚያዚያ፤ 2006/2014
የደሴ ሰላማዊ ሰልፍ (ፎቶ በነብዩ ሃይሉ)

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen